የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (40)

24. የውሸት ኑሮ አቁም

የብዙ ሰው ሕይወት በውሸት የተሞላ ነው ። የውሸት ይስቃል ፣ የውሸት ያለቅሳል ። የውሸት ይፎክራል ፣ የውሸት ይዘምራል ። የውሸት እንባውን ያፈስሳል ፣ የውሸት እልል ያሰኛል ። ያደረግነውን ነገር ያደረግነው ከልባችን ነው ወይስ ለማስመሰል ነው  ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። ከሰው ጋር የመኖር ትልቅ ምሥጢር ከራስ ጋር መኖር መቻል ነው ። ከራሳችን ጋር የምንኖረው በእውነት ብቻ ነው ። ሥልጣናችን ፣ ሀብታችን ፣ ትዳራችን ፣ ዝናችን የእውነት ካልሆነ በውስጣችን ታላላቅ ፍንዳታዎች በየሰከንዱ ይሰማሉ ። ሰው ራሱን አስሮ የሚያሰቃይበት እስር ቤት ካለ ውሸት ነው ። ለባለጠጎች በማያስቀው እየሳቁ ፣ እርስዎ ልክ ነዎት እያሉ ዕድሜአቸውን የሚገፉ አያሌ ናቸው ። ፓትርያርክ ፣ ጳጳስ ሲያዩ መወድስ የሚደረድሩ ዞር ሲሉላቸው መውቀስ የሚያበዙ ቍጥር የላቸውም ። አስመሳይነት የዲያብሎስ የበኵር ልጅ መሆን ነው ። ነገ ላይ ከሰው ላለመለየት ፣ ነገ ላይ ጨረታ ላለማጣት ፣ ነገ ላይ የሀብታሞችን ጥላቻ ላለማትረፍ የማያምኑበትን መጠጥ የሚጠጡ ፣ ቤታቸውን ርቀው በደጅ የሚያድሩ ብዙ ናቸው ። ይህን የውሸት ኑሮ ትዳራቸውም አምኖላቸዋል ። ከባለጠጋ ጋር ሲያመሹ ትዳሩም እሰየው ይላል ፣ ከድሀ ጋር ሲያመሹ ቤቱን አያከብርም ተብሎ ሽማግሌ ይጠራል ። ልጆቻቸውን ሳይቀር ለጥጋበኞች ጨረታ የሚያቀርቡ ወላጆች ባለፉት ሠላሳ ዓመታት አትርፈናል ።

ባለጠጎች ድሀን የፈጠሩት ይመስላቸዋል ። በምድር ላይ ባለጠጎችና ነገሥታት ትዳር ሲፈጽሙ ድሀ መጨነቅ ይጀምራል ። ገንዘብ ሐሰተኛ ወዳጅና እውነተኛ ጠላት የሚገዛ ነው ። በአገራችን ልቅሶ ብድር ነው ። እንባውን ለእኛ ልቅሶ ላፈሰሰ የእርሱም ሲሞትበት ሄደን እናለቅሳለን ። ሰውዬው ስለ ሞተ ሄደን አንቀብርም ፣ ተመልካች ዘመድ ካለ ግን እስከ ዐርባው አንለይም ። ልቅሶ በፖሊስ የምናለቅስበት አገር ይመስላል ። ጾማችን እንኳ በጾም ትራፊኮች ቁጥጥር ካልሆነ ላንጾመው እንችላለን ። በደርግ ዘመን ሽፍንፍን የሚባል ምግብ መጥቶ ነበር ። ጥብሱ ሥጋ አንድ እንጀራ ሙሉ ይለብሳል ። ከላይ ሲታይ የጾም ነው ፣ በቀዳዳው እጁን እየላከ የሚበላው ግን ሥጋ ነው ። በሁዳዴ ሽፍንፍን ተጀመረ ። የጾም ዋጋ ከፋይ እግዚአብሔር ነው ። ጾም በሁለት ነገር ይረክሳል ። የመጀመሪው የሌላውን አለመጾም ሲያሳየን ሲሆን ሁለተኛው የተውነውን ምግብ ለድሀ ባለመስጠታችን ነው ። ጸሎት ያለ ምጽዋት አይሆንም ። ምክንያቱም የእኔ ጸሎት እንዲሰማ የድሀን ጩኸት መስማት አለብኝና ። ጾምም ኢኮኖሚ ሳይሆን የተውነውን ምግብ በምጽዋት ለድሆች መስጠት ነው ።

ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ የሚፎክረው ደፍሮ ሳይሆን ፈርቶ ሊሆን ይችላል ። አቅሙን የሚያውቅ ውሻ አይጮህም ። አድብቶ ይይዛል ። ፉከራ ባለበት ፍርሃት ይነግሣል ። ደጅ ላይ በጣም ሽቁጥቁጥ የሆኑ ሰዎች ገና የቤታቸውን በር ሲያንኳኩ ቤተሰቡ መሯሯጥ ይጀምራል ። የደጅ ፈሪ የቤት ጀግና ነው ። ሰካራሙ ጭላጭ እየተደፋበትና እየተሰደበ ጠጥቶ እቤቱ ሲገባ አምባገነን ሁኖ እንቅልፍ ይነሣል ። የውሸት የሚፎክር ብዙ ነው ። ፉከራ ጸሎትን ያስረሳልና እንደ ጴጥሮስ ለክህደት ይዳርጋል ። እግዚአብሔር ከረዳኝ ያንን ወይም ይህንን አደርጋለሁ ማለት ይሻላል እንጂ ፉከራ ከንቱ ነው ። በኃይለ እግዚአብሔር ስንል መላእክት ይዋጉልናል ፣ በእኔ ጉልበት ስንል አጋንንት ይዋጉናል ። የውሸት የሚዘምር ብዙ ነው ። እንደ ሰማነው ስዘምር አለቅስ የነበረው አስለቃሽ ቅባት ተቀብቼ ነበር እየተባለ ነው ። እግዚአብሔር የደበቀላቸውን ነውር መደበቅ ያልቻሉ ብዙ ናቸው ። ግልጽነቱ መጠን ከሌለው እብደት ነው ። “እብድና ብርድ በግድ ያስቅ” ይባላል ። ብርድም እትትት.. ሲያሰኝ ፈገግታ አለው ። እብድም ፣ የጠባይ ነሆለልም በግድ ያስቃል ። አምልኮተ እግዚአብሔር ለብዙዎች ተውኔት ነው ። ምስኪኑን ሕዝብ የሚያስለቅሱበት እነርሱ ግን የሚስቁበት ነው ። በዓለም ያልጨረሰውን ጭፈራ በኢየሱስ ስም ለመጨረስ የተሰለፈው ቍጥር የለውም ። እንደዚህ ካለ ዓለማዊ ዝማሬ መሳይ ጋር መተባበር ስህተት ነው ።

አንዳንድ ተናጋሪ ሰዎች እንባቸውን ፈሰስ ሲያደርጉት ብዙ ሕዝብ ይከተላቸዋል ። እንባቸው የንግድ ፈቃዳቸው ነው ። አንደኛው በኢየሱስ ስም ፣ ሌላኛው በእመቤታችን ስም ሲያታልል ቀኑ ይመሻል ። አንድ ወጣት አንድ ሰው እያሳየኝ ያ ተናጋሪ የሚያለቅስበትን ደቂቃ አውቆታልና አሁን ሊያለቅስ ነው አለኝና ተናጋሪ ወዲያው አለቀሰ ። የሚያለቅሱበት ደቂቃ እንኳ የተለካ ሰዎች አሉ ። እንባ ግድ ካልሆነ በአደባባይ ባይደረግ መልካም ነው ። እነዚህ ሰዎች በድብቅ ያልቅሱ እንዳይባል በድብቅ አይጸልዩም ፣ አያለቅሱም ፤ ላይሰንሳቸውን ለማደስ በአደባባይ ያለቅሳሉ ። አማኝን ሳይሆን ገጸ ባሕርይ የተላበሱ ምእመናንን ያተረፍነው በዚህ ይመስላል ።

ብዙ ሰዎች በጌታ ሰላም አለኝ ፣ ደስተኛ ነኝ እያሉ ሲለፈልፉ ይውላሉ ። እውነቱ ግን እነዚህ ሰዎች ሰላምም ደስታም የላቸውም ። የያዙት ነገር አይወራም ። ራሱ ይናገራል እንጂ ። አዎ እንደ ተባለው፡- “የውሸት ኖረን የእውነት እንሞታለን ።”

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ