የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የመሆን አገልግሎት

“እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል” 1ጢሞ. 3፡2
እግዚአብሔርን ለማገልገል የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና የሰው ፍላጎት አስፈላጊ ነው ። ሰዎች በተለያየ ሁኔታ እግዚአብሔርን ለማገልገል ይፈልጋሉ ። አገልግሎት ለእግዚአብሔር ጊዜን ብቻ ሳይሆን ሕይወትንም መስጠት ነው ።ወደ አገልግሎት ለመግባት የሚፈልጉ ሰዎች ሊያስተውሉ የሚገባቸው ነገሮች አሉ ። የመጀመሪያው “የእግዚአብሔር ጥሪ አለኝ ወይ ?” የሚል ነው ። አብሮ አደጋችን ወይንም እኛ ወደ ቤተ ክርስቲያን ያመጣነው ሰው አገልጋይ ስለሆነ እኛም አያቅተንም ብለን የምንገባበት አይደለም ። ታላቁ ተቀምጦ ታናሹ ለአገልግሎት ይጠራል ። እኛ ያመጣነው ሰውም ከእኛ በላይ ይሮጣል ። አገልግሎት ግን ቁመት እየተለካካን የምንገባበት አይደለም ። እግዚአብሔር በቀጥታ ባለቤቱን ይጠራል ፣ ይህ እንደ ሙሴ ነው ። በሰው በኩል ይጠራል ። በነቢዩ ኤልያስ ኤልሳዕ ተጠርቷል ። ወደ አገልግሎት ጠቅልለን ለመግባት የእግዚአብሔር ጥሪ አስፈላጊ ነው ። እግዚአብሔር ሁለት ዓይነት ታላላቅ ጥሪዎችን ያመጣል ። አንዱ ለመዳናችን ሲሆን ሁለተኛው ለአገልግሎት ነው ።

ወደ አገልግሎት ከመግባታችን በፊት ልናስተውለው የሚገባን ሁለተኛው ነገር ጸጋው አለኝ ወይ ? የሚል ነው ። ጸጋው ያድናል ፣ ጸጋው ይቀድሳል ፣ ጸጋው በመከራ ውስጥ ኃይል ይሰጣል ። ማንም በግል መሣሪያው ለመንግሥት ግዳጅ አይዘምትም ። እንዲሁም በግላዊ ችሎታ ብቻ እግዚአብሔርን ማገልገል አይቻልም ። እግዚአብሔርም እርሱን የምናገለግልበት ጸጋ ይሰጣል ። ያለ ጸጋ አገልግሎት ትግል ብቻ ይሆናል ። ቊጠኛና ራሳቸውን የእግዚአብሔር ፖሊስ እንደሆኑ አድርገው የሚያዩ አገልጋዮች ያለ ጸጋቸው የገቡበት ሊሆን ይችላል ። ያለ ቦታቸው ሲገኙ የእነርሱ ቦታ ክፍት ይሆናል ። ያለ ቦታቸው አሉና ባለ ቦታውን መግፋትና ማጥፋት ይጀምራሉ ። ፖለቲካ ውስጥ ኖረው የመጡትን ሰባኪ ለማድረግ ሲሞከር ፣ ዘፋኝ የነበሩትንም ዘማሪ እንዲሆኑ ሲታጭ ብዙ ጊዜ እናያለን ። ነገር ግን ጸጋ አስፈላጊ ነው ። በዓለም ተግባር ውጤታማ በሆንበት ክህሎት እግዚአብሔርን ማገልገል አይቻልም ። የእግዚአብሔር ቤት ሰማያዊ ዓለም ነው ።
እግዚአብሔርን ለማገልገል በሦስተኛ ደረጃ ዋጋን መተመን አስፈላጊ ነው ።
አገልግሎት ላለፉት ሠላሳ ዓመታት እንዳየነው ቀላል አይደለም ። በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ የሚመጣ ፈተና ያለበት ነው ። ብዙ ሰዎች ጌታን የያዘ ምን ይሆናል ? እያሉ ይናገራሉ ። ግን ምን የማይሆነው አለ ? ስብከትን እንደ ጩኸትና እንደ ሙያ ለሚያስቡት አገልግሎት ቀላል ነው ። እረኝነትንም የበጉን ሥጋ ለመብላት ፣ አጥንቱን ለመጋጥ ፣ አንዳንዴም በቁሙ ቆዳውን ለመገሽለጥ ለሚያስቡ ተራ ነገር ነው ። አባታዊ ስሜት ለሚሰማቸው ፣ የሚያገለግሉትን እንደ ደምበኛ ሳይሆን እንደ መንፈሳዊ አካል ለሚያዩ ግን ዋጋ ያስከፍላል ። ሰው አገልጋይ ሲሆን የሰውነቱ ፈተና ይቀራል ማለት አይደለም ። አገልግሎት ሰውነትን ይዘን የምንገባበት እንጂ ጥለን የምገባበት አይደለም ። ቀጥሎ ከምናገለግላቸው ከራሳቸው ትልልቅ ፈተና ይመጣብናል ። ተገልጋዩ ይሁዳ ጌታውን እንደ ሸጠው አትርሱ ። ቀጥሎ ግዛቴ ተደፈረ ፣ የእኔ ስም ደበዘዘ በሚሉ አገልጋዮች የሃይማኖት ካባ የለበሰ ፈተና ይመጣል ። ከዚያም እግዚአብሔርን ከማያውቁ ሰዎች የሚወግር ድንጋይ ይወረወራል ፣ የሚመትር ሰይፍ ይሰነዘራል ። ረሀብም ጥማትም ተራውን እየያዘ ይመጣል ። አገልግሎት መስቀል ከሌለው እውነተኛውን ክርስቶስ እያገለገልን ላይሆን ይችላል ። ብዙ መስቀል የሌለባቸው ሰዎች መስቀል አሸካሚ ናቸው ። በዱላ የሚያገለግሉ ፣ ሲሰድቧቸው እጥፍ ስድብ የሚልኩ እነርሱ ፈተና የሌለባቸው ይምሰሉ እንጂ ሕይወታቸውን ከስረው የሚያገለግሉ ናቸው ። የግል እስር ቤት ያላቸው ፣ የደብዳቢ ቡድን አዘጋጅተው የሚነካቸውን የሚቀጡ አገልጋዮች እንዳሉ እየሰማን ነው ። እነዚህ ዋጋ የሚያስከፍሉ ናቸው እንጂ ዋጋ የሚከፍሉ አይደሉም ።
አራተኛ ለአገልግሎት የሚያስፈልገው ደረጃ ነው ። ዘሎ ወደ መድረክ መውጣት ፣ ብዙዎችን በትዕቢት የጣለ ፣ የበላዮቻቸውንም በመናቅ ከመንገድ ያስቀረ ነው ። ዕድሜአቸው ጠገግ ያላሉ ሰዎችን መድረክ ማስለመድ በቶሎ እንዲወርዱ ያደርጋል ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዓርገ ክህነት ለዚህ በጣም ጠቃሚ መሆኑን አምነው ሁሉም ቢከተሉት የተሻለ ነው ። ከመዘምራን ይጀምራል ። የእነዚህ ቦታ መግቢያው ጋ ቅኔ ማኅሌት ነው ። ቀጥሎ አናጉንስጢስ አለ ። በቅድስቱ ውስጥ ማንበብ ነው ።አናጉንስጢስ ወደ ዲያቆን ያድጋል ። ዲያቆኑ ወደ መቅደስ ይገባል ። መቅደሱ ውስጥም መንበሩን መንካት አይችልም። ስለዚህ ቄስ ሲሆን መንበሩን ይነካል ። ቀጥሎ ወደ ኤጲስ ቆጶስነት ሲያድግ መንበሩን መባረክ ፣ ክህነት መስጠት ይጀምራል ። አገልግሎቱ ደረጃ ስላለው ከቦታው ጀምሮ ድርሻው የተለያየ ነው ። ሰው ዘሎ ጳጳስ አይሆንም ። መሠረት እየያዘ አድጎ ፣ ከዕድሜው ዘለግ ሲል የሕዝብ አደራ ይቀበላል ። አገልግሎት ደረጃ ሲኖረው የሚከፈል ዋጋ አለና አክብሮ ይያዛል እንጂ በተበሳጩ ቊጥር ጥሎ መሄድ አይኖርም ። በቀላሉም ከአገልግሎት አይወጣም ። በአብዛኛው  ወታደር እስከ ዕለተ ሞቱ ወታደር ነው ። በየጊዜውም መዓርጉ ያድጋል ። ዘለው ላይ የወጡ ካሉ ማደግ ከፈለጉ መጨረሻ ላይ ስላሉ እርካታ ያጣሉ ።
አምስተኛው ሕይወቱ የተሰጠ ሊሆን ይገባዋል ። አገልግሎት እንደ ሐኪም ልብስ አውልቀን ወደ ቤታችን የምንሄድበት አይደለም ። አገልግሎት እንደ ሠራተኛ ከሥራ ሰዓቴ ውጭ ብለን የምንገፋው አይደለም ። አገልግሎት ሕይወታችንን የምሰጥበት እንጂ ሕይወቴ ብለን የሌላውን ሕይወት የምንቀጥፍበትም አይደለም ። ሕይወታችን ክርስቶስ እንጂ አገልግሎት አይደለም ። አገልግሎትን እንደ ግል ሱቅ የሚያዩ ሰዎች ሕይወቴ ነው ይላሉ ። እነዚህ ሰዎች የነካቸውን ሳይሆን በአጠገባቸው ያለፈ የሚመስላቸውን ሰው ለማጥፋት አይመለሱም ። አገልግሎትንም ራእዬ ብሎ መጥራት ተገቢ አይደለም ። ወንጌል የሥላሴ እቅድ እንጂ የእኛ ራእይ አይደለምና ።
ስድስተኛ ለአገልግሎት የሚያስፈልገን ነገር መሆን ነው ። መምሰል የትም የማያራምድ ከቅርብ የሚያሳድር ነው ። መስሎ ማገልገል የሌላውን እምነትና ነጻነትን መዳፈርን ያመጣል ። ኦርቶዶክስ አይደለሁም ነገር ግን መስዬ ላገልግል ማለት ተገቢ አይደለም ። በሁሉም መንገድ መሆን እንጂ መምሰል ተገቢ አይደለም ።
ሰባተኛ ብሶትን ይዞ መግባት ተገቢ አይደለም ። ሰዎች የተጎዱበት የተለያየ ስብራት አላቸው ። ያንን ስብራት ይዞ መግባት በቀለኛ የሚያደርግ በመሆኑ ከእግዚአብሔር አሳብ ይለያል ። የትላንትን ክፉ ገጠመኝ መርሳት የማይችል ሰው ወደ አገልግሎት ባይገባ መልካም ነው ። ዘራፍ እያሉ ሕዝብ የሚያሳድሙ ብሶታቸውን ጥለው ያልመጡ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች ጭር ካለ ዓለም የሚያልፍ ይመስላቸዋል ። አገልግሎት ግን ለአሙቁልኝ የምንጠራበት ሳይሆን አፈ ክርስቶስ የምንሆንበት ነው ። የሰዎች ስሜትና የራሳችንን ብስጭት መግለጫ መድረክም አይደለም ። አንድ ሺህ ሰው ባለበት ለአንድ ሰው የሚናገሩ ሰዎች ይህን ብሶት ያልረሱ ናቸው ። አደባባዩ የእኛ አይደለምና የራሳችንን ታሪክ ልናወራበት አይገባም ።
ጌታ ሆይ አንተ የምትፈልገው አገልጋይ አድርገህ ሥራን ።
1ጢሞቴዎስ 33
ጥር 5 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ