የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (24)

14. ንግግርህ ብቁ ይሁን (ቀ)

18. አትፎክር

አንድ ሰው በእግዚአብሔር ሲያምን በዘመድ ፣ በሥልጣን ፣ በጉልበት ይፎክር እንደሆነ ወዲያው “በኃይለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ” ይላል ። ሠራዊትም ሠረገላም ፣ የአየር ኃይል የምድር ታንክ እንደማያድን በቀይ ባሕር የሰጠመው ፈርዖን ፣ ሰባት ዓመት ሣር የጋጠው ናቡከደነፆር ፣ ዓለምን አስገብሮ በዕድሜ ድህነት በ32 ዓመቱ የሞተው ታላቁ እስክንድር ምስክሮች ናቸው ። የማይናወጥ የሥላሴ መንግሥት ብቻ ነው ። ስመጥሮቹ ስማቸው ጠፋ ፣ ነጭ ልብሳቸው አስታብዮአቸው መሬት ለመርገጥ ይጸየፉ የነበሩ ጭቃ ሆኑ ። የድሀ ልጅ ብለው ይሳደቡ የነበሩ ዕራቁታቸውን ወደ መቃብር ወረዱ ። ሀብትም ፣ ሥልጣንም ፣ ዝናም ፣ ከበሬታም አያድንም ። የሚያድነው በችንካር ብዕር ፣ በደሙ ቀለም ፣ በሥጋው ሰሌዳ ፣ በቃልነቱ ንባብ ቀራንዮ የተነበበው የእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ ነው ።

ፉከራ የትምክሕት ልጅ ነው ። የተፈቀደ ትምክሕት አለ ። በእግዚአብሔር መመካት ተፈቅዷል። ያልተፈቀደው ፉክራ ሌላውን ለማሳነስ ፣ ለማስጨነቅ ፣ አፍ እያለው ዲዳ ፣ እግር እያለው ሽባ ለማድረግ የሚሞክር ነው ። ትልቅ ሃይማኖት አለኝ ፣ እርሱም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነው ። ቢመኩበት የሚያስመካ ነው ። ተዋሕዶ ምሥጢር ነው ። እኛ ኢየሱስን የተዋሐድን እንጂ የተቀበልን አይደለንም ። መቀበል ጅማሮ ፣ በአፍአ ያለ ግንኙነት ነው ። መዋሐድ ግን ክርስቶስ በእኛ ፣ እኛ በክርስቶስ ውስጥ መሆናችን ነው ። ታዲያ ሃይማኖታችን የምንኖረው እንጂ የምንፎክርበት አይደለም ። ሃይማኖተኛ በወንድሙ መጥፋት ያዝናል ፤ ፎካሪ ግን በውድቀቱ ይደስታል ። ሃይማኖተኛ “ምነው እኔ የቀመስኩትን ወንድሜ በቀመሰ” ይላል ፣ ፎካሪ ግን እኔ ከቆምሁበት አትቆምም ብሎ ጦር ይወዘውዛል ። ዛሬ ብዙ ፎካሪ ስላተረፍን ንስሐ ገብቶ የሚመለስ ቢመጣ እንኳ ደግመህ ውጣ እንለዋለን ።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ “ለልጅ ምክር ለአባት መታሰቢያ” በተሰኘው መጽሐፋቸው፡-

ልጄ ሆይ ! ለእኔ ለአባትህ እንደ መሰለኝ ከመጻሕፍት ሁሉ ወንጌል ትበልጣለች።
ይህንም ማለቴ አንተ በወንጌል ተምረህ ክርስቲያን ሆነህ እንድትኖር ብዬ ነው እንጂ ፤ የእኔ ሃይማኖት ይበልጣል የእኔ መጽሐፍ ወንጌል ትበልጣለች እያልህ ክርክርን ከሚወዱ ሰዎች እንድትከራከር ብዬ አይደለም” ብለዋል ።

ፉከራ የጦርነት የመጋደል ዋዜማ ላይ የሚሰማ ንግግርና ዜማ ነው ። ንግግር በፉከራ የሚቃኝበት ጊዜ አለ ። ፉከራ ዛቻ ፣ ማስፈራሪያ ያለው ነው ። በትዳር ፣ በወዳጅነት ውስጥ እየፎከረ የሚኖር ሰው አያሌ ነው ። ፎካሪ ደመ ሙቅ ቢሆንም ሌላውን ግን ይጎዳል ። ፎካሪን ሰው መልመድ ከባድ ነው ። ፉከራ ያለማድረግ ወንድም ነው ። የሚፎክር ሰው ስለማያደርግ በመጨረሻ እየተናቀ ይመጣል ። ውስጣዊ ኃይላችን የሚባክነው በዋናነት በአንደበታችን ነው ። የምናደርገውን መናገር ፣ ያደረግነውንም መናገር ተገቢ አይደለም ። ሰባኪ አዋጅ ነጋሪ እንጂ ፎካሪ አይደለም ። አዋጅ አትሳሳቱ የሚል ማስጠንቀቂያ ነው ፤ ፉከራ ግን “ምነው በተሳሳተና በዘመትኩበት” ባይ ነው ። የሃይማኖት አቀበትን ፎካሪዎች አይወጧትም ፣ ጸሎተኞች ግን ይወጡአታል ።

መዝሙሩ ወደ ፉከራ ከተለወጠ አምልኮ መሆኑ ይቀራል ። መዝሙር ወደ ላይ የሚያርግ ሲሆን ፉከራ ግን ወደ ጎን የሚምዘገዘግ ወንድምን ሰባሪ ዘንግ ነው ። ዛሬ አንዳንድ መዝሙር ፣ አንዳንድ ቅኔ ስንሰማ ብሽሽቅ ፣ ለጠላነው ሰው የአደባባይ ደብዳቤ መላላኪያ ይመስላል ። ራስን መግዛት ከሌለ ፣ ሰው በመዝሙርም እንኳ ይወራረፋል ። ሰባኪውም በቅዱስ ፍርሃት ፣ በሥላሴ ትምክሕት መቆምና መስበክ አለበት ። ያናደደውን ሰው ለመንቆር መቆም ክብርን ያሳንሳል ። በርግጥ ሰባኪ ሰው ነውና ስሜት አለው ፣ እግዚአብሔር በውጣ-ውረድ ውስጥ ካስተማረው ላይ የሚያስተምር መሆኑን መርሳት አይገባንም ።

ፉከራ አገር ሲወረር ፣ ድንበር ሲደፈር ፣ ሥርዓተ መንግሥት ሲናቅ ወንዱን ሴቱን ለማጀገን ታሪክን ማንነትን ጠቅሶ ማነቃቃት የተለመደ ባሕላችን ነው ። በኑሮ ላይ ደግሞም በወንድም ላይ ፉከራ ግን ከፍቅር መጉደል ነው ። ከፉከራው ትንሽ ላሰማህ፡-

ቢብለጨለጩ እንደ ቅቤ ቅል ፣
መተኮስና መምታት ለየቅል ፤
ቢብለጨለጩ በልብስ በጫማ ፣
ሊፈረጥጡ ድምፄ ሲሰማ ።

እምቢ!!!

በለው በለውና አሳጣው መድረሻ ፣
ማዕረግ አያውቅም ወንበዴና ውሻ ፤
ያመጣል መንገድ ይወስዳል መንገድ ፣
አንድ የሚጠላ አንድ የሚወደድ ፤
ሀገር አስነካሽ ልጅ አይወለድ ።

ስንፎክር ሌላውን እናሳንሳለን ። በእግዚአብሔር ሳይሆን በራሳችንና በልምዳችን መመካት እንጀምራለን ። ጸሎት እናቆማለን ፣ ሰልፋችን ሥጋዊ ይሆንና ሰይፍ መምዘዝ እንጀምራለን ። ይህ በሐዋርያው ጴጥሮስ የታየ ነው ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ