የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (25)

13. ንግግርህ ብቁ ይሁን (ሸ)

19. በሰው ቍስል አትፍረድ

የወደቀ ሰው የሚፈልገው የሚያነሣው እጅ እንጂ ስለ ውድቀቱ ጥናት የሚሠራበት ፈራጅ አይደለም ። የራሳችን ችግር ተራራ አህሎ ፣ የሰዎች ውጣ ውረድ አንሶ የሚታየን ጊዜ ብዙ ነው ። ኃጢአትን በሚመለከት የራሳችን ትልቅ በደል ቅንጣት ፣ የሰዎች ትንሽ ስህተት ቁልል ሁኖ ይታየናል ። ሰዎችን ከደረሰባቸው ችግር በላይ የሚከብዳቸው በየጊዜው የሚያስተናግዱት የሌሎች የፍርድ ቃል ነው ። ደካማ ሰዎች የሰውን መታመም ፣ መቸገርና መዋረድ ሲያዩ እነርሱ ቅዱስ ፣ ያ ሰው ርኩስ መስሎ ይታያቸዋል ። ይህች ዓለም ግን ለክርስቶስ ሕመምን ፣ ረሀብን ፣ ጥማትን ፣ ውርደትን የከፈለች ዓለም ናት ። እውነተኛው ፍርድ ያለው በሰማይ ነው ። ውድቀት የራሱ ሆነ ድምፅ አለው ። ሰውን ውድቀቱ የሚናገረውን ያህል የእኛ ቃል ሊናገረውና ሊገሥጸው አይችልም። ፈሪሳውያን ሁሉንም እጦት ከኃጢአት ጋር ያያይዙት ነበር ። ሰው የሚታመመው ፣ የሚያጣው ባለማመኑ ነው የሚሉ ዘመናዊ ፈሪሳውያንም በዚህ ዘመን አሉ ። እነዚህ ሰዎች በብዙ አቋራጭ መንገድ እንደሚጓዙ ሕሊናቸው ያውቀዋል ።

በሰው ቍስል እንጨት መስደድ ለተቀባዩ ከባድ ፣ ላቀባዩ ግን ቀላል ነው ። በእኛ ቍስል ላይ ግን የሐኪም እጅ ፣ የመድኃኒት ጠብታ ሲያርፍ እንሳቀቃለን ። በሰዎች ቍስል ላይ ሌላ ቍስል ለመጨመር ግን አንፈራም ። በራሳችን ላይ ግን የመፍትሔ እጆችንና ሥራዮችን ሳይቀር እንሸሻለን ። ለሰው መርዝን በደስታ እንበጠብጣለን ፣ ለእኛ ግን መድኃኒቱንም አጥብቀን እንመረምራለን ። “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ማለት ተጠንቀቅለት ፣ ይቅርታ አድርግለት ፣ አስብለት ማለት ነው ። በእኛ አገር ብዙ ችግር አለ ። ትልቁ ችግራችን “ምን ይሉኛል?” የሚለው ከንቱ ስጋት ነው ። ያልተገነባው ማንነታችን በሚሉን ነገርና በሚሰጡን ክፉ ስም ይፈራርሳል ። ቀላል ሰው በጥቂት ምስጋና ደመና ይነካል ፣ በጥቂት ነቀፋ መቀመቅ ይወርዳል ። አራት አምስት ልጅ የቀበሩ የሚያሳስባቸው ከራሳቸው መጎዳት ፣ ከልጆቻቸው ማለቅ በላይ “ምን ይሉኛል?” የሚለው ፍርሃት ነው ። ለሁሉም ነገር አስተንትኖ መስጠት ግዳጅ የሚመስለው የአገሬ ሰው ፣ የራሱን ትቶ በሰው ቤት ላይ የሚውል የሚያድረው ወገኔ ፈውሱ መቼ ይሆን! ይህችን ጽሑፍ በምንጽፍባትና በምናነብባት ቅጽበት በሰው ላይ ነገር የሚሠሩ ፣ የስም ጥላሸት የሚቀቡ ብርቱ ሥራ እንደ ያዘ ተጠምደዋል ። በልመና ስንዴ መኖራችን አያሳቅቀንም ። ለልመናም ብቁ አይደላችሁም ተብለን ገሸሽ ሲያደርጉን እናኮርፋለን እንጂ ይህን ታሪክ ለመለወጥ ወኔ ያጥረናል ። አናበድራችሁም ሲሉን ጭልም ብሎብን እንደናበራለን እንጂ “እንዴት አድርገን ለችግራችን ሞትን እንክፈለው” የሚል ጥንካሬ ርቆናል ።

በሰው ቍስል ላይ መፍረድ ትልቅ ጭካኔ ነው ። ጨካኝ ብለን የምንጠራቸው ሰይፍ የሚዙ ፣ ጥይት የሚተኩሱ ሰዎችን ነው ። ትልቁ ጭካኔ ግን በሰው ቍስል ላይ መፍረድ ነው ። ጫካ ላይ ቆመው ሰውን የሚያስጨንቁትን ብቻ ሳይሆን በከተማ ያሉትን ግፍ የማይፈሩ ጠበቃና ዳኞችን ፣ ሐኪምና ባለሙያዎችን አሸባሪ ብለን ለመጥራት ድፍረት ያስፈልገናል ። ሁሉም በአቅሙ የሚበድልባት አገር መፍጠራችን በእውነት ያሳዝናል ። አዎ በሰው ቍስል መፍረድ ትልቁ የአንደበት ውድቀት ነው ። የወደቀን ሰው እንዲነሣ ከማገዝ ውጭ ምንም ዓይነት አሉታዊ ድምፅ ማሰማት አይገባንም ። ሃይማኖት ማለት የወደቀውን አዳም የፈለገ ፣ የበዳይን ሞት ሞቶ የካሰውን አምላክ ማመን ነው ። ሰዎች የሚወድቁት አንዳንዴ መንገዱ ጠፍቷቸው ነው ፣ ሌላ ጊዜ የሚዘሉት መስሎአቸው ገደሉ ሰፍቶባቸው ነው ፣ አንዳንዴም እነሣለሁ ሲሉ ይወድቃሉ ፣ አተርፋለሁ ሲሉ ይከስራሉ ፣ አስደስታለሁ ሲሉ ያሳዝናሉ ። አላዋቂነታቸውም የውድታቸው ምክንያት ይሆናል ። ለመማር ፣ በርታ ለመባል ዕድሉን ባለማግኘታቸው ሰሰዎች ይወድቃሉ ።

የእግዚአብሔር እጆች የወደቀን ለማንሣት ተዘርግተዋል ። እኛ ባናነሣቸው እንኳ በወደቁት ላይ ምሣር ማብዛት አይገባንም ። ምሣር ወይም መጥረቢያ የምናበዛበት ዛፍ ትላንት በልምላሜው ደስ ያሰኘን ፣ በአበባው ተስፋ የሰጠን ፣ በፍሬው ያጠገበን ፣ በጥላው ያሳረፈን ፣ በውዝዋዜው አየሩን የቀዘፈልን ፣ በውበቱ ቤታችንን ውድ ያደረገልን ነው ። ይህ ዛፍ ሲወድቅ ግን ሁሉም መጥረቢያ ይዞ ይከተክተዋል ። ሰው ዛፍ አይደለም ፣ ወድቆ አይቀርም ፣ ይነሣል ። ዛፍ ሲያድግ ድምፅ የለውም ፣ ሲወድቅ ግን ድምፁ ይሰማል ። ስናድግ ብዙ ሰው እንዳላየ ያልፈናል ፣ ቅናቱ ዱዳ ያደርገዋል ። ስንወድቅ ግን ሁሉ ይሰማዋል ። በወደቀው ዛፍ የቆሙት ቢስቁ ያ የወደቀ ዛፍ የመጥረቢያ እጀታ ሁኖ ሊቆርጣቸው እንደሚመጣ ቋሚዎች ይዘነጋሉ ። ዛሬ እያስጨነቁን ያሉት ትላንት ወደቁ ብለን የሳቅንባቸው ፣ ወይም ገፍትረን የጣልናቸው ወገኖች ናቸው ። ንስሐ እስካልገባን በገመድነው ጅራፍ እየተገረፍን እንኖራለን ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 14 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ