የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የመጣል ስሜት

እንኳን የሚናገር ሰው የምትናገር ወፍ የሚናፍቀን አንዳንድ ጊዜ አለ ። ሁሉም የረሳን ፣ ሁሉም ደጁን የዘጋብን ፣ ሁሉም ከልቡ ያራቀን መስሎ ይሰማናል ። ናዳ ሊያወርዱብን ብዙ እጆች ድንጋይ የያዙ መስሎ ያሸማቅቀናል ። ጦርነት በሌለበት በውስጣችን ሽብር ይፈጠራል ። ማለዳው ሠርክ የሆነ ፣ ቀኑ የመሸ ፣ ነግቶ ያልነጋ ይመስለናል ። ድንገት ከእንቅልፋችን ስንነሣ ፣ ለሥራ ስንዘጋጅ ፣ የቀኑን ተግባር ስናቅድ የሕይወት ጦርነት ይጀምረናል ። አንተ እኮ የተጣልህ ነህ ፣ የምትለፋው ለማን ነው ? የሚል ሙግት ይቋቋመናል ። የመጣል ስሜት ከዚህ በኋላ የሚፈልገኝ የለም ፣ ብፈልገውም እኔን ዋጋ የሚሰጠኝ ማንም የለም የሚል ሹክሹክታ አለው ። ድንገት ብስጩ ያደርገናል ። የሁሉም ነገር መፍትሔ ሞት ብቻ መስሎ ይሰማናል ። ሰማዩ ለበረከት ሳይሆን እኛን ለመጫን የተዘረጋ ጥቁር ጥላ ይሆንብናል ። ሰማይ ድሮ ሩቅ ነበር ፣ ዛሬ ግን አናታችን ላይ እንደ እንቅብ ሊከደንብን የቀረበ ዓይነት ስሜት ውስጥ ይከተናል ። የሚፈልገኝ ፣ የማስፈልገውም የለም ፣ እኔ ባልኖር ማንን አጎዳለሁ ? የሚለው የሌጣነት ስሜት ከብርቱ ጥዝጣዜ ጋር ይመጣብናል ። ሰው የሚኖርለት ነገር ሲጠፋው መኖር እየጠፋው ይመጣል ። ትልልቅ እቅዶች ፣ ከሳምንታት ፣ ከዕለታት በፊት የነበሩ ራእዮች ድንገት ይሰወሩብናል ። አዎ አንተ የተጣልህ ነህ ። ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከልጅነትህ የተረሳህ ነህ የሚል የግድ ነዋሪነት ስሜት ይጋፋናል ።

ስልኮች ሲደወሉ አናነሣም ፣ በተቃራኒው የሚደውልልኝ የለም የሚል ብሶት የወለደው ልቅሶ ይተናነቀናል ። ሰው ማግኘት አንፈልግም ፣ ሰው አይፈልገኝም እንላለን ። ሰዎች ሊረዱንና ሊያግዙን ወደ እኛ ሲመጡ እንሸሻቸዋለን ። ሰው ከመድኃኒቱ ያጣላዋልና መፍትሔአችን ላይ በር እንቆልፋለን ። ለመጸለይ አቅም የለንም ፣ ጸሎቴ አይሰማም የሚል ስሜትም ከቦናል ። ደግሞ መጸለይ አልቻልኩም የሚል ጸጸት ውስጥ እንገባለን ። ከፍተኛ የሆነ የስሜት መዘበራረቅ ይገጥመናል ። ሞትን እንመኛለን ፣ መልሶ ትንሽ ሕመም ሲሰማን እንፈራለን ። ምነው ኒውክለር በተተኮሰ ፣ አንዱ ሟች አንዱ አልቃሽ የሌለበት ፍርድ በመጣ እንላለን ፣ ወዲያውም ፊኛ ሲፈነዳ ልባችን ትር ትላለች ። ሰዎች እንዳያውቁብኝ እንላለን ፣ መልሰን በሬዲዮ ለዓለም ስሜቴን በገለጥሁ እንላለን ። ፍርሃትና ድፍረት ሜዳ አድርገው ይታገሉብናል ። ያ እልኸኝነታችን ይከዳናል ፣ ጉብዝናችን ትቶን ይሄዳል ፣ የወገባችን መታጠቂያ ይላላል ፣ ለመሮጥ አቅም እንዳይኖረን የጫማችን ማዘቢያ ይፈታል ። ልባችን ሲደልቅ ጎረቤት የሚሰማ ይመስለናል ። የሕልሙ ዓለም አለቅህ ብሎ በቁም ቅዠት ውስጥ ይከተናል ። ፀሐይ ቢወጣም ሕይወት ዳምና ትታየናለች ። የጨው ውኃ እንደ ጠጣ ምክር ፣ መዝሙር ፣ ማጽናኛ አይጠቅመንም ፣ አያረካንም ። ማደንዘዣው እንደ ለቀቀው ታማሚ መልሰን ከብዙ ምክር በኋላ እናቃስታለን ።

ሰማዩ ጥቁር ፣ ምድሩ እሾህ ፣ ዙሪያው ይሰቀል ባይ ፣ ሜዳው የሚሳለቅብን መስሎ ይሰማናል ። እስከ ዛሬ የምናውቃቸው ክፉዎች በፊት ለፊታችን ይመጡብናል ። እነርሱ ምንም ሆነው አያውቁም ፣ እኛ ግን የሕማም ሰው ነን ብለን ለራሳችን እንነግረዋለን ። ድንገት ታክሲ ውስጥ አብሮን የተቀመጠውን “ይቅር በለኝ” ብለን ያልበደልነውንና የማናውቀውን ሰው ይቅርታ ለመጠየቅ ይዳዳናል ። ሰማይና ምድር የተቀየሙ ሲመስለን ይህ ዝቅታ ይጫጫነናል ። የጠበቅነው ያ ጥሩ ቀን እየሸሸ ነው ። ከሰማይ የተጣለ ወደ ጥልቁ ሲወረወር ሰማይ ጥሎኝ እየጠፋ ነው ብሎ ያስባል ። እውነቱ ግን እርሱ ከሰማይ እየራቀ ነው ። ሰማይ በስፍራው ነው ፣ እርሱ ወደ ጥልቅ እየወረደ ነው ። አለመኖር በጣም ይሰማናል ። የንብረት ኑዛዜ ለማድረግ እንከጅላለን ። ግን ለማን እንናዘዛለን ። እኛ እኮ የተተውን ሰዎች ነን ። እኛ ከሌለን ያለን ነገር እንደ ፍጥርጥሩ ይውጣ ። ድርሻችን መሞት ነው ። ሌላውም የራሱን ድርሻ ይወጣ ። ከቀናት በፊት ታላቅ ስኬት ነበረን ፣ መልሶ ታላቅ ውድቀት ይመጣብናል ። አዎ የመጣል ስሜት ከባድ ነው ። ይህ ሁሉ ግን ስሜት ነው ፣ አዎ ስሜት ነው ። በንኖ የሚጠፋ ። አባረን ብንይዘው የአረፋ ኳስ የሆነው ስሜት ነው ። እውነቱ ግን “አልጥልህም ከቶም አልተውህም” ያለው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ነው (ዕብ. 13 ፡ 5) ።

ድምፅ ይሰማል ። ከሰማይ የሚንቆረቆር ዜማ ያለው የሚመስል መልእክት እየመጣ ነው ። ይህን ድምፅ ማንም እንዲያቋርጥብን አንፈልግም ። ሰዎች ለእኛ ቃል ያጠራቸው ፣ ያጽናናቸው ያቆሰሉን ፣ የጠበቅናቸው የከዱን ነንና አዎ ይህን ድምፅ ምንም እንዳይጋፋን እንፈልጋለን ። ያለን ተስፋ አንድ ነው ፣ እርሱም ከሰማይ ነው ። ተመስገን ድምፁ ተሰማ ። እኛ እየተናገርን ቢሆንም “የእኔን ድምፅ ስሙና እናንተ ትቀጥላላችሁ” በሚል ማባበል መጣ ።

“አሁን የማዕበል ጊዜ ነው ፣ የጸናውን ዓምድ እኔን ክርስቶስን ያዙ ። ሞገድ የማይበረታታበት መርከብ ትፈልጋላችሁ እኔ ኢየሱስ ነኝ ፣ በእምነት ተሳፈሩብኝ ። ሰዎች የራሳቸው ችግር አላቸውና ከችግር እንዲያወጡአችሁ አትከጅሉ ። ግን የሰው ድምፅ በራሱ መድኃኒት ነው ። በሩን ከፍታችሁ ውጡ ፣ ፀሐይ እያበራ ነው ፤ ምድር አሁንም ሰፊ ፣ ሰማይም ከፍ ያለ ነው ። ያላችሁን ከሌላችሁ ነገር አትተምኑ ። ካላችሁና ከሌላችሁም ፣ ከጉድለትም ከሙላትም በላይ እኔ አማኑኤል አለሁላችሁ ።”

ኡፍ ተመስገን ! ይህ ድምፅህ ያስገምግም ፣ እንደ መብረቅ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያብራ ። በአንድ ጊዜ ለወገን ይሰማ ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ