የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (26)

13. ንግግርህ ብቁ ይሁን (ተ)

21. የቤተሰብህን ምሥጢር አታውጣ

አንዳንድ ሰዎች ምን ዓይነት መንፈስ እንደ ተቆራኛቸው ባይታወቅም ትላንት ያልነበራቸውን ማንነት ፣ የሌላቸው ትልቅነት ሲያወሩ ይሰማሉ ። ሕይወት ግን ጓዳም አደባባይም ናትና የሚያውቃቸው ሲመጣ እነርሱም ይሸማቀቃሉ ፣ ሰምተው ያመኑአቸውም መሳቂያ ያደርጉአቸዋል ። ከነበራቸው ትልቅነት ቀንሰው ቢያወሩ ፣ ክብራቸውን ቢሰውሩ የሚያውቃቸው መጥቶ ስለ እነርሱ ከፍታ ሲናገር መጀመሪያ ያከበሩአቸው ይበልጥ እያከበሩአቸው ይመጣሉ ። ዝቅተኛውን ስፍራ የመረጠ ውረድ አይባልም ። ከፍተኛው ስፍራ የመረጠ ግን አዋቂ ሲመጣ ዝቅ በል ይባላል ። ሌላው ያክብር እንጂ ራስን አጋንኖ ማቅረብ ተገቢ አይደለም ። በዚህ ዓለም ላይ ገነኑም በነኑም ሁሉም ኃላፊ ነው ። ጸንቶ የሚኖረው መጨመርና መቀነስ የሌለበት የሥላሴ ክብር ብቻ ነው ። “ጅብ የማያውቁት አገር ሂዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል” ይባላል ። ዛሬ ቄስ ነበርሁ ፣ መነኩሴ ነበርሁ ፣ መሪጌታ ነበርሁ እያሉ የሚያወሩ ፣ የሄዱበትን ሰፈር ለማስደሰትና የመጡበትን ለማስጠላት ጠንቋይ ነበርሁ እያሉ የሚያወሩ አያሌ ናቸው ። ከኢየሱስ ይልቅ ስለ አጋንንት መስማት የሚወድዱት ወገኖች የእነዚህን ነበርሁ ባዮችን ወሬ እንደ ፊልም በተመስጦ ያዳምጣሉ ። እኔ ቆንጆ ነኝ ለማለት እገሌ አስቀያሚ ነው ማለት አያስፈልግም ። የራስን እምነት ከፍ ለማድረግ የሌላውን እምነት ማዋረድ አይጠበቅም ። አዎ ቄስ ነበርሁ አይባልም ። ቅስና ፣ ምርግትና ነበርሁ የለውም ።

አንዳንድ ሰዎች እንዲሁ ነው የኖርሁት ለማለት ይዳዳሉ ። እንዳለ የሚኖር ቋጥኝ ብቻ ነው ። ሰው ከፍና ዝቅ ይላል ። ይሞላል ፣ ይጎድላል ፤ ይሳሳታል ፣ ይመለሳል ፤ ያገኛል ያጣል ፤ ይወድቃል ፣ ይነሣል ። እንዲሁ ምሁር ሆኖ የኖረ ሰው የለም ። ከሌላው ያልተቀበለ ምሉዕ ሰውም አይገኝም ። በቀጥታ ከእግዚአብሔር ነው የተማርሁት ፣ የሰው መምህር አላስተማረኝም የሚሉ ደፋሮችም አሉ ። ግን በሰው የሚያስተምር እግዚአብሔር ነው ። ነቢያትና ሐዋርያት ሰዎች ነበሩ ። ሰው የእግዚአብሔር መሣሪያ ነው ። በፍጥነትም በኃይልም የበረቱ ቅዱሳን መላእክት ሳሉ ደካማዎቹ እነ ጴጥሮስ ለስብከተ ወንጌል የተላኩት እግዚአብሔር በሰው መሥራት ስለሚወድድ ነው ። ሰውዬውን ከማንነቱ ፣ ከአቅሙ ለይተን በእርሱ በኩል የተላከውን መልእክት መቀበል ብልህነት ነው ። እኔ ትልቅ ዘር ነኝ ። አያቶቼን የታሪክ መጽሐፍ ላይ አገኘኋቸው ። የእኛ ደም ልዩ ነው ማለት ሞኝነት ነው ። ይዞ መገኘት እንጂ ነበርሁ ጥጋብ አይሆንም ። ሲያልፍ የማያምን ፣ ማለፉን የማይቀበል የዓለምን መልክ የማያውቅ ነው ። “በሮም ሲኖሩ እንደ ሮማውያን” ይባላልና ባለንበት አገር እንደ አገሩ መኖር እንጂ በታሪክ መፎከር ፣ ሥራ ማማረጥ ጥቅም የለውም ።

አባቴ ትልቅ ነው ይላል የሰው ሞኝ ፣
ትንሹም ትልቅ ነው እንጀራ ሲያገኝ ፤

ራሳቸውን ከሆኑት በላይ የሚገልጡ የአእምሮ መቃወስ ያለባቸው ወገኖች እንዳሉ ሁሉ የቤተሰባቸውን ምሥጢር አደባባይ የሚያሰጡ ወገኖችም አያሌ ናቸው ። እኔ የድሀ ልጅ ነበርሁ ብሎ ማውራት ለዛሬ ድሆች ተስፋ የሚሰጥ ነው ። ታሪካችን ለሌሎች ተስፋና ትንሣኤ ሊሆን ይችላል ። ከዚያ ባለፈ ግን የቤተሰብን ምሥጢር ማውጣት አይገባም ። ሰው ገመና ያለው ፍጡር ነው ። እርሱና እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቁት ማንነትም ያለው ምሥጢር የሆነ ፍጡር ነው ። ሁሉ አይነገርም ። አንደበት የተፈጠረው ለመናገር ቢሆንም ሁሉን ለመናገር አልተፈጠረም ። “ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል” ይላሉ ። ይልቁንም የትዳርን ምሥጢር በፍቅርም በጠብም ጊዜ ማውጣት ተገቢ አይደለም ። ሁለት ሰዎች ያሳለፉት ነገር ለሦስተኛ ሰው አይወራም ። “የጨዋ ልጅ ሲፋታ የሚጋባ ይመስላል” ይባላል ። ደግ ደጉን ያወራል ማለት ነው ። ላለቀ ነገር መልካሙን ማውራት ይገባል ። ክፉ ንግግር ቢቀጥሉም ፣ ቢለያዩም ጠቃሚ አይደለም ።

አንተ ግን ንግግርህን ጠቃሚ ለማድረግ የቤተሰብህን ምሥጢር ፣ የትዳርህን ገመና አታውጣ ። ይልቁንም በቤት ውስጥ እንኳ ሊወራ የማይገባውን ነገር ዛሬ በተለያየ መገናኛ ብዙኃን ስንሰማ ምን ያህል ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ እንዳለን ማሳያ ነው ። ትዳር አደባባይ ሲወጣ እንደ መዝናኛ የሚታይ ሳይሆን የሚያስለቅስ ነው ! ትዳር ከአማካሪ እንኳ ደግ አማካሪ የሚፈልግ ስስ ርእስ ነው!

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ