አጉል ልማዶችን ተዉ
አጉል ልማዶችን ከሥር ጀምሮ ወላጆች ያስጥሉናል ። ቀጥሎ መምህራን ያስተዉናል ። መጻሕፍትም እንደ ሸለፈት የሆነውን ፣ ውበትና ጤንነትን የሚጎዳውን ክፉ ልማድ እንድንተው ያግዙናል ። የሰው ልጅ በሕይወት እስካለ ድረስ ለማወቅና ለንስሐ ጊዜው አይረፍድበትም ። አጉል ልማድ ባለማወቅ ምክንያት ፣ ሥነ ሥርዓትን ባለመማር ፣ ልቅ በሆነ ባሕል ውስጥ በማደግ ፣ ሥልጣኔ በሚመስል ዘላንነት በመያዝ ሊመጣ ይችላል ። አጉል ልማዶች እጅግ ብዙ ሲሆኑ ሁሉንም መንቀስ አይቻለንም ። አጉል ልማዶች ትንሽ የሚመስሉ ትልቅ ጥፋት የሚያስከትሉ ናቸው ። አጉል ልማድ ውስጥ ካለን ከሰዎች ጋር እንጋጫለን ። ሰዎች ባይጋጩንም ለእኛ ያላቸው ክብር ይቀንሳል ። አንዳንድ ሰዎች ሊነግሩን ይችላሉ ። የሚበዙት ግን እየታዘቡ ዝም ይሉናል ። በአፍ መፍረድ ፣ በልብ መታዘብ ሁለቱም አንድ ዓይነት ኃጢአት ቢሆንም ሰዎች ታዝበው ዝም ይሉናል ። መመከርን መቋቋም የማንችል ፣ ግን ብዙ ግድፈት ያለብን ሰዎች ልንሆን እንችላለን ። በዚህ ምክንያት የበለጠ እኛን ላለማጣት ዝም የሚሉን ይበዛሉ ።
መኝታ አታብዛ ። ገንዘብ እየፈለግህ መኝታ እያበዛህ አይሆንም ። አንተ እንድትተኛ የተጉልህ ሰዎች ይኖራሉ ። ነገር ግን እነርሱ ጊዜያዊ እንጂ ዘላለማዊ በረከቶችህ አይደሉምና እልፍ ይላሉ ። ያን ቀን በራስህ መቆም ያቅትሃል ። የራስህ ሕይወት ስለሌለህ የእነርሱ ህልውና ሲያበቃ ያንተም ያበቃል ። ወረተኛ አትሁን ። ሸሚዝ እንጂ ሰው አይቀያየርም ። ቶሎ ስልቹ ሆነህ መልሰህ እገሌን አታሳዩኝ ፣ አታሰሙኝ አትበል ። ሰው ብዙ ነው ፣ ሰው ጥቂት ነው ። ካከበርከው ሰው ብዙ ነው ። ከናቅኸው ግን ሰው ጥቂት ነውና አንድ ሰውም ታጣለህ ። ወሬ አታጣጥም ። “ፐ ፣ ይገርማል ፣ እስኪ ንገኝ” እያልህ የወሬ ሱስህን አትወጣ ። አንዳንዱን ነገር ባትሰማው የተሻለ ነው ። ፊት ለፊት ልትነግረው የፈራኸውን ሰው ከኋላው አትማው ። ስታወራ ከንፈርህን እየመጠጥህ ፣ ግንባርህን እያሸህ አታውራ ። ስትሰብክ አትወራጭ ፣ ከቦታ ቦታ አትፍለስ ። እጅህን አታወናጭፍ ። ሰዎች በግልህ የነገሩህን ራሳቸው ያውሩ እንጂ ስማቸውን ጠርተህ በአደባባይ አታውራ።
ምግብ ስትመገብ በመጠኑ ጥቅልል እንጂ ሰሐኑን እንደሚወስዱበት ሰው ከልክ በላይ አትጠቅልል ። ጥቂት በጥቂት መጉረስ ክብር ነው ። ስትበላም አፍህን ገጥመህ ብላ እንጂ ስታላምጥ አጠገብህ ያለ ሰው መስማት የለበትም ። በትልቅ ማዕረግ ላይ ያለህ ከሆንህ በአደባባይ ምግብ አትብላ ። ጳጳሳት በአደባባይ ባይመገቡ ይመከራል ። ወደ ድግስ ስትጠራ በልተህ ሂድ ። በምንም መንገድ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጣ ። ጠላት ያለበት ሰው በሴት ፣ በሆዱና በአልኮል መጠጥ ያጠምዱታልና ተጠንቀቅ ። ሰዎችን ስታወራና ስታናገር ፊት ለፊት እያየሃቸው ተነጋገር ። አፍረህ አንገትህን መቅበር ፣ እንደ ተንኮለኛም ግንባርህን አቀርቅረህ በዓይንህ ግልባጭ ሰውን ማየት በጣም ነውር ነው ። ሰው አፍ ውስጥ የምትገባ እስክትመስልም አፍጥጠህ አታነጋግር ። ሰዎቹን ራሳቸውን ተመልከት እንጂ የለበሱት ልብስ ፣ ያደረጉት ጫማ ላይ ዓይንህን አትላከው ። እንደ ውሻም እግር እግር አትመልከት ። ዜማ ስታዜም ፣ መዝሙር ስትዘምር የላይኛውንም የሥረኛውንም ጥርስህን አታሳይ ። ጥርሱን የሚያሳይ የሞተና የረገፈ አጽም ብቻ ነው ። እቤትህ ሳትጨርስ ደጅ ላይ ወጥተህ ቀበቶህን መፍታትና መዝጋት ነውር ነው ። በሰው ላይ ማዛጋት ፣ ሰው ፊት መሐረብ ሳይሸፍኑ ማሳልና ማስነጠስ ተገቢ አይደለም ። ቀጠሮ አክብር ። ሁለት ጊዜ ደውለህ ስልክ ያላነሣልህ ሰው ጋ መደወል አቁም ።
ሰዎችን ሰላም ብለህ ከሸኘህ በኋላ ዞር ብለህ አትመልከታቸው ። ጀርባን የሚያይ ጠላት ነውና ። ከሰዎች ጋር ሆነህ ስልክህን አትጎርጉር ። ከተከበረ ሰው ፊት እግርህን አጣምረህ አትቀመጥ ። ታላቅህ ሲመጣ ከመቀመጫህ ተነሥተህ ተቀበለው ። ሲደወልልህ ስልክህን አንሣ ። ማንሣት የማትፈልግ ከሆነ ጉዳዩን ገልጸህ እንዳይደውሉ አድርግ ። ሰዎችን በገዛ ስህተታቸው ይቅርታ አትጠይቅ ። ይህ እውነትን የሚቀብር ፣ መለማመጥን የሚያሰፍን ነው ። ደግሞም ስህተታቸውን እንዳያዩ አስተዋጽኦ ታደርጋለህ ። ካልተገራ ሰው ጋር ቀልድ አትቀልድ ። ባለጌ ሥራውን አይረሳምና ለመደ ብለህ በርህን አትክፈትለት ። ለሰዎች ቀጠሮ ስትሰጥ ጉዳዩንም አብረህ ንገራቸው ። “እፈልግሃለሁ ብርቱ ጉዳይ አለ ፣ አሁን አልነግርህም” እያልህ የሰውን ሰላም አትንሣ ። የማትጨርሰውን ወሬ አትጀምር ። “ይህ ለምን ሆነ ?” አትበል ፤ እንዲህ እንዲሆን እኔ ምን አጥፍቻለሁ ? ብለህ ታረም ። የማምሸት ልማድህን ተው ። በጊዜ መተኛትን ልመድ ። ሰዎች ሲናገሩ አታቋርጣቸው ። እኔ ብቻ ልናገር አትበል ። ሁሉን እንደምታውቅ ከተሰማህ ታመሃልና እርዳታ ያስፈልግሃል ። ምንም ብትቀራረብ ባለሥልጣንን በአደባባይ አንተ ብለህ አትጥራ ። የጎሣና የቋንቋ ትችት ያለበት ወሬ አትጀምር ። ያየኸውን የሰው ገመና ለሌላው አትናገር ። ይህ የጸሎት እንጂ የወሬ ርእስ አይደለምና ። መጓዝ ያለብህ ሰዎች እስከፈቀዱልህ ድረስ ብቻ ነው ። ያልተፈቀደልህን መስመር ስታልፍ የተፈቀደውንም ታጣለህ ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም.