የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ሥነ ሥርዓት 9

8- አለባበስህን ጠብቅ

ለልብሳቸው የሚጨነቁ ለልባቸው ግድ የሌላቸው ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ፤ ለልባቸው የሚጨነቁ ለልብሳቸው ደግሞ ግዴለሽ የሆኑ ሰዎች አሉ ። ሕይወት ግን ሚዛናዊ ናት ። አስበን መልበስ መልካም ነው ፣ ተጨንቀን መልበስ ግን ራስን ማድከም ነው ። እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ ለአዳምና ለሔዋን ልብሰ ብርሃን አልብሷቸው ነበር ። ይህ ልብሰ ብርሃን ጸጋ እግዚአብሔር ነበረ ። የዚህ ልብሰ ብርሃን ጠባዩ ልዩ ነው ፤ ብርሃን ሁሉ ዕራቁትን ያሳያል ፣ ይህ ልብሰ ብርሃን ግን ይሸፍናል ። ልብስ ሁሉ ይወይባል ፣ ይነትባል ፣ ያልቃል ። ይህ ልብሰ ብርሃን ግን እየታደሰ ይኖራል ። አዳምና ሔዋን በኃጢአት በወደቁ ጊዜ ይህን ልብሰ ብርሃን ተገፈፉ ። ስለዚህም ዕራቁታቸውን እንደሆኑ አወቁ ፣ ተፋፈሩ ። አዳም በሔዋን ላይ የነበረውን የጸጋ ያያል ፣ ሔዋንም በአዳም ላይ ያለው ጸጋ ታያለች ። የሚያዩት ጸጋን ብቻ ነውና አንዱ በአንዱ ፊት የከበረ ነበር ። ሲመሽ የዋለው ልብስ ይወልቃል ። ልብሰ ብርሃን ግን በምሽት የሚወልቅ አልነበረም ። ልብሰ ብርሃን በአቧራ ፣ በጭቃ የሚቆሽሽ ልብስ አልነበረም ። ንጹሕ ልብስ ነበርና ሌላውንም ንጹሕ አድርጎ ያሳያል ። ልብስ ሁሉ ቅያሪ አለው ፣ አዳምና ሔዋን ግን ይህን ልብስ ለዘመናት ለብሰውት ነበር ።

በኃጢአት በወደቁ ጊዜ እግዚአብሔር የቁርበት ልብስ አደረገላቸው (ዘፍ. 3 ፡ 21) ። ይህ የቁርበት ልብስ ገበሬው የሚለብሰው ሌጦ ፣ ዘመናዊው ሰው የሚለብሰው ሌዘር ልብስ ነው ። መጽሐፍም ስለ አለባበስ ሕግ አለው ። ይህ በብሉይም በሐዲስም የጸና ነው ። ሴቶች በወንድ ልብስ ማጌጥ ፣ ወንዶችም በሴት ልብስ ማጌጥ አይፈቀድላቸውም ። ሴቶች መሸፈን ፣ ወንዶች ራሳቸውን መግለጥ የተፈጥሮና የመንፈሳዊነት ሕግ ነው ። ሴቶች ፀጉራቸውን መቆረጥ ፣ ወንዶች ማሳደግ አልተፈቀደም (1ቆሮ. 11፡14-16)። ስለ አንድ ዕቃ አጠቃቀም የሠራው ፋብሪካ ቢናገር ይበልጥ እናምነዋለን ። ስለሚያምርብንን የፈጠረን እግዚአብሔር ሲናገር በደስታ ልንቀበል ይገባናል። የሚገርመው ወንዱ የሴት ልብስ ቢለብስ ብዙ ውግዘት ይነሣል ፣ ሴት የወንድን ልብስ ስትለብስ ዝም ይባላል ። እግዚአብሔር የመረጠልን ጾታ ክቡር ነው ። እያንዳንዱ ጾታም የራሱ አለባበስ አለው ። በዚህ ዓለም ላይ ሦስት ዓይነት ወገኖች የአለባበስ ሥርዓት አላቸው ። እነርሱም ወንዶች ፣ ሴቶችና የሃይማኖት መሪዎች ናቸው ።

መጽሐፍ እንዲህ ይላል፡- “ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፥ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ ይህን የሚያደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና።” ይላል (ዘዳ. 22፡4) ። ዳግመኛም፡- “በእግዚአብሔርም መሥዋዕት ቀን አለቆችንና የንጉሥን ልጆች እንግዳ ልብስ የሚለብሱትንም ሁሉ እቀጣለሁ።” (ሶፎ. 1 ፡ 8) ።

ልብስ የባሕል መግለጫ ነው ። በዚህ አንጻር የምንለብሰው ልብስ የምዕራባውያንን ባሕል የሚገልጥ ነው ። ልብስ የሃይማኖት መግለጫም ነው ። በልብሱ አገሩን ፣ ባሕሉን ፣ ሃይማኖቱን እናውቃለን ። ልብስ የጾታ መግለጫ ነው ። የሴት ልብስ ለብሰው አደጋ ያደረሱ ወንዶችን እንሰማለን ። የወንድ ልብስ ለብሰውም አደጋ ያደረሱ ሴቶችን በቅርበት እየሰማሁ ነው ።

በማኅበረሰብ ዘንድ ጤናማ መተማመን እንዲኖር ልብስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ። አንድ ሰው አእምሮውን ስቷል ለማለት አንዱ ማስረጃችን ልብሱን ጥሎ መሄዱ ነው ። የሰው ልጅ የግል የሆነ የአካል ክፍል አለው ። እግዚአብሔር ሲፈጥረው ማኅበራዊ ብቻ ሳይሆን ግላዊም አድርጎ ነው ። ይህ ሕግ ሲጣስ ብዙ ጥፋት ይከተላል ። ልብስ የአንድን ሰው ሥነ ልቡናዊ ማንነት ይገልጻል ። በልብሳችን ላይ ልባችን ይታያል ። ልብስ ከሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎት አንዱ ነው ። አንድ ሰው ባለመልበስ ብቻ ለሞት ሊዳረግ ይችላል ። ብርዳማ በሆኑ አካባቢዎች ልብስ ከሕይወት ጋር የተያያዘ ነው ። የታመሙ ወገኖች በብርድ ምክንያት የበለጠ ኃይል እንዳያባክኑ ሙቀታቸውን በልብስ መጠበቅ አለባቸው ። እግዚአብሔር አምላክ ለልብስ የሚሆኑ ነገሮችን እንደ ጥጥ ያሉትን በመፍጠሩ ልናመሰግነው ይገባናል ። ልብስ የፋብሪካ ውጤት ይመስለናል ። ጥሬ ዕቃው ግን የእግዚአብሔር ነው ፣ የተሠራበት አእምሮም የእርሱ ገንዘብ ነው ። ታዲያ አለባበሳችን ምን መምሰል አለበት ። ይህ ከሕይወት ሥነ ሥርዓት አንዱ ነውና ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 28 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ