የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (19)

13. ንግግርህ ብቁ ይሁን (መ)

7. ቀልድና ተረት አታብዛ

ተረት ገሀዱን ዓለም በቃላት መግለጥ ነው ። የሰው ልጆች እውነትን በደረቁ መጋፈጥ ይከብዳቸዋልና ተረት በእንስሳትና በአራዊት እየተመሰለ ሰውን የሚመክር ነው ። በጽኑ የታመመ ሰው ፈትፍተው እንዲያጎርሱት ፣ በእጅ ሳይሆን በማንኪያ እንዲሰጡት ተረትም የሰውን ስሜትና ፍርሃት ተረድቶ በዘዴ እውነትን ማስተላለፊያ መንገድ ነው ። ተረት ተናጋሪው ለራሱ ሳይሆን ለሰሚው የሚጨነቅበት የትሕትና መንገድ ነው ። ሰሚው ክብሬ ተደፈረ እንዳይል ደግሞም አንድን ሰው ዒላማ ያደረገ መልእክት እንዳይመስል ተረት ዓለም አቀፋዊ ትምህርት ነው ። ሰዎች አብሮ መመከር ብቻ ሳይሆን አብሮ መታመምም ይደፍራሉ ። “ላገር የመጣ ነውና አያስፈራም” ይላሉ ። ተረት የገሀዱ ዓለም ነጸብራቅ ነው ። ተረት ሕፃናት የሚያድጉበት የጆሮ ፍትፍት ነው ። ተረት የሚፈጥርና ተረት የሚናገር ሰው በዓለም ላይ ትልቁ ሊቅ ነው ። ምክንያቱም እርሱ ባለበት ደረጃ ሳይሆን ሰዎች ባሉበት ደረጃ ዝቅ ብሎ ማስተማር የሚችል በመሆኑ ነው ። ብዙ ሊቃውንት የጋን ውስጥ መብራት ሆነው የቀሩት ባሉበት ደረጃ ቆመው ለማስተማር ስለሚፈልጉ ነው ። እግዚአብሔርን ስንለምን እውቀትን ብቻ ሳይሆን እውቀቱን የምናስተላልፍበት ዘዴም ስጠኝ ብለን መለመን ይገባናል ። ብዙ አዋቂዎች እንኳን ለሰው ለመናገር ፣ እያጉረመረሙ ለራሳቸውም ለመንገድ ይቸገራሉ ።

ተረት ትልቁና ትንሹ የሚሰሙት ቋንቋ ነው ። እግዚአብሔር አምላክ በተፈጥሮ ውስጥ ደግነቱንና ፍቅሩን ብቻ ሳይሆን እውቀትንም ገልጧል ። ስለዚህ እንስሳት ፣ አራዊትና እጽዋት ለተረት ግብዐት ሆነው ያገለግላሉ ። እግዚአብሔር እንስሳትንና አራዊትን ለማስተማሪያነት እንደሚጠቀም መጽሐፈ ኢዮብ ይነግረናል ። በወንጌልም እባብ ፣ ርግብ ፣ ተኩላ ፣ አበቦች ፣ ወፎች ማስተማሪያ ሆነው አገልግለዋል ። ተረት ትልቁ የማስተማሪያ ዘዴ ነው ። እውነትን በፍቅር መግለጥ እንዳለ ሁሉ እውነትን በጥበብ መግለጥ እርሱ ተረት ይባላል ። ተረት ግን ሲበዛ ሰዎች ይንቁታል ። ተናጋሪውም ተረታም ይባላል ። ማርም ሲበዛ ይመራልና ራቅ ራቅ እያሉ ጣል ጣል ማድረግ ብልህነት ነው ። ተረት መደበኛ ምግብ ሳይሆን በመደበኛው ምግብ ውስጥ የሚገባ ማባያ ነው ። በአጭር ቃል ተረት የትምህርት ማጣፈጫ ነው ።

ቀልድ ቦታ የተለዋወጠ እውነት ነው ። ቀልድ በተቃራኒው የመናገር ጥበብ ነው ። ተረት ፍጥረትንና ሁኔታዎችን መሠረት ሲያደርግ ቀልድ ደግሞ ከእውነቱ ተቃራኒ ሆኖ እውነትን ያስተላልፋል ። በተረት ሰዎች እየተገረሙ ይማራሉ ፣ በቀልድ ደግሞ እየሳቁ እውነትን ይጨብጣሉ ። ትምህርት አስጨናቂ መሆን የለበትም ። ትምህርት ጭንቀት ካለበት እንኳን አዲስ ሊያውቁበት ፣ ያወቁትም ይጠፋል ። ጌታችን አንቀጸ ብፁዓንን ያስተማረበት ተራራ ከፊት ለፊቱ የጥብርያዶስ ባሕር ይታያል ፣ ተራራው በውብ አበባ ተሸፍኗል ። ይህን ቦታ እየጎበኘው ሳለ አንድ ሰባኪ ጋር ተገናኘን ። እርሱም፡- “ጌታችን እንዲህ አሳርፎ ያስተማረውን የተራራውን ስብከት ፣ እኛ ሕዝቡን እያስጨነቅን እንሰብከዋለን” አለኝ ።

አንዱን ሥጋ አንዷ ባለሙያ ቀይ ወጥ ፣ ሌላዋ አልጫ ፣ ሌላዋ ዱለት ፣ ሌላዋ ክትፎ አድርገው ይሠሩታል ። አንዱ እውነት በተለያየ ባለሙያ ሲቀርብ ጣፋጭ ፣ የሚያቃጥል ፣ የሚጥም ሁኖ ይቀርባል ። ይህ ሁሉ ከእውቀት የተፈናቀለውን የሰው ልጅን ወደ ልቡናው ለመመለስ ነው ። ይልቁንም አትንኩኝ የሚሉትን ፣ ከሕዝብ መሐል ወጥተው ራሳቸውን እንደ አማልክት የሚያዩትን የምድር ገዥዎች ፊት ለፊት መናገር በሰይፍ ያስቆርጣልና ቀልድና ተረት የመናገሪያ ዘዴ ሆኖ ያገለግላል ። ሁልጊዜ ቀልድ ማብዛት ግን ሰዎች ቀልዱን እንጂ እውነቱን ላይፈልጉት ይችላሉ ። በዚያው ወደ ቀልደኛነት ወደ አጫዋችነት መግባት ይመጣል ። የሚያስቅ ሰው ምንም ባይናገር ገና ሲታይ ይስቁበታል ። አስቃለሁ ባይ መጨረሻው መሳቂያ መሆን ነው ። ቀልድን አንዳንድ ጊዜ ጣል ማድረግ ሰዎች በፍርሃት እንዳይርቁን ያደርጋል ። ይልቁንም በሥልጣን ላይ ያሉ አንዳንዴ ቀልድ ሲናገሩ የሚሰማቸው ይረጋጋል ።

ሳቅ ለጤና ትልቅ በረከት ይሰጣል ። የተወጠረውን አካል ያፍታታል ። አንድ ሰዓት ስፖርት ከሚሠራው ሰው ይልቅ አሥር ደቂቃ የሚስቀው ሰው ይደክመዋል ፣ ይበረታታል ። ጭንቀትም ይለቀዋል ። ሳቅ አይብዛ እንጂ አስፈላጊ ነው ። አለመሳቅ ፣ ሁልጊዜ ጥቁር ደመና ሁኖ መዋል መንፈሳዊነት የሚመስላቸው ሰዎች አሉ ። መለኪያ ከሌላቸው ሰዎች ጋር መኖር እንዴት ከባድ ነው !

አንዴ ጃንሆይ ጠጅ እንጠጣ ብለው ጣይቱ ሆቴል ከጠባቂዎቻቸው ጋር ይገባሉ ። አንዱ ጠጥቶ የሰከረ ወጣት እየተንገዳገደ ሊወጣ ሲል የጃንሆይ ፎቶ ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ ያያል ። ፎቶው በጣም ጥቁርና የማያምር ሆኖ ታየው ። ለስድብ ተዘጋጀና እየተኮላተፈ “አሁን ይሄ ሰው ነው በማርያም!? አሁን ይሄ ሰው ነው…” ብሎ ወደ ጎን ዞር ሲል ጃንሆይና ጠባቂዎቻቸው ቆመው ያያል… “የምሬን ነውኮ አሁን ይሄ ምኑ ሰው ይመስላል መልአክ ነው እንጂ!” ብሎ ነፍሱን አተረፋት ይባላል ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ