የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት ( 44 )

27- አዎንታዊ ሥነ ሥርዓት ይኑርህ !

ሥነ ሥርዓት የተዋበ አደረጃጀት፣ አቀማመጥ፣ አመላለስ፣ አገላለጥ፣ አስተያየት ማለት ነው። ያልተዋቡ ሥርዓቶች አሉ። ብዙኃኑ ስለ ተቀበላቸው ውሸት ሳሉ እውነት፣ ነውር ሳሉ ክብር የተባሉ አያሌ ልማዶች አሉ። እነዚህ ቃለ እግዚአብሔርን የሚያሳብሉ፣ ሐዲሱን ኪዳን የሚያናንቁ ፣ የሰውን ልጅና  የፆታን እኩልነት የማይቀበሉ ናቸው። ሥርዓት መነሻው ልምድ፣ ሥልጠና፣ ሃይማኖት፣ ድንጋጌ ሊሆን ይችላል። ሥርዓት ራስንና ማኅበረሰብን ለመገንባት እጅግ ወሳኝ ነው። ይህ ዓለም ሲፈጠር፣ የሰውነታችን አካላት ሲዋቀሩ ፣ የሚቀድመውና የሚከተለው በጊዜው ሲመጣ ይህ ሁሉ ሥርዓት ነ ው::  ሥርዓት ምሥጢር ተብሎም ይጠራል። ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ብለን ልንጠራ እንችላለን። ምሥጢራት ያለ ሥርዓት አይፈጸሙም፤ ሥርዓትም ያለ ምሥጢር የሰው ልማድ ብቻ ይሆናል ። ሥርዓት ከአምላክ የምንቀበለው የሃይማኖት ጌጥ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ሥርዓት ተብሎ ይጠራል። ሥርዓት ካህንን ካህን ፣ ወታደርን ወታደር የሚያደርግ ነ ው። ያለ ሥርዓት የሚሄዱ  ነገሮች ሁሉ  ዕድሜ የላቸውም። ሥርዓት ሲታሰብ ነጠላ ስለ መልበስ ፣ ጫማ ስለ ማውለቅ ብቻ እናስባለን። ሥርዓት ግን ዲሲፕሊን የሕይወት መመሪያ ነው ። የምንገዛለት አቋምም ነው።

“ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።” (1ቆሮ. 14፥ 40)። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የጸጋ ችግር የላትም። ጸጋው ግን ሥርዓት በማጣት የውስጥ ግጭት፣ የውጭ ትዝብት  ፈጥሯል። ሥርዓት አገባብ ነው።  አገባብ በርን ለማስከፈት በጨዋነት ማንኳኳት ነው። ተገቢ የሆነ ፣ ሊደረግ የሚገባው ነገር ሳይቀር መደረግ  አለበት ።  ሥርዓት ከሌለ ግን ሀብተ ሥጋን ሀብተ መንፈስ ቅዱስን በአግባቡ መጠቀም አይቻልም። ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት የሌላውን ጸጋ ማክበር መቻል ሥርዓት ነው። ያ ሰው የሰውን ክብር አልፈልግም ቢል፣ መገፋቱንም በጸጋ ቢቀበል ሥርዓት ግን ተገቢ የሆነው ነገር እንዲደረግ ግድ ትላለች። የምናከብረው ክቡር ስለሆንን ነው። ጸጋ ያለ ሥርዓት ይባክናል። ለቤተ ክርስቲያን የትችት ናዳ  ያመጣባታል። ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን ስትደነግግ ብሉያትና ሓዲሳትን ፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክንና የጉባዔያት ቀኖናዎችን እንዲሁም ትውፊቶችን አጣቅሳ ነው ። ሥርዓቱ ምንም የዶግማን ያህል ባይቆጠርም እንደ ዶግማ ግን ሊከበር ይገባዋል። ቤተ ክርስቲያን ሺህ ዓመታት በጉልበት እንድትጓዝ ያደረጋት ሥርዓት ነው ። ሥርዓት በሲኖዶስ እየታየ የመሻሻል ዕድል አለው። ሥርዓት ግን በለዘብተኞችና በቍሳውያን ወገኖች እያለ ጥርስ እንደሌለው አንበሳ ሊኖር ይችላል።

ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ልምድ ተነሥተን ሥርዓት ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን መተንተን እንችላለን።

1- የሚበልጠውን ማስቀደም ነው ። ሙት ከማንሣት ይልቅ ወንድምን መውደድ የሚበልጥና  የሚቀድም ተግባር ነው። ሥርዓት የሚቀድመውን ያውቃል። የሚቀድመው ሲቀድም ለሚከተለው ቦታ ይኖረዋል። ሥርዓት የትላንቱን ማክበር ነ ው::  ትላንት ባይኖር ዛሬ አይኖርም ነበር።

2- ሥርዓት የምናደርገውን ማወቅ ነው። ለምናደርገው ነገር በቂ እውቀትና ትርጉም ያስፈልገናል። እግዚአብሔር እንደ አብሾ አሳብዶ፣ እንደ መጠጥ አስክሮ ማንንም አይመራም። አእምሮአችንን መጠቀም አለብን። ከሕልምና ከራእይ በፊት የተሰጠን ትልቅ ጸጋ አእምሮ ነው። ሌሎች ስላደረጉት  ሳይሆን ለምን እንደምናደርገው በቂ እውቀት ያስፈልገናል። መጽሐፍ እውቀት ማጣትንና እውቀት መጥላትን ሁለቱንም ይወቅሳል። እውቀት ያጡ መሃይምናን አሉ፣ እውቀት የጠሉ ትዕቢተኛ አገልጋዮች አሉ። “ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል ፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፤”ይላል  (ሆሴ 4፥6 )።

3- ወረተኛነት ሥርዓት ማጣት ነው። ወረተኛ ሰው ሳይጀምር የሚጨርስ ነው። ሁሉን የሚያውቅ ምንም አያውቅም። ሁሉን የሚወዳጅ ምንም ወዳጅ አይኖረውም። ሁሉን ሥራ የሚሠራ ምንም ውጤት አይኖረውም። ተአምር ፈላጊነት ወረተኛ ያደርጋል። ወረቱ ደግሞ ከእግዚአብሔር ወደ ሰይጣን ሽግግር ያደርጋል። የቀደመ የሚወስዳቸው ፣ በዋሉበት ፈስሰው የሚቀሩ፣  የግጥምጥሞሽ ሕይወት የሚኖሩ ሥርዓት የላቸውም። የእኔ ስም ሰይፈ ገብርኤል ነው፣ የእርስዋ  ወለተ ገብርኤል ነው ፣ የተገናኘነው ቁልቢ ነው መጋባት አለብን ቢሉ ይህ ሥርዓት ማጣት ነ ው።  ሁሉን ነገር ማመናፈስ የሚወዱ አሉ። መንፈሳዊና ማመናፈስ ልዩነት ኣለው። የመኪና ጎማ ሲተነፍስም ጠላት እየተዋጋኝ ነው ብሎ ማሰብ ማመናፈስ ነው። አትሳቁ ፣ አትጫወቱ፣ የሚጣፍጥ ምግብ አትብሉ ፣ ጥሩ ሽታ አትውደዱ የሚሉ የሚያመናፍሱ ብዙ አሉ። አይዘልቁበትም ። ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰይጣን ትልቅ ሆኖ ይታያቸዋል።

4. ሁሉም ሰው የሚናገርበት መገዛት የሌለበት ስብስብ ሥርዓት የለሽ ነው። ሥርዓት በሌለበት ጫጫታ ፣ የውድድር ስሜት፣ ዳኛም አባወራም የሌለው ጉዞ ይከሰታል። በመጨረሻም በድብድብ ያልቃል። ሁሉም ጸጋ አለው። ሁሉም ዓይነት ጸጋ ያለው ግን ማንም የለም። ብናውቅም ከእውቀት ከፍለን ነው፣ ጸጋ ብንቀበልም በምድር እንጂ በሰማይ የማይቀጥል ነው ። ልሳን ፣ ድውይ መፈወስ በሰማይ አያስፈልግም። አንዱ የአንዱን ጸጋ ማክበር አለበት። አሊያ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ ይደናቀፋል። ባለዜማው ሊቁን  “የጋን ውስጥ መብራት” ቢል፣ ሊቁ ባለ ዜማውን “ድምፅና ቁንጫ ባዶ ቤት ይወዳል” ቢል ጸጋ እግዚአብሔር ይባክናል።

5- መሪን ማክበር ሥርዓት ነው ። የቤት መሪ አባወራው ነው። ሾፌሩ መሪውን ስለ ያዘ የበታችነት አይሰማንም። አባወራ ቤቱን ስለ መራ ሴትነት ተዋረደ ማለት አይደለም። የክህነት ሥልጣንም ለሁሉም ወንዶች አልተሰጠም። ሴቶች ለምን ተገለልን ማለት አይገባቸውም። መሥራቹ እግዚአብሔር በቤቱ የሚሾመውን እርሱ ያውቃል። በቤትም፣ በማኅበርም መሪ ያስፈልጋል:: ሁሉም መሪ ከሆነ መኪናው ይገለበጣል። ሁሉም ሰው ተንታኝ መሆን የለበትም። ተናግረን ከማሰብ ፣ አስበን መናገር የተሻለ ነው። ሁሉም ሰው ወደ ሚዲያ መውጣት የለበትም። ሚዲያን መቋቋም የሚችሉ ጥቂት ሰዎች ናቸው ። ጆሮ ተደፍኖ አፍ የተከፈተበት ዘመን ያስፈራል።

6- የግብር ይውጣ ሥራ አለመሥራት ሥርዓት ነው። ሰዎች ሥራውን አላቆሙም፣ ከዚህ በፊት የሚያደርጉትን እያደረጉ ነው። ነገር ግን በፍቅርና በክብር ካልሆነ ለራሳቸውም ለሌላውም ደስታ አይሰጥም። ሥርዓት ሥራን መውደድ ነው። አድርጉ ግን በፍቅር ከውኑ። ተናገሩ ግን በሥርዓት ተናገሩ። የማይሠሩ፣ የማይነገሩ ፣  የሚተው ነገሮች አሉ። ሕይወት በሜዳ ላይ ሳይሆን በገመድ ላይ እንደ መሮጥ ጥንቃቄና ማቻቻል ያላት መሆኗን ተገንዘቡ ።

7- ሥርዓት ጌጡን በቦታው ማስቀመጥ ነው። ለማን ምን መናገርና መስጠት እንዳለብን መለየት እርሱ ሥርዓት ነው። የጋኑን በገንቦ መገልበጥ ሥርዓት ማጣት ነ ው። ያወቅነውን  ሁሉ ላወቀ ሰው  እንጂ ላወቅነው ሰው አይወራም። ብዙ ማውራትም ያስንቃል። የሰውነታችን ብዙ ኃይል የሚወጣው በመናገር ነውና ንግግራችን የተቆጠበና የተቀመረ መሆን አለበት። ብዙ ንግግር ስህተት አያጣውም። የአፍ ማዳለጥ እንዳቀያየመ ይኖራል።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 9 ቀን 2ዐ17 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ