የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት 3

2- በየዕለቱ አንብብ

አንድ ነገር ሳታውቅ የዋልህባትን ቀን እንደኖርህባት አትቍጠራት ። አንድ ነገር ሳታውቅ ፣ አንድ በጎ ነገር ሳትከውን ከዋልህ ቀኑን ኖርኩበት አትበል ። በዚህ ዓለም ላይ የሥጋ ድንግል ክብር አለው ። የእውቀት ድንግል ግን ክብር የለውም ። እውቀት እንዳይነካህ ተጠንቅቀህ የምትኖር ከሆነ ሞተህ የምትኖር ነህ ። ድንግል አእምሮ የያዘ ሰው የሚያሳዝን ፣ ጎስቋላ ነው ። ብዙ ሰው ማወቅ የማይፈልገው ተሳስተሃል መባልን ስለሚፈራ ነው ። እስከ ዛሬ እውቀት የመሰለው ነገር አሁን እውቀት አይደለም ቢባል የኖረበት ዘመን በዜሮ የተባዛ ይመስለዋል ። ይህችን ዓለም ለመሰናበት አንድ ደቂቃ ቢቀርህም ለመታረም ዝግጁ ሁን ። የሚጸናው የመጀመሪያው ሳይሆን የመጨረሻው ነው ። ታርሞ እንደ መሞት ያለ ክብር የለም ። ብዙ ሰዎች እንደ አዋቂ የሚያዩት ደፋር መሃይም ማወቅ አይፈልግም ። ምክንያቱም ሲያነብና ሲማር ያዩት እንደሆነ የሚንቁት ይመስለዋል ። የሚያሳፍረው በእጅ መጽሐፍ መያዝ ሳይሆን የስካር ብርጭቆ መጨበጥ ነው ። ለንስሐና ለእውቀት ጊዜ አለፈ አይባልም ።

እምነት ያለ እውቀት አለማመን ነው ። ፍቅር ያለ እውቀት ልማድ ነው ። ምግባር ያለ እውቀት የአጋጣሚ ጥረት ነው ። ትዕግሥት ያለ እውቀት እያረሩ መሳቅ ነው ። ተስፋ ያለ እውቀት የራሱ ጉዳይ ብሎ መሪውን መልቀቅ ነው ። ሀብት ያለ እውቀት ከልክ በላይ በታኝ ወይም ከልክ በላይ ስስታም የሚያደርግ ነው ። እውቀት ከተለያየ መንገድ ይገኛል ። የመጀመሪያው ከመጽሐፍ ነው ። ሁለተኛው ከአዋቂዎች ነው ። ሦስተኛው የዘመን ባለጠጋ ከሆኑ ሽማግሌዎች ነው ። አራተኛ ከድሆች ነው ። አነባበቡን ካወቅህበት ሰው ሁሉ መጽሐፍ ነው ይባላል ። ያለ እውቀት የሚደረግ ነገር ሁሉ በሰማይም በምድርም ዋጋ አያሰጥም ። በእውቀት የምናደርገው ነገር ደስታ አለው ። ያመነውን ያወቀ አያፍርም ። የሚወደውን ያወቀ ዋጋ መክፈል አይፈራም ። መጽሐፍ ቃሉን የማያጥፍ ወዳጅ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ብዙ መጻሕፍት ቢኖሩም ቅዱስ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍት ናቸው ። እነዚህ የሕግ ፣ የጸጋ ፣ የበረከት ፣ የሕይወት መገኛ ናቸው ። በየዘመናቱ የነበሩ አማኞችን ተመሳሳይ ቋንቋና ተመሳሳይ ሕይወት እንዲኖራቸው ያደረጉ ናቸው ። ብሉያትና ሐዲሳት ለእምነት ምስክር የሚጠሩ ናቸው ።

የዕለቱን ተግባር ከመጀመርህ በፊት በማለዳ ተነሥተህ አንብብ ። የምታነበውም መጽሐፍ ቅዱስን ፣ የተባረኩ እጆች የጻፉአቸውን መጻሕፍት ፣ የእግዚአብሔርን ትልቅነት እየተናገሩ የሚሰብኩህን ሊሆን ይገባዋል ። ደግሞም የታሪክ ፣ የምክር ፣ የመጽናት መጻሕፍትን አንብብ ። ቀኑን ኃይል ይዘህ ለመቀላቀል ያግዝሃል ። እውቀት ጋሻ ነውና የሚወረወረው ጦር አያገኝህም ። አእምሮ ማረፊያ ይፈልጋልና በማለዳ መስኩን ልትሰጠው ይገባሃል ። ደግሞም ሆድህ እንጀራን እንደ ጠየቀህ አእምሮም እውቀትን ይጠይቅሃል ። በማንበብህ ከመርሳት በሽታ ትድናለህ ። አእምሮ ካላነበብህበትና እውቀትን ካልቀሰምህበት እየዛገ ይመጣል ። እውቀትን በሚመለከት መገብየትና መቅሰም የሚሉ ቃላት ይደመጣሉ ። ገበያ ሁሉም ምርት አለው ። ገበያ የምንወጣው ግን የሚያስፈልገንን ለመግዛት እንጂ ገበያ ያለውን ሁሉ ይዞ ለመምጣት አይደለም ። ስናነብ የማነበው የቱን ነው ? በማለት መምረጥ ያስፈልጋል ። የጥንቆላ ፣ የሐተታ መናፍስት መጻሕፍትን በማንበብ አእምሮአቸውን ያጡ አሉ ። መቅሰም የሚለው ቃል ለእውቀት ይነገራል ። መቅሰም የንብ ተግባር ነው ። ንብ ከቆሻሻ ሳይሆን ከአበባ ትቀስማለች ። ከመልካም መጻሕፍት መቅሰም ይገባል ። ግን እንደ ንብ ታታሪ መሆን ግድ ይላል ።

የዓይን ብርሃን ፣ የማንበብ እውቀት ኖሮት የማያነብ ዓይናቸውን ያጡ ያዝኑበታል ። ያልተማሩ አባቶችና እናቶች ይረግሙታል ። መጻሕፍትን ለማየት የተፈጠረውን ዓይን ፊልም በማየት የሚፈጁት ንስሐ መግባት ያስፈልጋቸዋል ። መጽሐፍን ዋጋ ከፍሎ ማግኘት ፣ ደግሞም ማንበብ ይገባል ። መጽሐፍን ገዝቶ አለማንበብ ወዳጅን እቤት ጋብዞ እንደ ማኩረፍ ነው ። ከሕይወት ሥነ ሥርዓት አንዱ ማንበብ ነው ። እያነበብን ነው ። በማኅበራዊ ሚዲያ ቀኑን ሙሉ እናነባለን ። የምናነበው ግን ሐሜትን ነው ። የምናነበው የተቆራረጠ አሳብን ነው ።

ስናነብ ምን ይከሰታል ? አእምሮአችን ይበለጽጋል ። ሕይወትን የምናይበት መነጽር ይለወጣል። ምክንያታዊ እንሆናለን ። ከጭፍን እይታ እንድናለን ። የሰውን ዋጋ እናውቃለን ። የምንናገረው ቁምነገር እናገኛለን ። በአሳብ ላይ ተንተርሰን ከሰዎች ጋር እንወያያለን ። ካላነበብን የምንሆነው አሁን እየሆንን ያለነውን ነው ። እወቀትን የተራቡ አእምሮዎች አራዊት ይሆናሉ ።

መጽሐፍ ጓደኛ ነው ፣ አሳብን ይካፈላል ። መጽሐፍ ጓደኛ ነው ፣ ያዋራል ። መጽሐፍ ጓደኛ ነው ፣ ብቸኝነትን ይዋጋል ። አንብቡ ! አንብቡ ! አንብቡ ! ኧረ እባካችሁ አንብቡ !!!

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 11 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ