የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (35)

20. ያየኸውን ገመና አትናገር

“አዋላጅና አዋቂ ያየውን ሁሉ አይናገርም” ይባላል ። ሰውን ሰው ያሰኘው ገመና ያለው ፍጡር መሆኑ ነው ። በሙሉ ማንነቱ አውቆ የሚያፈቅረው እግዚአብሔር ብቻ ነው ። የሠሩትን የጭካኔ ተግባር የነገሩንን ፣ ያደረጉትን ኃጢአት ለእኛ ብቻ ያወሩትን ምናልባት ከዚያ ቀን ጀምሮ ጠልተናቸው ፣ ተጠራጥረናቸው ፣ እነርሱን ባየን ቍጥር ስህተታቸው እየታየን ይሆናል ። የሰዎችን ጉድለት ለማየት ሥልጠናና ሥልጣን ይፈልጋል ። በዚህ ምክንያት ካህን ተምሮ የሰውን ገመና ያያል ። የሥነ ልቡና አማካሪ ብዙ አጥንቶ የሰውን ውስጣዊ ትግል ከባለቤቱ አፍ ይሰማል ። ሐኪምም ተመራምሮ የሰውን ልብስ ገልጦ ያያል ። የሰዎችን ስህተት ከሌሎች ብንሰማ ካህን መሆን አንችልም ። ምክንያቱም ካህን ከራሱ ከባለቤቱ ሰምቶ መንገድ ያመለክታል ። የሥነ ልቡና አማካሪም ስለ እገሌ ከእገሊት ቢሰማ እውቀቱን መተርጎም አይችልም ። ሐኪምም መንገድ ላይ የተራቆተ ሰውን ቢያይ ሙያውን መጠቀም አይችልም ። ምሥጢር የባለቤቱ ሀብት ነው ። ያንን ምሥጢር በራሱ አንደበት ሲናገረው መፍትሔ ያገኛል ። ፖሊሶች ወንጀልንና ወንጀለኛን ያነፈንፋሉ ። ዓላማቸው ንጹሑንና አዳፋውን ለይቶ እርምጃ ለመውሰድ ነው ። ፖሊስ ምሽት ላይ ለአለቃው ዛሬ ሚስቱን ሲያስቀድም ያየሁት ባል ፣ ችግረኞችን ሲያጥብ ያየሁት ወጣት ብሎ ሪፖርት አያቀርብም ። ካህን ለምሕረት ፣ ሌላው ደግሞ ለፍርድ ይሰማል ።

አንድ ሰው ገመናውን ከነገረን ትልቅ ሹመት እየሰጠን ነው ። አንተ ካህኔ ፣ አማካሪዬ ፣ ሐኪሜ ነህ እያለን ነው ። እኛ ብንሆን ለዚያ ሰው ገመናችንን አንገልጥለትም ነበር ። ከምናከብረው በላይ ያ ሰው ያከብረናል ። ሰዎች ምሥጢራቸውን ከነገሩን በነገሩን ገመና ምክንያት አደጋ ቢደርስባቸው ልንደግፋቸው ይገባናል ። ቀድሞ መስማት ለመርዳት ባለ ዕዳ መሆን ነው ። በመከራ ቀን አጋዥ ለማግኘት ምሥጢርን ለሚገባው ሰው መንገር ይገባል ። አስቀድሞ በመስማቱ ከጀማው ጋር ሁኖ ይሰቀል አይለንም ። አይዞህ ብሎ ያበረታናል ። በዚህ ዘመን በሰው ገመና መነገድ የተለመደ ተግባር ሆኗል ። በዚህ የተካኑት ከዓለማውያን ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተቀመጡት ጨካኞች ናቸው ። ወንጌል ገባኝ ባዮች የዚህ አበሳ ተሸካሚዎች ናቸው ። እርስ በርሳቸው በምሥጢር ያወሩትን አደባባይ ያወሩታል ። አንዱ አንዱን ያጋልጣል ። እንኳን ኢየሱስ የመከራቸው ጨዋ ያሳደጋቸው አይመስሉም ። በገመናቸው እስረኛ በማድረግ ብዙዎችን ለሞት ያበቁ ሰዎች አሁንም አሉ ። እንዲህ ስታደርግ ቀርጸንሃል እያሉ ያንን ሰው መጫኛ አህያ ፣ መጓጓዣ ፈረስ በማድረግ ይሰብሩታል ። ያም ሰው መሸከም ሲከብደው ራሱን ያጠፋል ። በጣም ሞኝ ነው ።

ብዙ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች በገመናቸው እስረኛ የተደረጉ ሰዎች ናቸው ። በእውነት እንዲህ ያለውን ክፋት አንዳንድ ጊዜ ዓለማውያንም ላያደርጉት ይችላሉ ። አንድ አማኝ የወንድሙን ገመና በአደባባይ ካወጣ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ሊያድን መጣ የሚለውን ቃል በግልጥ ክዷል ። የሚያማክሩትን ሰው በመቅረፀ ድምፅ የሚቀርጹ ፣ ከዚያም የሚያስፈራሩ ወንጌላዊ ነን ባዮች እንዳሉ እናውቃለን ። አውቀንም ዝም ብለናል ። አንዳንድ ጉባዔዎች የገመናቸው እስረኞች የተሰባሰቡበት ነው ። እረኛ ነኝ ባዩ በምሕረት በትር ሳይሆን በገመናቸው አስሮ የራሱ አገልጋይ ያደርጋቸዋል ። በእውነት ከምንደኛ እረኛው በላይ በፍርሃት የተቀመጠው ሰው ያሳዝናል ። ራስን ነጻ ማውጣት ይገባል ። አልሠራኸው እንደሆነ ስምህ ቢጠፋ ክብርህ ነው ። በድለህ እንደሆነ ንስሐ የተዘጋጀው ላንተው ነው ። ራስህን በዚህች ጀምበር ነጻ አውጣ ። የአእምሮ የለሾች መጫወቻ ሆነህ አትኑር ። በባርነት ከመኖር በነጻነት መሞት ይሻላል ።

ፍርድ ቤት አካባቢ የማይጠፉ የሐሰት ምስክሮች አሉ ። እነዚህ ሰዎች “ክፈሉኝ ፣ አየሁ ሰማሁ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ” የሚሉ ናቸው ። በኢትዮጵያ ባሕል የተጠሉ የሚባሉ የመጀመሪያዎቹ የሐሰት ምስክሮች ናቸው ። ቀጥሎ የሰውን ገመና የሚያወጡ ነውረኞች ናቸው ። ካህን ምሥጢር ካወጣ መቃብር አፍ አወጣ ይባላል ። አዋቂና ሥልጣን ያለው ያየውን ሁሉ አያወራም ። ለራሱም ክብር አይመጥነውም ። መቃብር የያዘውን ሬሳ ሲሸት ፣ ሲፈርስ ፣ ሲበሰብስ አንድም ቀን አውርቶ አያውቅም ። የእግዚአብሔር ልጆችም እንደ መቃብር አበሳን የሚሸፍኑ ናቸው ። ከመቃብር አንሰን የማውቀውን ሁሉ ማውራት አለብኝ ማለት ተገቢ አይደለም ። ይህ ዘመን ትዳር አደባባይ የወጣበት ነው ። የልጁን እናት ፣ የልጇን አባት ገመና በአደባባይ ያወራሉ ። ሲፋቀሩ ያልነገሩንን ሲጣሉ ለምንድነው የሚነግሩን ? ብለን መጠየቅ አለብን ። ለአቅራቢዎቹ ወሬው እንጀራቸው ነው ። እኛ ግን ለትዳር ክብር ስንል ገመና በአደባባይ መውጣት የለበትም ብለን ጆሮን መንሣት ያስፈልገናል ። ይህ ምሥጢር የሚነገርበት ቦታ አለ ። አንድ ማኅበረሰብ የመፍረስ አደጋ ውስጥ ነው የሚባለው የቤት ችግር እየገነፈለ አደባባዩን ሲበክል ነው ። የመንገድ የቆሻሻ መፍሰሻዎች ሲፈነዱ እንሳቀቃለን ። ከዚያ በላይ የሰው ምሥጢር ሲባክን መሳቀቅ አለብን ።

አንተ ግን ያየኸውንና የሰማኸውን ገመና አትግለጥ ። ያንተም ተሸፍኖልህ እንደምትኖር እወቅ ። ስለ ሰው ፣ ሰው ቢናገር ውሸት ነው ። ስለ ሰው እግዚአብሔር ቢናገር ተገቢ ነው ። ብዙ የሚያየውና የሚያውቀው እግዚአብሔር ዝም ብሎ ጥቂት የምታውቀውና ያየኸው አንተ ለፍላፊ አትሁን ። አምኖ የነገረህ ምሥጢር ምናልባት ሚስቱ ፣ ልጆቹም የማያውቁት ሊሆን ይችላል ። ይህን ያህል ክብር ተጥሎብህ ወርደህ እንዳትገኝ ተጠንቀቅ ። በሰማኸው ምሥጢር ያ ሰው ተፈርዶበት ወኅኒ ቢወርድ ተግተህ ጠይቀው ። ጓደኝነት ልኩ አንዱ የአንዱን ምሥጢር መጠበቁ ነው ። ከሁሉ በላይ የእግዚአብሔር ሰው ለሰማው ገመና ይጸልያል ። ምናልባት ማንም ያላየውን ያየኸው የጸሎት ርእስህ እንዲሆን ነው ። ያ ሰው ገመናውን ገልጦልህ አንተ ብታወጣው የሰውዬው በደል ባንተ ላይ ይቆጠርና ሰውዬው ነጻ ይወጣል ። ሆድ ብዙ ቆሻሻ ተሸክሟል ፣ እንኳን የሰውን ገመና ። በሆድ የሚይዙት በአፍ አይነገርም ። በምንም መንገድ ሁለት ሆናችሁ ያደረጋችሁት ለሦስተኛ ሰው አይወራም ። ብታወራ የሚሰማህ ሰው ይፈራሃል ፣ ይጠነቀቅሃል ። ነግ ለእኔ ነው ይልሃል ። ይልቁንም መንግሥታዊ ምሥጢርን ሰማህ ማለት ሰይፍ ባንገትህ አስረህ እንደ መዞር ነው ። ምሥጢሩን ከጠበቅኸው ይጠብቅሃል ፣ አሊያ ያጠፋሃል ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ