13. ንግግርህ ብቁ ይሁን (ሠ)
9. ቋንቋ አትቀላቅል
ቋንቋ በባቢሎን ርግማን ፣ በበዓለ ሃምሳ በረከት ሆኗል ። ብዙ ቋንቋ ማወቅ በጣም ጠቃሚ ነው ። በቋንቋ ውስጥ የሰው ልጅ ባሕል ፣ ፍልስፍና ፣ ታሪክ ፣ ቅኔና የተፈጥሮ ውበት አለ ። ቋንቋ ወደ ብቃት ሲሄድ ሥዕላዊ እየሆነ ይመጣልና ተፈጥሮ የዚህ ሥዕል ቡሩሽና ቀለም ነው ። ቋንቋ ወንዝ ስለሚያሻግር ብቻ ሳይሆን ጠቃሚ ስለሆነም ፣ አእምሮንም ስለሚያሰፋ ማወቅ ወሳኝ ነው ። የሰው ልጅ እስከ ሰባት ዓመት ዕድሜው ብዙ ቋንቋ የማወቅ ዕድል አለው ። ልጆችን የአራትና የአምስት ቋንቋ ባለቤት ማድረግ ይቻላል ። ቋንቋ ፍላጎት ፣ በድፍረት መናገርና ብዙ ማውራት ፣ ብዙ ማዳመጥ ካለ በቀላሉ እየታወቀ ይመጣል ። ቋንቋ ራሱን የቻለ እውቀት በመሆኑ አማርኛ ስለምንናገር አማርኛ እናውቃለን ማለት ላይሆን ይችላል ። የቋንቋውን ግሡን ፣ ሥሩን ፣ ሰዋስዉን ፣ ከፍና ዝቅ ፣ ጠበቅና ላላ የሚለውን ድምፁን መለየት አስፈላጊ ነው ። ቋንቋ በማንበብና በመጻፍ ሲዳብር የበለጠ የዝምታ ንግግር እየሆነ ይመጣል ። ማንበብና መጻፍ በዝምታ ያለ ፍንዳታ ነው ። የቋንቋ ብቃቱ ማንበብና መጻፍ ከሆነ የመናገር መጨረሻው ዝምታ ነው ማለት ነው ።
አያሌ ቀጣፊዎች ብዙ ቋንቋ የማወቅ ጥማት አላቸው ። ቅጥፈት ዓለምን የሚያጠብብ ፣ በሁሉ ቦታ ስደተኛ የሚያደርግ ነውና እነዚህ ሰዎች ብዙ ቋንቋ ያጠናሉ ። ብዙ ቋንቋ መሰብሰብ በውስጡ እውቀትንና ፍልስፍናን ማዳበር ካልተቻለ ልብን ቀውላላ ያደርጋል ። አንድን ነገር በደንብ ተረድቶ ያንን ማብሰል ፣ የበሰለውን ለትውልድ ምግብ አድርጎ ማቅረብ የሰው ልጅ ክብሩ ነው ። አዎ ብዙ ቋንቋ ብታውቅም ስትናገር አትቀላቅል ። በፍርድ ቤት የቆመ ተጠያቂ ቋንቋ እየቀላቀለ ቢናገር የፍርድ ሂደቱን እንደማሳት ስለሚቆጠር አንዱን መምረጥ ፣ ወይም አስተርጓሚ ማቆም አለበት ። የእያንዳንዱ ቀን ውሎአችን ጥንቃቄ የሞላበት ሊሆን ይገባዋል ። በአንድ ሰከንድ ስህተት መላው ዕድሜ ሊታጣ ይችላል ። ይልቁንም ያውቃል እንዲባል አንድ ሰባኪ ቋንቋ እየቀላቀለ ማስተማር አይገባውም ። ዓላማው ሰዎችን ስለ እግዚአብሔር ለማሳወቅ እንጂ ስለ ሕዝቦች ቋንቋ ለማስጠናት አይደለምና ሰባኪ ቋንቋ መቀላቀል አይገባውም ። በእግዚአብሔር ቤትም ዲያቆን ፣ ቀሲስ ፣ ብፁዕ አባታችን ከመባል የበለጠ ማዕረግ የለምና ዶክተር ፣ ኢንጂነር እገሌ እየተባለ መድረኩን ባያጣብብ ፣ አልተማሩም የሚባሉት ላይ የመብረቅ ሸክም ባይሆን መልካም ነው ። በሰለጠነውም ዓለም የትምህርት መጠሪያዎች የስም ማሳመሪያ አይሆኑም ። እኛ አገር ሥራውን ፈጽሞ ወደ አገሩ የተመለሰውን ሳይቀር “አምባሳደር እገሌ” እያልን እንጠራለን ። የስም ጥማታችን ወደር የለውም ።
ስም የሚያበዙ ሰዎች ሥራ የላቸውም ። ሰው ስሙና ልብሱ ካልቀለለው ሥራ መሥራት አይችልም ። የእግዚአብሔር አደባባይ የእኛ የሕይወት ታሪክ መንገሪያ አይደለም ። “መልከ ጥፉ በስሙ ይደግፉ” እንዲሉ ብዙ ሥራ ስለሌለን ስም ማብዛት ሥራ መስሎናል ። እኛ ረጅሙን መወዳደስ በምናቀርብበት ቅጽበት አንድ ምእመን በተኩላ እየተነጠቀ ነው ። በየትም ዓለም አገልጋዮች ሠርተው ያሠራሉ ። ሠርተው ይደነቃሉ ። በእኛ አገር ግን ሥራ ጥለን ወሬን ገንዘብ አድርገን ፣ ድሀ ባስገባችው በስእለት ገንዘብ እንወዳደራለን ። የዚህ ውጤቱን እያየነው ነው ። በቶሎ ካልነቃን ላይድን እንቆስላለን ። አልጀሪያ ወይም ሂፖ የቅዱስ አውግስጢኖስ መንበር ነበረች ፣ ዛሬ የክርስትና ምልክት የላትም ። ቱኒዚያ የጥንትዋ ካርቴጅ ብዙ ቀኖና የተሠራባት የክርስቲያን አገር ነበረች ። ዛሬ የለችም ። ሊቢያ ወይም ቀሬና ብዙ ጳጳሳት ያስተዳደርዋት ትልቅ የክርስቲያን መዲና ነበረች ዛሬ የለችም ። የኑቢያ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ህልውና የነበራት ቤተ ክርስቲያን ነበረች ። ዛሬ የለችም ። ግብጽም ክርስትና የተስፋፋባት አገር ነበረች ። ዛሬ ክርስቲያን ተሸማቆ የሚኖርባት ፣ ከአገሩ ሕዝብ ቍጥርም ጥቂት ክርስቲያን ያለባት አገር ሆናለች ። የአገሬ ካህን በጊዜ ንቃ ። ለማልቀስም ዕድል ላይገኝ ይችላል ። እረኛ ይጠብቃል እንጂ ተኩላን ሲረግም አይውልም ።
አዎ ንግግርህ ክብር እንዲኖረው ፣ ካንተ የሚበልጥ ጸጋና እውቀት ያለው እንዲያደንቀው ቋንቋ አትቀላቅል ። “ይህን አማርኛ ጌታ ይገሥጸው” ያለ ፓስተር ሰምቻለሁ ። እንደ እርሱ አነጋገር የሚገልጥለት እንግሊዝኛ ነው ። “አባቱን አያውቅ አያቱን ናፈቀ” የሚባለው እንዲህ ላለው ነው ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም.