የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (28)

14. ቀጠሮ አክብር

ቀጠሮ የተጀመረው በእግዚአብሔር ነው ። ይህ ዓለም በመለኮታዊ ቀጠሮ የተፈጠረ ዓለም ነው ። ዘመን የሌለው ጌታ ዘመንን ለሰዎች ሰጠ ። ሰው በበደል በወደቀ ጊዜ ለመዳን ቀጠሮ ተሰጠው ። ሰው ከእግዚአብሔር ሳይለይ ከእግዚአብሔር ተለየ ። ለሆዱ እንጀራን ፣ ለአፍንጫው እስትንፋስን የሚያገኘው ከእግዚአብሔር ነው ። እንኳን በምድር በሲኦልም የሚኖረው በእግዚአብሔር ሕይወት ነው ። ጌታችን ወደ ምድር የመጣው ለሰዎች እንጀራ ለመስጠት ሳይሆን ራሱ ኅብስተ ሕይወት መሆኑን ለመግለጥ ነው ። 5500 ዘመን ሰው እንጀራ እየበላ ነበር ። ነፍሱ ግን ስደተኛና ረሀብተኛ ነበረች ። ሰው እግዚአብሔርን የሚክደው ከእግዚአብሔር የተቀበለውን እስትንፋስ መልሶ ሳይሆን በእግዚአብሔር ሕይወት ላይ ቆሞ ነው ። “በማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ!” ይባላል ። እርሱ የካዱትን ቢክድ ኖሮ ፍጥረት በምድር ላይ ባልቆየ ነበር ። እግዚአብሔር ቀጠሮን መጀመሩ ብቻ ሳይሆን የሺህ ዘመናት ቀጠሮን የሚሰጥ አምላክ ነው ። የሰው ልጅ በምድር ላይ ከሚኖረው ዕድሜ የረዘመ ቀጠሮ ተሰጠው ። ይህ ብዙ ፍቺ አለው ። የመጀመሪያው የሰው የህልውናው መጨረሻ መቃብር አይደለም ። በሥጋው ያጣውን በነፍሱ ሊክሰው የሚችል አምላክ አለው ። ዛሬ በሥጋ ጉድለታችን ስንፈራ ስንጨነቅ ጌታ ግን አይጨነቅም ። ምክንያቱም በሰማይም ሊጋብዘን ይችላልና።

እኛ ምንም ሳናደርግላቸው የሄዱት ወገኖቻችን የእግር እሳት ሆነውብን ይሆናል ። ደግነታችንን መቃብር ገድቦት ይሆናል ። በሰማያዊው ዓለምም የሚሰጥ አምላክ ግን ሞት ገደቡ አይደለም ። ከሰው ዕድሜ የሚረዝመው ቀጠሮ ለምን ተሰጠ ካልን ከ5500 ዘመን በኋላም የሚኖረው ሰው አዳም ስለሆነ ነው ። ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ ያላቸው እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚኖሩ ሆነው አይደለም ። የእነርሱን ሥራ የሚያስቀጥል ሁሉ ሐዋርያ ስለሆነ በደቀ መዛሙርቶቻችሁ ላይ አድሬ እሠራለሁ ማለቱ ነው ። ስለዚህ ጴጥሮስ ይህን ሲሰማ ብሞትም ሕያው ነኝ ፤ የመንፈስ ልጅ አለኝ ብሎ ይጽናናል ። የአዳምን ቀጠሮ ክርስቶስ ሲሰቀል የነበሩ ሁሉ ፍጻሜውን አይተዋል ። አንድ አዳም ነን ። አንድ ስለሆንን የአዳም በደሉና ጥፋቱ አግኝቶናል ። የአዳም መዳኑና ካሣው ነጻ አውጥቶናል ። በሞት አንድ ሁነን በኑሮ መለያየታችንና መከፋፋታችን ይገርማል ።

የእግዚአብሔርን ቀጠሮ ልዩ የሚያደርገው የማይረሳ አምላክ መሆኑ ነው ። እኛ ቀጠሮአችንን በመርሳት ፣ ባለመመቸት ፣ ባለመፈለግ ፣ በመስጋት ፣ ሌላውን ጉዳይ በማስበለጥ እንሰርዛለን ። እግዚአብሔር ግን መርሳት የሌለበት የሕሊናት ሁሉ ባለቤት ነው ። አይመቸውም አይባልም ፣ እርሱ የሌለውን ና ብሎ መጥራት የሚችል አምላክ ነው ። በሰጠው ተስፋ አይጸጸትምና አልፈልጋችሁም አይለንም ። የሚሽረው የለምና አይሰጋም ። የዘላለም ጉዳዩ እኛ ነንና የእርሱ ውዶች ነን ። እግዚአብሔር ቀጠሮን የሚያከብር አምላክ ነው ። የእርሱ ተከታዮች እርሱን ይመስላሉና ቀጠሮን ያከብራሉ ። “ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤” ገላ 4፡4 ።

አንተም ቀጠሮ መስጠትን ልመድ ። ምክንያቱም አንተ እንደ ተመቸህ ያ ሰው አይመቸውምና በድንገት ውረድ ፍረድ አትበል ። ዓመት ሙሉ የረሳኸውን ሰው ዛሬ ስታገኘው አልላቀቅህም ብለህ ስሜታዊ አትሁን ። ቀጠሮ መስጠት ለሰውዬው ምቾት ፣ ለጉዳዩ ክብደት ነው ። ቀጠሮ በሰጠህ ጊዜ ወዳጅህ ተኝቶ እንዲያድር ወይም ተዘጋጅቶ እንዲመጣ ርእሱን ንገረው ። የምፈልግህ በዚህ ምክንያት ነው ብለህ አሳውቀው ። ምናልባት ስጦታ ልትሰጠው ሊሆን ይችላል ። ለምን እንደ ቀጠርከው ካላወቀ ግን የሞት ያህል ያስጨንቀዋል ። ስትቀጥረውም አንተም እርሱም የማትረበሹበት ቦታ ይሁን ። ያ ወዳጅህ የማይፈልገው ሰው ካለ ይዘህበት አትሂድ ። የማይፈልገውና ከዚህ በፊት ተነጋግራችሁበት የተዘጋ ነገርን አታንሣበት ። የቀጠሮውን ርእስ ለመንገር የማይቻል ከሆነ በሻይ ቡና ርእስ አግኘው ። እየጋበዝህ ግን ነገር አታብላው ። በምድር ላይ እጅግ ባለጌ የሆኑ ሰዎች ምግብ እየጋበዙ ነገር አብረው የሚያበሉ ናቸው ። አንድ ኪሎ ሥጋ ጋብዘው አራት ኪሎ ሚጥሚጣ ነስንሰው ይሄዳሉ ።

ቀጠሮ ስትሰጥ ያ ሰው ተጨንቆ እንደሆነ ለማረጋገጥ “ይመችሃል ወይ?” ብለህ ጠይቅ ። ምቾቱን ፍላጎቱን የምትነካበት ሰው እየጠላህ ይመጣል ። ሰው ከምንም በላይ ነጻነቱን የሚወድድ ፍጡር ነው ። ቀጠሮ እጅግ አድርገህ አክብር ። ቀጠሮህን እንዳትረሳ የሚያስታውሱ ማስታወሻዎች አድርግ ። በጸሎት ስፍራህ ወይም በቢሮህ ጠረጴዛ ላይ የቀጠሮህን ወረቀት አስቀምጥ ። ሊያነቃህ የሚችል ደወል ሙላ ። ሴቶች በማስታወስ ጎበዝ ናቸውና አስታውሱኝ ብለህ ንገራቸው ። ቀጠሮ ማክበር የመንፈሳዊነትም የሥልጣኔም መለኪያ ነው ። ምናልባት ያ ሰው ቢያረፍድ ደግሞም ቢቀር ጊዜህን እንዳታባክን የምትሠራውን ሥራ ፣ የምታነበውን መጽሐፍ ይዘህ ውጣ ። ቀረ ብለህ አትቀየም ። ለሰውም አትናገር ። ምናልባት በአደጋ ተሰናክሎ ይሆናል ። ወደ ቀጠሮህ ስትሄድ ጸልይ ። ንግግር ከመጀመራችሁ በፊትም ከዳኅፀ ልሳንና ልቡና እንዲሰውርህ አምላክህን ለምን ። በይበልጥ ለመጨዋወት ቀጠሮ መያዝ መልካም ነው ። አንዳንድ ጉዳዮች በስልክም ሊያልቁ ይችላሉና ለሁሉም ነገር ቀጠሮ ይያዝልኝ አትበል ። ዶሮ በጋን እንዳይሆንብህ ።

ሰው እፈልግሃለሁ ሲልህም አትኩሮት ስጥ ። ምናልባት ላለመኖር እየወሰነ ይሆናል ። ያንተ ቀጠሮ የሰውን ዕድሜ ማስቀጠል ከቻለ ከዚህ በላይ የምትኖርበት ዓላማ የለም ። ዛሬ ቢሞት ለመቅበር ይመችሃል ፣ ተጨንቄአለሁ ሲልህ አይመቸኝም አትበለው ። ያለችው ቀን ይህች ብቻ ልትሆን ትችላለች ። ብቻ ቀጠሮ አክብር ። ክቡርነትህን ማሳያ ነው ። ወላጆችህ ቀጠሮ ይከብዳቸው ነበር ። ሌሊቱን ሙሉ ሳይተኙ ሲንቆራጠጡ ያድሩ ነበር ። የሰውን ዋጋ ስላወቁ ዕድሜ ተሰጣቸው ። ለሰው ክብር የሌለው ዘመኑ አጭር ነው ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ