የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት ( 45 )

አዎንታዊ ሥነ ሥርዓት ይኑርህ /2

ሰዎች “ሥነ ሥርዓት ይኑርህ” ብለው ከተናገሩ ቍጣ ላይ እንዳሉ ግልጽ ነው ። “ሥነ ሥርዓት ይኑርህ” ሲሉም እንዳታጠፋ እያሉ ሳይሆን በጥፋትህ እንዳትቀጥል እያሉ ነው ። ስለዚህ ሥነ ሥርዓት አንደኛ አለማጥፋት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በጥፋት አለመቀጠል ነው ። “ካፈርኩ አይመልሰኝ” የሕይወት ሥነ ሥርዓት አይደለም ። መርዝ መጠጣት የጀመረ ሰው ካፈርኩ አይመልሰኝ ካለ ቀጥሎ ሟች ነው ። ሲጨርሱት ክብርና ሕይወት ያለው መልካም ነገር ብቻ ነው። የአገራችን ሰው ጨርሶ ነው የሚኖረው ። ጨርሶ የሚኖር ሰው መማር ፣ መጸጸት ፣ መመለስ ፣ ይቅርታ መጠየቅ አይፈልግም ። ይቅርታ ከምንጠይቅና አንድ ሚሊየን ሰው ከሚያልቅ ብንባል አንድ ሚሊየን ይለቅ የምንል ነን ። ሥርዓተ መንግሥት ብለን እንናገራለን ፣ የመንግሥት ሥርዓት ፣ መንግሥታዊ ሥልጣን ፣ አሁን እየገዛ ያለ ሕግና መሪ ማለት ነው ። ሥርዓት ሥልጣንን ያመለክታል ማለት ነው ። ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ተብሎ ክስ ሲቀርብ ስንሰማ መንግሥቱን ፣ ሕገ መንግሥቱን ማለት ነው ። ሥርዓት ሥልጣን ነው ። ሥርዓት ያለውን ሰው በቤታችን በሕይወታችን ላይ ሙሉ መብትና አደራ እንሰጠዋለን ። ሥርዓት ለሹመት የሚያሳጭ ፣ ለምሥጢር ተፈላጊ የሚያደርግ ነው ። ሥልጣን ያላቸው ፣ እውቀት ያላቸው ፣ ሀብት ያላቸው ሰዎች ሥርዓት የላቸውም ተብለው ይናቃሉ ፣ ይፈራሉ ። ሥርዓት ያለው ሰው ከበላይ ሁኖ የሚያዝዝ እግዚአብሔርና የሕሊና ሕግ ያሉት ነው ። ሥርዓት ያለው ሰው እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰውን የሚያፍር ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ብቻውን እንዳለ ሰው ቤቱን ፣ መንደሩን ፣ አገሩን አያዝበትም ። የጋራ ዓለም ነውና ። ሥርዓት ሌላውን ማክበር ነው ። ክብርን የምንፈልግ ከሆነ ማክበር አለብን ። የዘሩትን ማጨድ ክብርን የሚመለከትም ሊሆን ይችላል ።

“ማክበር መከበር ነው ፣
መወደድ ነው መውደድ ፣
ላዋርድ ካሉማ ይመጣል መዋረድ”

“በሥርዓት አድርገው” የሚል ምክር ከሰማን በተርታ አድርገው ማለት ነው ። የሚቀድመውንና የሚከተለውን ለይ ማለት ነው ። የሰው ዕድሜ የሚባክነው የሚከተለውን ቀዳሚ በማድረጉ ነው ፣ ለቀዳሚው ደግሞ ጊዜና አቅም ሲያጣ ያን ጊዜ መጨነቅ ይጀምራል ። አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ አስቸኳይ አይደሉም ። አስፈላጊውንና አስቸኳዩን መለየት ያስፈልጋል ። ከሥራ በኋላ የሚያጫውተንን ነገር ሥራን ትተን ካደረግነው የሚኖርልን ሌላ ወገን አለ ማለት ነው ። ስልኮቻችንን ማየት ያለብን ከሥራ በኋላ ለጥቂት ጊዜ ነው ። ሙሉ ሕይወታችን እዚያ ላይ ከተጠመደ አእምሮአችን ጤነኛ ፣ ጉልበታችን አምራች መሆን አይችልም ። በሕይወታችን ተርታ ያስፈልገናል ። ሱሪ ሳንለብስ ጫማ ብናደርግ ከመፍጠን ይልቅ መዘግየትን እናመጣለን ። መቸኮል መዘግየት ነው የሚባለው ለዚህ ነው ። ለዛሬ አስፈላጊውና አስቸኳዩ ምንድነው ? ብለን መለየት ፣ ለማያስቸኩለው ነገር ቀጠሮ መስጠት ተገቢ ነው ። ሁሉንም ነገር ዛሬ ካልከወንሁ ማለት ሁሉንም ነገር አለማድረግን ያመጣል ። ለነገም ሥራ ማስቀመጥ አለብን ። ጥንቅቅ ያለ ቤት ፣ የተሟላ የትዳር እሴት ጨብጦ ስለ ማግባት ማሰብ የለብንም ። እያንዳንዱ ነገር በጊዜው ሲሟላ ብዙ ደስታ ለማየት በተርታ ማድረግ ይገባናል ። በድሀ ቤት ብዙ የልብ ሙቀትና ደስታ ያለው ከብዙ ልፋት በኋላ በር ሲቀየር የድል አድራጊነት ስሜት ይኖራል ። ሁሉንም ነገር ስለማሟላት ማሰብ አስፈላጊ አይደለም ። ነገ ላይ ምን ልንኖር ነው ? የአማዞን መሥራች ባለሀብት “ጭንቀት የሥራ ብዛት ሳይሆን መሥራት እየቻልን ያልሠራነው ነገር ነው” ብሏል ።

ዓለም ስትዋቀር በአንድ ቀን ጉዳይን ለመፈጸም ዕድል ያላት ሆና አይደለም ። እግዚአብሔር ከፈቀደ ነገም የእኛ ነው ። ሥራን በጊዜ መፈጸም መልካም ነው ። ሥራን ሁሉ ግን ዛሬ እፈጽማለሁ ማለት ራስን ለጭንቀት መዳረግ ነው ። ይልቁንም ልናደርጋቸው እየቻልን ያላደረግናቸው ነገሮች እንዳፈጠጠ አውሬ በየሰዓቱ ይታዩናል ። የሚገርመው ቆም ብለን እነዚህን ጥያቄዎቼን ልመልስ አንልም ። በማይረባ ነገር ጊዜአችን እየባከነ ለሚያስጨንቀን ነገር መፍትሔ አንፈልግም ። መርዳት እየቻልን የሞቱ ወላጆቻችን ፣ መጠየቅ እየቻልን ናፍቀው የቀሩ ወዳጆቻችን የሕይወት ቅሬታን ያመጡብናል ። ለሚወዱን ቅድሚያ መስጠት የሕይወት ሥነ ሥርዓት ነው ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 15 ቀን 2ዐ17 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ