የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (41)

የውሸት ኑሮ አቁም – ክፍል 2

ብዙ ኑሮአችን በውሸት የተሞላ ነው ። ውሸት ከእውነት በላይ ዋጋ ያስከፍላል ። “እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር” እንዲሉ እውነት ለጊዜው መራራ ቆይቶ ጣፋጭ ናት ። ውሸት ለጊዜው የሚጣፍጥ እስከ መጨረሻው ግን የሚመርር ነው ። ስንዋሽ ያንን ግለሰብና ያንን ተቋም በእውቀት በለጥኩት የሚል ስሜት ያሳድርብናል ። ቆይቶ ግን ነገሮችን ጨለማ ያደርግብናል ። የውሸት ጋብቻዎች ብዙ ዋጋ ያስከፍላሉ ። ከአገር ለመውጣት የሚገባባቸው የውሸት ጋብቻዎች ብዙ መቀያየም ያመጣሉ ፣ የጋብቻንም ክብር ይጥላሉ ። የመጣው ውጤትና የተከፈለው ዋጋ አልመጣጠን እያለ ደስታን ይነሣል ። ለዚህ ነው ወይ ይህን ሁሉ ዋጋ የከፈልኩት  ያሰኛል ። የትም ቢሄዱ ሰማይና አፈር አንድ ነው ። ይኸው ሰማይ ፣ ይኸው አፈር ነው ያለው ። ሁሉም ቤት የራሱ የሆነ ልቅሶ አለው ። እዚህ የእንጀራ ጥያቄ እዚያ ያለመርካት ጥማት አለ ። ድሀ ቸገረኝ ይላል ፣ ሀብታም ጨነቀኝ ይላል ። ችግር በዕለት ጉርስ ጸጥ ይላል ። የጨነቀው ግን አገር ካገር ቢንከራተት ፣ ቤቱን ትቶ ጭፈራ ቤት ቢያድር አይታገሥለትም ። ቸገረኝ ከሚል ጨነቀኝ የሚል ያሳዝናል ። የቸገረውን ድሀ ሁሉ ያዝንለታል ፣ የጨነቀውን ባለጠጋ ግን የሚያዝንለት የለም ። በትልልቅ ቤት ትልልቅ ጥያቄ አለ ። በትልልቅ ቤት ትልቅ ጉድ አለ ።

ውሸት በልምምድ እንኳ ትክክለኛውን መልክ መምሰል ይሳናታል ። ረጅም ጊዜ መተወን አይቻልም ። ለአንድ ሰዓት ተውኔት አንድ ዓመት ተለማምደው ያውም አይሳካላቸውም ። እውነት ወጪዋ ትንሽ ነው ። የሐሰት በጀት ግን ብዙ ነው ። ሰው ከውሸት አገኘዋለው የሚለውን ለእውነት ቢኖር ያገኘው ነበር ። እውነትን በእንቅልፍ ልባችንም ልንናገረው የምንችለው ነው ። ውሸት ስንናገር የልባችን ትርታ ይጨምራል ። ስጋታችን ከፍተኛ ይሆናል ። በቆራጥነትና በመታገል የምንደርስበትን ስኬት በውሸት ማግኘት አስፈላጊ አይደለም ። ዛሬ ዓለምን በአእምሮ ቅኝ የሚገዙት በኳስና በፊልም አብዮት ነው ። የኳሱ ደጋፊ ሁልጊዜ ተዝናንቶ የሚኖር አይደለም ፣ በሰለጠነው ዓለም ያለው ደጋፊ ጭንቀቱን የሚያስተነፍስበት ስፍራ ነው ። ፊልሙ ሐሰተኛና ብዙ ወጣቶችን የሚያሳስት ነው ፣ የሆሊውድ አባላት በዓለም ላይ በጭንቀት በመማቀቅ ቀዳሚ ናቸው። በፊልም እንደ ሠሩት ዝሙት ያንን ያህል ረጅም ደስታ የለውም ። የፊልሙን ቅንብር በእውነተኛው ኑሮ ውስጥ ፈልገው ያጡ ወጣቶች ለጭንቀት ይዳረጋሉ ። እንደ ሌሎች ለመልበስ ፀጉርን ለመቆረጥ መሞከር ራስን የማጥፋት ወንጀል ነው ። የምንኖረው የራሳችንን ኑሮ ሊሆን ይገባዋል ። የውሸት ቤት ሳይፈርስ አይቀርም ።

ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር የራሳቸው ባልሆነ ነገር የሚብለጨለጩ አሉ ። ለዚህ ከፍተኛ ወጪ ያወጣሉ ። አገራት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያወጡት ለመዋቢያ ነገሮችም ነው ። ተፈጥሮአቸውን ሳይጠቀሙ የሌሎችን የጌጥ ገበያ የሚያደምቁ ወጣቶች ያሳዝናሉ ። ፀጉር እያላቸው ፀጉር ይገዛሉ ። የልጅነት አፍላ መልክ እያለ ሜካፕ ይሸምታሉ ። የጌጣጌጥ ትልቁ ችግር ያንን ጌጥ ካላደረጉና ያንን ሽቱ ካልተቀቡ የመቆም ድፍረት የሚያሳጣ ነው ። ሰው ሠራሽ ነገር ሁሉ የራሱ ችግር አለው ። እነ ማይክል ጃክሰን ቆንጆ ጥቁር ነበሩ ፣ መልካቸውን ወደ ነጭ ሲቀይሩ የመኖር አቅምና ዕድሜ አላገኙም ። ራስን መሆን ውሸትን ድል መንሣት ነው ። እንደ እነ እገሌ ማውራት የሚፈልጉ ሰዎች ከላይም ከታችም ብዙ ናቸው ። በርግጥ የማረኩን ሰዎች በውስጣችን ይገዙናል ። የሌሎችን ስንይዝ የራሳችንን ጥለን መሆን የለበትም ።

ሰርግ መልካም ነው ። አዳምና ሔዋን ግን እንደ ተጋቡ እንጂ እንደ ተሰረጉ ብዙ አናውቅም ። እግዚአብሔር ያቀደላቸው ለሰርግ ሳይሆን ለጋብቻ ነው ። በእውነት ባንተ ሰርግ ከልቡ የሚደሰት ሃያ ሰው ካገኘህ በጣም ሀብታም ነህ ። ታዲያ ሺህ ሰው መጋበዝ አስፈላጊህ አይደለም ። አንዳንዱ ከሥራው ውጥረት የተነሣ ሰርግህ ላይ የመጣው እንዳትቀየመው ነው ። ከዚህ ሁሉ በላይ የኪራይ ቤት ልትገባ የሚሊየን ብር ሰርግ መሰረግ ይህ የውሸት ኑሮህ ውጤት ነው ። ሰርግህን የንጉሥ አድርገህ የችግረኛ ኑሮ ከመኖር ፣ ሰርግህን ቀልጠፍ አድርገህ የሰርግ ያህል መኖር የተሻለ ነው ። በልቶ ለማያመሰግንና አቃቂር ለሚያወጣ ሰው ብዙ መድከም አስፈላጊ አይደለም ። ዝክር ቢሆን በረከት ታገኝበታለህ ፣ እግዚአብሔርም ዋጋ ይከፍልሃል ። አጉል ወጪህ ግን አንተኑ አራቁቶ ይቀራል ።

ቤትህን እያስራብህ በደጅ ብዙ ገንዘብ ለጥጋበኛ ትበትናለህ ። ይህ የውሸት ኑሮ ነው ። በደጅ የጋበዝካቸው የወደቀውን ቤትህን ሲያዩ ለእኛ ብሎ ነው አይሉህም ፣ ይልቁንም ይታዘቡሃል ። ስትታመም የምትጠራው ያችው ሚስትህ ናት ። የጋበዝካቸው ቀብርህ ላይ እንኳ ላይገኙ ይችላሉ ። የጉራ ኑሮህን ተጸየፈው ። ከልብህ ሳትወዳቸው እነ እገሌን እንደ ወደድህ አድርገህ አታስመስል ። መውደድ በራሱ መፍቀድ የሚል ትርጉም ያለው ነው ። መቼም መሣሪያ ተደግኖበት የሚወድድ ማንም የለም ። ዛሬ ንግግራችን ራሱ ግራ የገባው ነው ። እወድሃለሁ ግን ላፈቅርህ አልቻልኩምና ተለያይተናል የሚሉ ሰዎችን እንሰማለን ። መውደድና ማፍቀር የአማርኛና የግእዝ ጉዳይ ካልሆነ ሁለቱም ተመሳሳይ ነው ። አዎ ከእውነቱ ስሜቱን የሚያምን ትውልድ ለውሸት ኑሮ ተላልፎ ይሰጣል ። በትክክልም ሰውን ላንወድ እንችላለን ። የምንወደው ስሜታችንን ነው ። ያንን ስሜታችንን ያጋጋለ ሰው እርሱን ካልያዝሁ እንላለን ። ከአቅም በላይ ልጆችህን አታሳድግ ። ያጣህ ቀን ጠላት ይሆኑሃል ። በልክ መኖር ከጭንቀት ያድናል ። ከመሬት ብዙም ያልራቁ ለመውደቅ አይሰጉም ። ትንሽ ስታገኝ ሀብታም ሰፈር ለመከራየት አትቸኩል ፣ ማግኘትህን በትክክል አረጋግጥ ።

ከሌሎች ጋር ቁመት እየተለካካህ አትኑር ። ሽንገላን ተጸየፈው ። የዝሙት አዳሪዎች እንጂ ጨዋ ሰዎች ሸንጋይ አይደሉም ። ልጅህን በአቅምህ አሳድገው ። የልኩን እንጂ የትላንት አስተዳደግህን ለመካስ ብለህ ከመጠን በላይ አትመግበው ። የማትኖረውን ኑሮ በፎቶ ላይ እያስዋብህ አትልቀቅ ። ዘመኑ ያልኖረ መልክ እየሰጠህ ያታልልሃል ። ማድያቱም ፣ ጥቁረቱም የመኖርህ ትርፍ ነውና ውደደው ። በዚህ ዓለም ላይ እንኳን ሰው ድንጋይም ይጠቁራል ፣ ድንጋይም ይከሳል ። ውሸት ፕራንክ ተብሎ በመጣበትና በሚያዝናናው ዘመን ስለ ውሸት መጻፍ በራሱ ተጠዪ ያደርጋል ። የሰውን ሥራ እየሰረቁ አዋቂ ፣ ደራሲ የሚባሉ ባሉበት ዘመን ውሸት ኃጢአት ነው ማለት ብዙ ጠላት የሚያስነሣ ነው ። ፖለቲካው ከጅማሬ እስከ ፍጻሜ ውሸትን ጌጥ ባደረገበት ዘመን ለእውነት መኖር ባንዳ የሚያሰኝ ነው ። ቢሆንም ለእውነት ኑር ። ሞት አይቀርምና ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ