የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የመጠመቁ ምሥጢር

እንኳን ለ2016ዓ.ም. የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ!

ጌታችን ለሦስት ዓመት አገልግሎት ሠላሳ ዓመት ተሰወረ ። ሙሴ ለአርባ ዓመት አገልግሎት ሰማንያ ዓመት ተዘጋጀ ። በዚህም ምክንያት የ430 ዘመን የባርነት ሸክም እንዲቃለል እግዚአብሔር ተጠቀመበት ። ዝግጅቱ ከሰፋ ውጤቱ ብዙ ይሆናል ። ዝግጅቱ ካነሰ ውጤቱም አናሳ ይሆናል ። ጌታችን ለእኛ አርአያ ለመሆን ሠላሳ ዓመት ተሰወረ ፤ ሦስት ዓመት አገለገለ ። የጌታችን ጥምቀት የመገለጥ ዘመን ነው ። ዘመኑም ዘመነ አስተርእዮ ይባላል ። በርግጥ መላው ዘመነ ሥጋዌ ዘመነ አስተርእዮ ቢሆንም ሠላሳ ዓመት ተሰውሮ የነበረው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነቱን የገለጠው በጥምቀት ነውና አስተርእዮ ይባላል ። አዳም የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሁኖ ተፈጥሮ ፣ ልጅነቱን አጎሳቍሏልና ክርስቶስ በሠላሳ ዓመቱ ልጅነት የምታሰጠውን ጥምቀት ሊመሠርት መጣ ። አምላክ ሲያዝዝ ልዩ ነገር እንዳለ ማሰብ ግድ ይላል ። ጥምቀት ግን ራሱ ባለቤቱ አርአያ የሆነበት ነውና ትልቅ ምሥጢር ነው ። ጥምቀት በመልእክተኛ ፣ በነቢይ በሐዋርያ ሳይሆን በክርስቶስ መመሥረቱ ታላቅ ጥቅም እንዳለው ያሳያል ። መጽሐፍ “አንተ ልጄ ነህ” እንዲል በጥምቀት በርነት የሚመጡትን “አንቺ ልጄ ነሽ” “አንተ ልጄ ነህ” ብሎ እግዚአብሔር የሚቀበልበት የምሥጢራት መግቢያ ነው ።

ጌታችን መጠመቁ ብዙ ነገሮችን ያሳየናል ። ጥምቀታችንን መባረኩን ፣ እስከ ምጽአት የሚቀጥለውን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ማስጀመሩን ያሳያል ። ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ብዙ ነገሮች ቆመው ወድቀዋል ፣ ተጀምረው ቀርተዋል ። ጥምቀት ግን አሁንም ብዙዎች የእግዚአብሔር ልጆች የሚሆኑበት ምሥጢር ነው ።

የጌታችን ጥምቀት ትሕትናን ያሳያል ። ሰው ሁሉ የሚጠመቀው ፣ የሚባረከው በሚበልጠው ካህን ነው ። ጌታችን ግን በሚያንሰው አገልጋዩ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ ። ይህም የሚበልጡንን ብቻ ሳይሆን የሚያንሱንን ማክበር እንዳለብን የሚያስረዳ ነው ። የጌታችን ጥምቀት ንስሐን እንደሚያከብር የሚያሳይ ነው ። በዮሐንስ ዘንድ እየተናዘዙ ሊጠመቁ የመጡ ብዙ ሰልፈኞች ነበሩ ። ኃጢአት የሌለበት ክርስቶስ በኃጢአተኞች ሰልፍ መካከል ቆመ ። ንስሐን የሚወድድ መሆኑን ገለጠ ። በበረት የተወለደው ፣ በዓመፀኞች ከተማ በናዝሬት አድጎ ናዝራዊ ኢየሱስ የተባለው አሁን ደግሞ በኃጢአተኞች ሰልፍ መካከል ቆመ ። እርሱ ኃጢአትን እየጠላ ፣ ኃጢአተኞችን የሚወድድ አምላክ ነው ። እኛ ደግሞ በተቃራኒው ኃጢአትን እየወደድን ፣ ኃጢአተኞችን የምንጠላ ነን!

የጥምቀቱን በረከት ያሳድርብን !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ