መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የመምህራን ክብር

የትምህርቱ ርዕስ | የመምህራን ክብር

እባካችሁ አንብቡት

እግዚአብሔር ይህችን ዓለም ያለ መካሪ አልተዋትም ። ሌሊትን ያለ ጨረቃ ያልተወ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ያለ አስተማሪ አልተወውም ። አዳም ሲፈጠር ነቢይነት ተቀዳጅቶ ነው ። ነቢይ ዛሬን የሚገሥጽ ፣ ነገን የሚያሳይ ነው ። ነቢይ አእምሮ ይበራ ዘንድ ሰማያዊ ፋና የጨበጠ ነው ። ነቢይ በዚህ ዓለም ላይ መኖሩ ለእርሱ ከሚጠቅመው ይልቅ ለሕዝብ ይጠቅማል ። አንድ ሊቀ ጳጳስ በዕድሜ ሸምግለዋል ፣ “ለእኛ ሲል ያቆይልን” ሲሏቸው ይቆጣሉ “ለእኔም እዘኑልኝ ፣ ቶሎ ሄጄ ጌታዬን ልየው” ይላሉ ። ላም ወተትዋ ለእርስዋ ከሚጠቅማት ይልቅ ለጥጃዋና ለሕፃናት ይጠቅማል ። ሕይወት ይሰጣል ፣ ያሳድጋል ። አገልጋይም ለራሱ የሚጠቅመው እምነቱና አምልኮ ነው ። አገልጋይነቱ ግን የሚጠቅመው ለእኛ ነው ። ጨረቃም የምትሰወርበት ጊዜ አለ ። ቃሉና የቃሉ መምህራን የሚጠፉበት ጊዜ አለ ፣ በቅርብ ዘመን ይሆናል ። አንዳንድ ዘመን የሞቱትን ደጋጎች መቃብራቸውን ፈልገን ማሩኝ የሚያሰኙ ናቸው ። እውነተኛ አስተማሪ እንደ እህል ይርባል ፣ እንደ ውኃ ይጠማል ። የወላጅ ዋጋ ሳለ አይታወቅም ፣ ወላጆች ያለፉ ቀን ጸጸቱ መብረጃ ፣ ትካዜው ማገጃ የለውም ። አስተማሪ ፣ ብሉይ ሐዲስን የሚተነትን ወላጅ ነው ። የሚቆጩን ቀን ይመጣል ።

በአይሁዳውያን ባሕል መምህራን ትልቅ ስፍራ ይሰጣቸዋል ። በርግጥም እስራኤል በመንግሥትነት ከኖረችበት ይልቅ መንግሥት አልባ ሁና የኖረችበት ይበልጣል ። እስራኤል የሚባል ዘር ፣ ዕብራይስጥ የሚባል ቋንቋ ፣ ቶራ የሚባል መመሪያ የተረፈው በመምህራን ነው ። መምህራን ለብዙ ሺህ ዓመታት ሕግን አጥንተው ፍትሕ ሚኒስቴር ነበሩ ። ፊደል ከማስቆጠር ጀምሮ በመልፋት ትምህርት ሚኒስቴርን ወክለው ኖረዋል ። መድኃኒት ቀምመው በማዳን የጤና ሚኒስቴር ነበሩ ። ዜማን ከነምልክቱ በመስጠት የባሕልና ኪነ ጥበብ ሚኒስቴር ነበሩ ። ሥርዓትን በማስተማር የንጉሥና የሕዝብ የፕሮቶኮል ሹም ነበሩ ። መምህራን ከሰማይ ጓዳ ስለሚቀዱ የሚታጣባቸው ምንም ነገር የለም ። ቋንቋ ፣ ባሕል ፣ ታሪክ ፣ ክብር እንዲቆይ ደክመዋል ። አሮጌውንና አዲሱን ትውልድ በማስታረቅ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል ። ስማቸውን አጥተው ለአገርና ለቤተ ክርስቲያን ስም ሆነዋል ፣ የሥልጣኔ መገኛ ናቸው ። ተወግዘው ለብዙዎች ማመን ደክመዋል ። አዋቂዎችን ሲሞቱ ከማወቅ ሳሉ መጠቀም መልካም ነበር ። የመምህራን ምክር ነጻ የሆነው ርካሽ ስለሆነ ሳይሆን ዋጋ ሊገዛው ስለማይችል ፣ ደግሞም በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ የሚል አምላካዊ መመሪያ ስላለ ነው ።

አይሁዳውን ከሥጋ አባት ይልቅ የእውቀት አባት የሆነው መምህር እንደሚበልጥ ያምናሉ ። እነርሱ መምህር የሚሉት ያንን የእግዚአብሔር ሰው ነው ። የሥጋ አባት ለዚህ ምድር ይወልዳል ፣ መምህር ግን ለሰማይ ይወልዳልና ክብሩ ከፍ ያለ ነው ። ሰው ሆኖ የተወለደው ሰው ሆኖ አንዲኖር መምህራን አስፈላጊ ናቸው ። የሰውን እንስሳዊና አራዊታዊ ጠባይ የሚያስወግድ እውቀት ነው ። መምህራን የነፍሳችን አጋፋሪ ናቸው ። አባትና ልጅ በመንገድ ቢሄዱ ሁለቱም እኩል የሚያከብሩት መምህሩን ነው ። ስለዚህ ከወላጅ ክብር የመምህራን ክብር ይበልጣል ማለት ነው ። ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ ያሉት የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር በድህነት የሚኖሩ በአሁኑ ወቅት ትዳር የሌላቸውና ልጆችን ያልወለዱ ናቸው ። ታዲያ “ልጅ የሎትም” ሲባሉ የሰጡት መልስ “በሕንድ ምድር የሚወለዱ ሕፃናት ሁሉ የእኔ ልጆች ናቸው” ብለዋል ። እንዲህ ለማለት ያበቃቸው የመንፈስ ምጣቸው ፣ ንብረትን ንቀው በድህነት በአገር ፍቅር ስሜት ስለሚኖሩ ነው ። መምህራንም መላውን የሰው ዘር እንደ ልጃቸው ይቆጥራሉና የመንፈስ ወላጆች ናቸው ። አንዳንድ ሰዎች እመቤታችን ከጌታ ሌላ ልጆች ወልዳለች እያሉ ያሳነሱ መስሎአቸው ይናገራሉ ። ልክ ነው እመቤታችን ከጌታ በኋላ የእኛ ሁሉ እናት ናት ። በሥጋ አልወለደችንም ፣ የዳነው ወገን ሁሉ ግን እናት ናት ። የዮሐንስም እናት ሁኖ በመስቀል ተሰጥታለች ። ጌታን የሚወድ ሁሉ እናታችን ይላታል ። መምህራንም አልወለዳችሁም አይባሉም ፣ ልጆቻቸው ሊቆጠሩ አይችሉምና ።

አዳም ሲፈጠር አስተማሪ ነበረ ። አባት አስተማሪ መሆን አለበት ። የመጀመሪያው አባት አዳም አስተማሪ ነበርና ። ነቢያት ፣ ፈላስፎች ፣ ሐዋርያት ፣ ሊቃውንት ፣ ሰባክያን መምህራን ናቸው ። አፍላጦን ትምህርት ቤት ከፍቶ ያስተምር የነበረ የጥንት ፈላስፋ ነው ። በትምህርት ቤቱ ደጃፍ ላይ፡- “ልጆቻችሁን እዚህ አምጡ ሰው አድርገን እንመልሳቸዋለን” የሚል ጥቅስ ለጥፎ ነበር ። ታላቁ እስክንድር ዓለምን በአጭር ጊዜ የተቆጣጠረው እስከ ዛሬ ዝናው የናኘው ፣ በስሙ ከተሞች የተሰየሙለት ከፈላስፋ እግር ሥር ቁጭ ብሎ ስለ ተማረ ነው ። ቄሣሮች ከመምህር እግር ሥር ቁጭ ብለው አልተማሩምና ምንም ዓለምን ቢገዙ ዝናቸው ደብዝዟል ።

ታዲያ በመንገድ ላይ የሥጋ አባትህ ሸክም ተሸክሞ ብታየው ታግዘዋለህ ፣ አስተማሪህ ኑሮ ከብዶበት ፣ ቃለ እግዚአብሔርን ስለመረጠ ረሀብ ታውጆበት ስታየው ለምን ታልፈዋለህ ? የሥጋ አባትህ ሲታመም ከሩቅ አገር በረህ ትደርሳለህ ፣ መምህርህ ታሞ እጸልያለሁ ብለህ እቤት መቀመጥ እንዴት አስቻለህ ? የሥጋ አባትህ ሰክሮ ስታገኘው ተሸክመህ ታስገባዋለህ ፣ ገመናውን ለራስህ ስትል ትሸፍናለህ ፣ ታዲያ መምህርህ ሲሳሳት እንዴት በአደባባይ ታዋርደዋለህ ? አንተ ያገሬ ሰው እውቀትን በመጥላት መምህራንን አሳፈርካቸው ፣ ከሥጋ አባትህ በላይ ሳሉ በማሳነስህ ክብር ራቀ ። ገመናቸው ያንተ ገመና መሆኑን ረስተህ ፣ ከምታውቃቸው በላይ እንደሚያውቁህ ዘንግተህ ስህተታቸውን አወራህ ። ተዉ አገሬ ተመለስ ! መካሪዎችህን ትተህ አጫዋቾችን አትምረጥ!

መምህራነ ወንጌል የሚከብሩበት ዘመን ይቅረብልን!

ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ታኅሣሥ 9 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ