የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት (42)

26. ሁኔታዎችን ተቀበል

በፕሮግራም መኖር ጥሩ ነው ። የሰውነትም ልክ ነው ። ዓለም ግን ከፕሮግራም ውጭ የምትሆንበት ጊዜ ብዙ ነው ። መጠንቀቅ መልካም ነው ። እጅግ መጠንቀቅም ቀድሞ የሚገድል ነው ። አንዱን ሞት በየቀኑ እያዩት ፣ ፍርሃት ንጉሥ ሆኖባቸው የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው ። ብርሃንና ጨለማ የዕለቱ መቍጠሪያ እንደሆኑ ሁሉ ተራራና ሸለቆ የሕይወት መገለጫ ነው ። ተለዋዋጭና ተነዋዋጭ በሆነው ዓለም ላይ ሁሉም ነገር በአድራሻው አይገኝም ። የትላንት መንገዶች ዛሬ ዝግ ናቸው ፣ ደማቅ መንደሮች ዛሬ ሰው አልባ ሆነዋል ። ታሪክ የትላንቱን የምናይበት መስተዋት ነው ፤ ታሪክ ሁሉም ነገር አላፊ መሆኑን የሚነግረን ነው ፤ ታሪክ እኛም አንድ ቀን የታሪክ ግብዓት እንደምንሆን የሚያስረዳን ነው ። ሁላችንም በታሪክ ፊት ነንና ። እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን በማለት በሕይወት ውስጥ ደስተኛ መሆን አይቻልም ፣ የፈለግነውን ብቻ ሳይሆን የተፈቀደልንን ለመቀበል መዘጋጀት ያስፈልጋል ። የወደድነውን አጥተን የጠላነው ሲመጣ የጠላነውን እያፈቀርን መኖራችን የተለመደ ነው ። እኛ የምንኖረውን ኑሮ ሌሎችም እየኖሩት ነውና ብቸኛ ተጠቂዎች ነን ብለን ማሰብ የለብንም ፣ ደግሞም ከሌሎች አንበልጥም ፤ ሁሉም አጥቷል ፣ ሁሉም ቀብሯል ። ከብዙ በጥቂቱ የፈለግነው ሆኗል ፣ አብዛኛው ግን ደስ አላሰኘንም ። ምርጫችን እንደ ውድማው እህል ገለባውም እንክርዳዱም ያለበት ነው ። ነገሮችን እንዳሉ ይኑሩልኝ ብሎ መመኘት ዓለም ለእኔ ፍላጎት ተፈጥራለች ብሎ ማሰብ ነው ። ለምን ተነካሁ ማለትም አይቻልም ፣ መገፍተርም አለና ። ባሕር የሰጠመውን ፈርዖንን ፣ ሣር የጋጠውን ናቡከደነፆርን ስናስብ የመሰላሉ ርዝመት ላለመውደቅ ዋስትና አይደለም ። እንደውም ከፍ ባልን ቍጥር የመውደቂያው ገደል ይርዝማል ።

ራሳችንን በማንጠብቀው ቦታ የምናገኝበት ጊዜ ጥቂት አይደለም ። ንስሐ ፣ ትንሣኤ ፣ ተስፋ የሚሉ ቃላት የመጡት መውደቅ ፣ መሞት ፣ በጨለማ መቀመጥ ስላለ ነው ። ተስፋ ዛሬ የኔ አይደለችም ብሎ ለሚያስበው ከፊት ለፊቱ የተቀመጠ መና ነው ። በሬው ረጅም ጉዞ እንዲጓዝ ጨው ያልሱታል ። ባለ ጨዉ ያለው ከፊት ነው ። ተስፋም እንደ በሬ ወደ ቄራ ሳይሆን ወደ ክብር የምንደርስበት ፊታውራሪ ነው ። በሕይወት ውስጥ ሁሉም ነገር በአቅማችን የተለካ አይደለም ። ዕቁብ የምንገባው ለዚህ ነው ። ሁልጊዜም መኖር የለምና ዕድር እንገባለን ። የማይቀሩ ሁነቶች አሉ ። ለዚያ መዘጋጀት ልብን ከመሰበር ይጠብቃል ። ሁልጊዜ ጤንነት ፣ ሁልጊዜ ሰጪነት ፣ ሁልጊዜ የበላይነት አይኖርም ። ሲረታ የማያውቅ መከራውን የሚጨምር ነው ። ትላንት የሰጠናቸው ድሆች ዛሬ ሀብታም ሊሆኑ ይችላሉ ። የትላንት ሎሌዎች ዛሬ አስተዳዳሪዎች ይሆናሉ ። ዓለም ሸለቆ ናት ፣ አንዱ ሲወጣባት ፣ አንዱ ይገባባታል ። ስንወጣ የሚወርደውን መገፍተር ፣ ስንወርድ የሚወጣውን መክሰስ ጥቅም የለውም ። ሁሉም ነገር በውክልና የያዝነው እንጂ የእኛ ንብረት አይደለም ።

ባርኔጣዎች ሲሸጡ ስታይ አንድ ቀን መላጣ ትሆናለህ ብለው እየጠበቁህ ነው ። ከዘራዎችም አንድ ቀን እነዚህ እግሮችህ ሲደክሙ ወደ እኛ ና ይሉሃል ። መድኃኒት ቤቶችም የዛሬው ጤነኛ የነገ ታማሚ ነህ ይሉሃል ። ይህን ሕይወትህን ጣዕም ያለው ለማድረግ በቅዱስ ፍርሃት ተመላለስ ። ማንኛውንም ነገር በእኔ አንቀጽ አትናገር ። ገንዘቤ ፣ ቤቴ አትበል ። ጤና ስታጣም ጤናዬን ስጠኝ አትበል ። ያንተ ቢሆን ኖሮ መብትህ ነው ፣ መብት ይጠየቃል እንጂ አይለመንም ነበር ። ጤና የእግዚአብሔር ነውና ጤናህን ስጠኝ በለው ። ብቻ ሁኔታዎችን ተቀበል ። እንደ ባለ አእምሮ ተዘጋጅ ። የሚያስፈልግህን ነገር አስቀምጥ ። የሰበሰብከውን ለመብላት ግን እግዚአብሔር መፍቀድ አለበት ። ቀኑ ካንተ ይልቅ የእግዚአብሔር ሎሌ ነው ። የሁልጊዜም አሸናፊ አይደለህም ፣ የትላንቱ ሕፃን ልጅ አድጎ ሊጥልህ ይችላል ። በትላንት ወኔህ ዛሬ አትጋጠም ። ጊዜን ለባለ ዕድሉ ተውለት ። ጡንቻህን ለማሳየትም የተወጠረ ልብስ አትልበስ ፣ ልታይ ያለ ገላ ደብቁኝ ይላልና ። ራስህን በመሸጥ ፣ ፎቶ በመነስነስ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ በመሥራት ለመኖር አስብ ። እየታዩ የሚኖሩ በፓርክ ውስጥ ያሉ ብርቅዬ እንስሳት ብቻ ናቸው ። አንተ ሰው እንጂ የዱር እንስሳ አይደለህምና ለመታየት አትኑር ። የሚሆነው አይታወቅምና ኑዛዜህን ጥርት አድርገህ አስቀምጥ ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ