የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (23)

13. ንግግርህ ብቁ ይሁን (ሸ)

15. የማይወሩ ነገሮችን ለይ

አፋችን በተፈጥሮው መክፈቻ ብቻ ሳይሆን መዝጊያ ተበጅቶለታል ። ጥርስን የሚያህል የብረት አጥር ፣ ከንፈርን የሚያህል የሚሞቅ ምንጣፍ ተደርጎለታል ። ንግግርን ጨዋና ልከኛ ለማድረግ መንፈሳዊነት ፣ ጨዋ አስተዳደግ እጅግ ወሳኝ ነው ። አንዳንድ ሰዎች ዕድሜአቸው ቀላል አይደለም ፣ ነገር ግን የሚያወሩትን ነገር ማጥለል አይችሉም ። ዕድሜ አይለውጥም የሚባለው ለዚህ ነው ። ልጆችን ስናሳድግ የቱ እንደሚወራ ፣ የቱ የት ቦታ እንደሚነገር ፣ የቱ ፍጹም እንደማይወራ ማሳወቅ አለብን ። ይህ የአስተዳደግና የመንፈሳዊነት ክፍተት ዛሬ በጉልህ እየታየ ነው ። እኛ ኢትዮጵያውያን የተደበቀውን ማንነታችንን ማኅበራዊ መገናኛ እያወጣው ነው ። ሊነገሩ የማይገባቸው ነገሮች ብዙ ናቸው ። ጥቂቱን ማየት ብንችል መልካም ነው ።

ለሰዎች ያደረግነውን ውለታ ማውራት ፍጹም አይገባም ። ለራሳቸው ለሰዎቹ ይህን አድርጌልህ ነበር ማለት አስፈላጊ አይደለም ። ሰው በጠባዩ የሰጠውን አይረሳምና የዛሬ ሠላሳ ዓመት እንዲህ አድርጌልህ ነበር እያለ ሲያወራ ራሱን ያቀላል ። ሰዎች ውለታቸውን የሚያወሩት በተለያየ መንገድ ነው ። ውለታቸውን ለራሱ ለዋሉለት ሰው የሚናገሩት የመጀመሪያው ያ ሰው እንደ ጠላቸው ሲያስቡ ነው ። ሁለተኛው ከዚያ ሰው ጋር ያላቸው ግንኙነት መጨረሻ ላይ ሲደርስ ነው ። ሦስተኛው “ሰው በክፉ ይስለኛል እንጂ እኔ ቸር ነኝ” ለማለት ነው ። ሰውዬውን ለማገዝ ያደረግነውን ነገር ሰውዬውን ለማሳቀቅ ማዋል ፣ በማንኪያ ሰጥቶ በአካፋ መውሰድ ነው ። ሥጋውን ጠግኖ ነፍሱን ማፍረስ ነው ። ስጦታችን ልብንም ሥጋንም የሚጠግን መሆን አለበት ። በዚህ ዓለም ላይ ይዘን የመጣነውና ይዘን የምንሄደው ምንም ነገር የለም ። የሰጠነው የእኛ ያልሆነውን ሀብተ ሥላሴ የሆነውን ነው ። ደግሞም አንድ ቀን ትተነው ስንሄድ ተዝካራችንን እያወጡ ወስኪ ይራጩበታል ። ከመዝራት ይልቅ ገንዘባችንን ይበትኑታል ።

የማይወራ ነገር ሰዎች የነገሩን ምሥጢር ነው ። ምሥጢርን መሸከም የማይችል ሰው ጠባየ ቀላል የሆነ ሰው ነው ። ጓደኛ ለጓደኛው ልክ እንደ ንስሐ አባት ምሥጢሩን ሊደብቅለት ይገባል ። ምሥጢሩን የነገረን ሰው በምድር ላይ ከሚያከብሩን ሰዎች ቀዳሚው ነው ። የሰውን ምሥጢር ማውጣት ራስን ማዋረድ ነው ። “እገሌ ወሬ አያድርለትም/አያድርላትም” መባል ትልቅ ስድብ ነው ። ይልቁንም ሁለት ሆነን የሠራነውን ነገር ስንጣላ ማውጣት ተገቢ አይደለም ። ስንፋቀር ሌላውን ሰው ሸሽተን ነበር ። አሁን ስንጣላ ግን የዕድር ጡሩንባ ማስነፋት ፣ ስሙልኝ ማለት ተገቢ አይደለም ። ሰዎች ለሰርጋቸው ድምፁ በማይሰማ ወረቀት ይልካሉ ። ልቅሶአቸውን ግን በጡሩንባ ያስለፍፋሉ ። ዛሬ በአደባባይ የምንሰማው የትዳር ምሥጢር ፣ የባከነው የቤት ገመና የማኅበረሰቡን ውድቀት የሚያሳይ ነው ።

የአገር ምሥጢርን ማውጣት በአንገት ላይ ሰይፍ አንጠልጥሎ እንደ መዞር ነው ። በራሽያ ፣ በእንግሊዝ የተደበቁ የአሜሪካንን ምሥጢርን ያወጡ ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን ። የአገር ምሥጢርን ያወጡ ሰዎች ምሥጢሩን ካወጡ ቀን ጀምሮ ሞት ጥላ ሁኖ ይከተላቸዋል ። ምሥጢር ከጠበቅነው ይጠብቀናል ። ካባከነው አሳዳጃችን ይሆናል ። ከዚሁ ጋር የግላችንንም የቤታችንንም ምሥጢር ለማይችል ሰው መንገር ጥፋቱ የእኛ ነው ። ለመንፈሳዊ አባት ግን የማይነገር ምሥጢር ያለ አይመስለኝም ። ሰይጣን ለመንፈሳዊ አባት ድብቅ እንድንሆን በማድረግ ለትልቅ ውድቀት ይዳርገናል ። አባቶች፡- “ሞኝ ለጠበቃው ምሥጢር ይሸሽጋል” እንዲሉ ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ