የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የመፈጸም ጭካኔ

                 የካቲት 7 2004 ዓ.ም.
             ‹‹. . . መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫውን ጨርሼአለሁ . . .››
                                                          / 2 ጢሞ. 4፣7/፡፡
በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ውድድር ታሪክ ውስጥ የተፈጸመና ብዙዎችን ያስገረመ አንድ ታሪክ አለ፡፡  የታሪኩ ባለቤት ኢትዮጵያዊ አለመሆኑን ባውቅም፤ታሪኩን ካነበብኩበት ጊዜ አንፃር ግን ስሙንም  ሆነ አገሩን አላስታውስም፡፡ ታሪኩ አውነት መሆኑን ግን አውቃለሁ፡፡- ይኸውም ከአንድ አፍሪካዊት ሀገር በሄደ የማራቶን ተወዳዳሪ የተፈጸመ አስደናቂ ድርጊት ነው፡፡ ይሄ ተወዳዳሪ ውድድሩን የጀመረው እንደ ማንኛውም ተወዳዳሪ በልቡ የአሸናፊነትን ተስፋ ሰንቆና በዓለም መድረክ ላይ የሀገሩን ሰንደቅ ዓላማ በክብር ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ለማድረግ ነበር፡፡ የ42 ኪሎ ሜትሩን ውድድር ቢጀምርም ከአየሩ ሞቃታማነት የተነሣ  ውድድሩን በጀመረው ፍጥነት በመቀጠል ከተፎካካሪዎቹ  እኩል መሄድ አልቻለም ነበር፡፡
ከተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች በኋላ እጅግ ድካም እየተጫጫነውና እግሩም ከሙቀቱ እየተነሣ መላላጥና ቀስ በቀስም መድማት ይጀምራል፣ ይህ ሯጭ ምንም እንኳ አሸናፊ መሆን ባልችልም ውድድሩን ግን እስከ መጨረሻዋ ኪሎ ሜትር ሮጬ መፈጸም ይገባኛል በማለት ለራሱ ቃል በመግባት ቀስ እያለ በመሮጥ የውድድሩ ተሳታፊዎች ሩጫውን ካጠናቀቁ ከበርካታ ደቂቃዎች በኋላ የመጨረሻ በመሆን  እጅግ ደክሞትና እግሮቹ ደም እያዘነቡ ወደ ውድድሩ ማጠቃለያ እስታዲየም በላብ ርሶ ደረሰ፡፡ በስታዲየሙ ሜዳ ላይም ጥቂት እረፍት ለማግኘት ሲል በጀርባው ተጋደመ፡፡

ወደ ውድድሩ ማጠናቀቂያ ስታዲየም ሲደርስ እጅግ ድካም የሚታይበትንና እግሮቹ በደም የራሱትን ያን አፍሪካዊ ሯጭ በመገረም ሲያስተውሉት የነበሩ በስፍራው የነበሩ ጋዜጠኞችና ታዛቢዎች እንዲህ በማለት ተናገሩት፡- ‹‹ውድድሩ ከተፈጸመ በርካታ ደቂቃዎች አልፈዋል ይሄን ሁሉ ከምትደክም እግሮችህም እንዲህ ከሚቆሳስሉ ለምን ውድድሩን ብዙዎቹ እንደሚያደርጉት አቋርጠህ አልወጣህም›› በማለት ጠየቁት፡፡ ይህ ተወዳዳሪም የመለሰላቸው መልስ ጋዜጠኞቹንና በዛ ስፍራ የነበሩትን ሁሉ ያስደነቀ ነበር፡-
‹‹ሀገሬ›› አለ ይሄ በብዙ ድካምና ትዕግሥት በመጨረስ ከሰዓታት በኋላ የ42 ኪሎ ሜትሩን ውድድር ያጠናቀቀው ሯጭ፡- ‹‹ሀገሬ ወደዚህ ታላቅ የኦሎምፒክ ውድድር የላከችኝ ሩጫውን እንድጀምር ብቻ ሳይሆን እንዳጠናቅቅም አደራ ሰጥታኝ ነው፣ ውጤቴ ምንም ይሁን ምንም ይሄን ሩጫ በብዙ ድካምና ልፋት እግሮቼ ቆሳስለው፣ ከውድድሩ ፍጻሜ በኋላ ሰዓታትን እንኳ ዘግይቼ ብጨርስም ውድድሩን በማጠናቀቄ ልዩ ኩራት ነው የሚሰማኝ፣ ሀገሬ የጣለችብኝ አደራም እንደተወጣሁ ነው የማምነው›› በማለት ለጋዜጠኞቹ መልስ ሰጠ፡፡
የዚህን ተወዳዳሪ ምላሽ የሰሙ ጋዜጠኞች የዚህን አፍሪካዊ ሯጭ ትዕግሥትና ጽናት በማድነቅ ወሬውን ለዓለም የመገናኛ ብዙኃን ሁሉ በማሰራጨት የዚህን ሰው ስምና ዝና እንዲናኝ አደረጉት፡፡ በእርግጥም የሀገሩ አደራ የማራቶን ውድድሩ ጀማሪ ከተሳካለትም ባለ ድል እንዲሆን ብቻ ሳይሆን የውድድሩ ፈፃሚም እንዲሆን ጭምር የሚለውን ቃል ለመፈጸምም ጭምር ሲል ነው በውድድሩ ተሳታፊ የሆነው ይሄ የኦሎምፒክ የማራቶን ሯጭ፡፡
በዚህ ምድራዊ በሆነ የሩጫ ውድድር፣ ሽልማቱም ሆነ ክብሩና ዝናው በዚህ ምድር ለሚቀር የኦሎምፒክ ማራቶን ይሄ አፍሪካዊ ሯጭ የከፈለውን መሥዋዕትነትና ያሳየውን ትዕግሥትና ጽናት እንዲሁም ሀገሩ ሩጫውን እንዲጀምር ብቻ ሳይሆን እንዲጨርስም ጭምር አደራ ተሰጥቶት እንደተላከና ያንንም አደራ በመውጣት ለሀገሩና ለቃሉ ታማኝ ለመሆን ያሳየውን ታላቅ ታማኝነት ስንመለከት፤ ለመሆኑ ለማያልፈው ርስትና መንግሥት ወራሾች ለመሆን የምንሮጥ ክርስቲያኖች ምን ያህል ትጋትና ትዕግሥት እያሳየን ነው? የሚለውን ጥያቄ ሁላችንም ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡ በአጀብና በሞቅታ የክርስትናን ጉዞ የጀመሩት ብዙዎች በተለያየ ምክንያት የሩጫው ጀማሪ እንጂ ፈጻሚ መሆን ባልቻሉበት ሁናቴ ውድድሩን በማቋርጥ ጥለው የሚወጡበትን በርካታ አጋጣሚዎች ትናንት ነበሩ፣ ዛሬም አሉ፡፡
አንዳንዶች እንደ ዴማስ የዚህ ዓለም ክብርና ውበት ማርኳቸው፣ አንዳንዶች በክርስትና ሩጫቸው የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች መታገሥ አቅቷቸው፣ በብዙ ዝለትና ድካም የተነሣ ተስፋ ቆርጠው፣ ሌሎች ደግሞ አቋራጭ መንገድ ፈልገው፣ የሚበዙቱ ደግሞ የእምነታቸው ፈጻሚና ራስ የሆነውን ኢየሱስን ለማየት ዓይናቸውን ወደ ላይ ወደ አርያም ማቅናት አቅቷቸው በምድረ በዳ በክፉ እባብ ተነድፈው ቁስለኞች ሆነው ከሩጫቸው ተገተዋል፡፡
ሌሎችም በእናቴ መቀነት አደናቀፈኝና በውኃ ቀጠነ ጥቃቅኑን ነገር ሁሉ ትልቅ አድርገው በማየት፣ የወንድሞቻቸውንና የእህቶቻቸውን ድካምና በደል መሸከም አቅቷቸው በፍቅር ባልሆነ የሞተ እምነት፣ በነተበ ተስፋ የሚሮጡ የሚመስሉ ግና ወደ ሩጫው ፍጻሜ የሚያደርሰውን መንገድ የሳቱ፣ ከንቱ ሯጮች የሆኑበት. . . በመንፈስ ጀምረው በሥጋ ለመጨረስ የሚዳክሩ ሯጮች የክርስትናውን ሜዳ ያጥለቀለቁበት የሚመስልበት ጊዜ ላይ ያለን መስሎ ይሰማኛል . . .፡፡ እኛስ ከየትኛው ሯጮች መካከል እንደሆንን  ራሳችንን መመርመር አይገባን ይሆን? በትክክልስ በሩጫው መንገድ ላይ ነን? . . . በምንሮጠውስ ሰማያዊ ሩጫ ዓይኖቻችንን ያቀናነው በማን ላይ ይሆን?
  
የዕብራውያን ጸሐፊ የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ታላቅ የክርስትና ሩጫ አስመልክቶ ክርስቲያኖችን እንዲህ በማለት ይመክራል፡-
እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎ የሚከበንን ኃጢአት ሁሉ አስወግደን፣ የእምነታችንንም ራስና ፈፃሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፣ እሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ቀኝ ዙፋን ተቀምጦአልና፡፡  ዕብ. 12፣1-2፡፡
ከእኛ በፊት የነበሩ የቀደሙት ሕያው የእግዚአብሔር ምስክሮች በምን ዓይነት ጽናትና ተጋድሎ ሩጫቸውን ፈጽመው በሰማይ ሆነው፤ ዛሬ ደግሞ የእኛን ድል ለማየት በመጓጓት ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ፣ ወደ ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም፣ በደስታም ወደተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፣ በሰማያት ወደ ተጻፉ ወደ በኩራት ማኅበር፣ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፣ ፍጹማንም ወደሆኑ የጻድቃን መንፈሶች፣ የአዲስ ኪዳንም መካከለኛ፣ የእምነታቸውና የእምነታችን ራስና ፈጻሚ ወደሚሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እስክንደርስ በታላቅ ጉጉት ሆነው የሚጠብቁ እነዚህ ሩጫቸውን በታላቅ ተጋድሎ የፈጸሙ ቅዱሳን እንደ ደመና በዙሪያችን ከበውን እንዳሉ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ይነግረናል፡፡
ስለዚህም ሐዋርያው በመልእክቱ እንደሚያሳስበን ‹‹ኃጢአትን እና ቶሎ የሚከበንን ሸክም ሁሉ አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት ሆነን የእምነታችንን ራስና ፈጻሚ የሆነውን ኢየሱስን በመመልከት ሩጫችንን መሮጥ ይገባናል፡፡›› የተጠራነው የክርስትናን ሩጫ እንድንጀምር ብቻ ሳይሆን እንድንፈጽመውም ጭምር ነው፡፡ እግዚአብሔርም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መንግሥቱ የጠራን መልካሙን ሩጫ በመሮጥ የድል ባለቤቶች በመሆን ከአምላካችንና ከአባታችን ዘንድ የተዘጋጀልንን የድል አክሊል እንድንቀበል ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሩጫውን አጠናቆ ከዚህ ምድር መለየቱ እንደደረሰና ወደ ሰማያዊ ቤቱ የሚሄድበት ቀን እንደተቃረበ ለወንጌል ልጁ ለጢሞቴዎስ በጻፈለት የመጨረሻ መልእክቱ፡-
በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፣ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል፡፡ መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፣ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፣ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፣ ደግሞም መገለጡን ለሚጠባበቁ ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡ 2 ጢሞ.4፣ 6-8፡፡
የሰማያዊው ሩጫ ተካፋዮች የሆንን ክርስቲያኖች ሁሉ የጀመርነውን ይህንን መልካም ሩጫ ለመፈጸም እንችል ዘንድ ትዕግሥትና ጽናት በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ በዚህ በዘመን መጨረሻ ያለን አገልጋዮችስ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- ‹‹መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫውን ፈጽሜአለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ…፡፡›› ብለን በክርስቶስ ወንጌል የምናገለግላቸውን የመንፈስ ልጆቻችንን የምናበረታታበትና ሩጫቸውን ይፈጽሙ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ ፍቅርና ርኅራኄ ደፍረን እንዲህ ወደምንልበት የመንፈስ ልዕልና ላይ ደርሰን ይሆን?… ተገልጋዮችስ የአባቶቻቸውን ተምሳሌት በመከተል መልካሙን ሩጫ ለመሮጥ ምን ያህል መንፈሳዊ ወኔና ዝግጅት አለን?
ዛሬ ዛሬ በአብዛኛው የምንታዘበው የክርስትናው ሩጫ መስቀል አልባ፣ ፍጻሜው በሰማይ ሳይሆን በዚሁ ምድር ላይ የሆነ፣ ምድራዊ ሹመትን እና ሽልማትን ግብ ያደረገ፣ በመንፈስ ተጀምሮ በሥጋ የሚያልቅ ፍጻሜው ኢየሱስ ክርስቶስ ያልሆነበትን ሩጫ በመሮጥ ክብርና ሽልማታችንን በዚሁ ምድር ላይ ለመቀበል የወሰንን፣ በዚህም ተደላደልን የተቀመጥን ነው የምንመስለው፡፡ ዓይኖቻችንን በሰማይ ወዳለው የእምነታችን ራስና ፈጻሚ ወደሆነው ወደ ኢየሱስ በማንሣት ታላቁን ሩጫችንን ልንሮጥ ይገባናል፡፡ በታላቅ ትዕግሥትና ጽናት፣ በመልካም ገድል ሩጫቸውን በድል ያጠናቀቁትን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ምስክሮች የሆኑትን አባቶቻችንን ምሳሌ በማድረግ ሩጫችንን በትዕግሥት እንሩጥ… ዘመኑ ቀርቦአል፣ የትንሣኤው ጌታ በደጅ ነው ያለው… ማራናታ! ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና!
                                              ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ