የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሚበላና የሚወራ አይታጣም

 ባልና ሚስቱ ወደ ገበያ ሲወጡ አህያ ላይ ተሳፍረው ይጓዛሉ ። ሰዎችም አዩአቸውና፡- “እንዴት ሁለቱም አህያ ላይ ተቀምጠው ይሄዳሉ ? ለአህያዋ አያስቡም ወይ ?” አሉአቸው ። እነርሱም ይህን ትችት ሰምተው ባል በአህያዋ ተቀምጦ ሚስት በእግሯ ልትሄድ ተስማሙና ጉዞ ጀመሩ ። ያዩአቸው ሰዎች ግን፡- “ምን ዓይነት ጨካኝ ቢሆን ነው ሚስቱን በእግር እንድትሄድ የሚያደርጋት ?” አሉ ። ባልም፡- “እኔ ልውረድና አንቺ በአህያዋ ላይ ተቀምጠሽ እንጓዝ” አለ ። ሚስቲቱም በአህያዋ ላይ ተቀምጣ ባልዋ በእግሩ መጓዝ ጀመረ ። ያዩአቸው ሰዎችም፡- “ምን ዓይነት ዘመን መጣ ? ሚስት ባልን ማክበር ተወች” አሉአቸው ። በዚህ ጊዜ ባልና ሚስት ግራ ተጋቡና ሁለቱም በእግራቸው እየተጓዙ አህያዋን መንዳት ጀመሩ ። በዚህ ጊዜ ያዩአቸው ሰዎች፡- “እንዴት ያሉ ሞኞች ናቸው ? በአህያ መገልገል እንኳ አያውቁም” አሏቸው ። 

ሰነፎችና አላዋቂዎች ተናብበው የሚሠሩ ናቸው ። አንዱ ላንዱም አሳልፎ ይሰጣል ። ስንፍና ወደ አለማወቅ ያደርሳል ። ማወቅ ዋጋ የሚያስከፍል ፣ ከብዙ ምርጫዎች የሚሻለውን መምረጥ የሚጠይቅ ነው ። ሺህ ንባብ ፣ ሺህ ትምህርት ባለበት በዚህ ዘመን የሚሻለውን ያልመረጠ የወሬ እንጂ የእውቀት አባት መሆን አይችልም ። ገበያ ውስጥ ብዙ ዓይነት ምርት አለ ። ይሁንና ሁሉንም ይዘን አንገባም ። የሚያስፈልገንን ፣ አቅማችን የሚችለውንና ያማረንን ገዝተን እንገባለን ። ብዙ ዓይነት እውቀትና መረጃ ባለበት ዘመን የሚያስፈልገውን ፣ የሚችለውንና ያማረውን መምረጥ ካልቻለ ዘመኑን በፍለጋ ይጨርሳል ። ሰነፎች በማያስፈልጋቸው ነገር ጊዜ የሚያጠፉ ፣ የሚያስፈልጋቸው ጋ ሲደርሱ ጊዜ የሚያጡ ናቸው ። ለማያስፈልገው ነገር የነበረው ጉልበት ለሚያስፈልገው ነገር መዋል ይችላል ። ለወሬ አቅም አጠረኝ ያላሉ ሰዎች ፣ ለእውቀት ግን አቅም አጠረኝ ይላሉ ። እውቀት ለመኖር በምንመገበው ምግብ የምንሰበስበው ሀብት ነው ። ለትምህርት ተብሎ የሚበላ ልዩ ምግብ የለም ። እውቀት በዚህ ዘመን በመዳፋችን ላይ የተቀመጠ ነው ። ባለመምረጣችን ግን ተጎድተናል ። 

ስንፍና ቀላል ነገር አይደለም ። ስንፍና አምላክ የለም የሚያሰኝ የክህደት መገኛ ነው ። ስንፍና ንዋይ ስለመሰብሰብ እንጂ ስለሞት የማያስብ ነው ። /መዝ. 52፡1፤ ሉቃ. 12፡20/ ስንፍና ስለሌሎች አስተያየት ሲሰጥ የሚውል ነው ። 

የተሰጠን ጊዜና አቅም ለሚመለከተን ነገር ብቻ የሚበቃ ነው ። የሚመለከተን ነገርና የማስፈልግበት ቦታ የቱ ነው ? ካልን በቂ አቅምና ጊዜ አለን ። ሰዎችን ለመተቸት አደራ የተቀበልን መስሎን ከተሰማን ስህተት ነው ። በሕሊና ፣ በዜግነት ፣ በመንፈሳዊነት ግዴታ ግን የማናልፋቸው ነገሮች ፣ ፍርድ ልንሰጥባቸው የሚገቡ ጭካኔዎች ፣ ትክክል አይደለም የምንልባቸው ሚዛናዊነቶች በጣም ያስፈልጉናል ። የራሳችንን ኑሮ ረስተን ግን የግለሰቦችን ጓዳ ስንተች መዋል ተገቢ አይደለም ። ባለቤቱ ፈቅዶ ችግሩን ነቅሰን እንድንነግረው ምክር ካልጠየቀን በቀር ሲዘልፉ መዋል ፣ አግድም አደግነትን የሚገልጥ እንጂ መልካም ሰብእናን የሚያሳይ አይደለም ። 

ከቤታችን መውጣት ስንጀምር የሚቀበለን ነገር ቢኖር ትችት ነው ። ትችትን የሚፈራ ሰው በሩን ቆልፎ መቀመጥ አለበት ። በሩን ከፍቶ የወጣ ሰው ይተቻል ። ላስተምር ያለ በነፍስ ነጋዴዎች ፣ ልጻፍ ያለ ማንበብ በማይወዱ ሰዎች ወይም ንባባቸውን ለቁማር በሚጠቀሙ ሰዎች ፣ ላገልግል ያለ በሕዝብ በሚገለገሉ ወገኖች ይተቻል ። ትችት ፈርተው ዝም ያሉ ምሑራን ፣ መስጠት ያቆሙ ሀብታሞች ፣ የማይወስኑ ባለሥልጣኖች ብዙ ናቸው ። በእግዚአብሔር ዘንድ ተምሮ ዝም የሚል ፣ ሀብት እያለው የሚነፍግ ፣ ሥልጣን እያለው የማይወስን የተጠሉ ናቸው  ። የምንሄድበትን ወስነን መውጣትና የሚመጣውንም ዋጋ መተመን ከቻልን ትችቶች መንገድ ላይ አያስቀሩንም ። ተቺዎች ባያስቆሙ ማዘግየት ይወዳሉ ። ተቺዎች እንደ እነርሱ የቆመ ሰው ማብዛት ዓላማቸው ነው ። የሚሄዱና የሚሠሩ ሰዎችን ሲያዩ የሕሊና ወቀሳ ስለሚያመጡባቸው እነርሱን በማስቆም ዕረፍት ለማግኘት ይፈልጋሉ ። ተቺዎች ራሳቸውን በብዙ ማጽናኛ የሚመግቡ ናቸው ። የሚናገር መሳሳቱ ፣ የሚራመድ መደናቀፉ አይቀርም ። ተቺዎች ግን እንኳን አልተናገርኩ ብለው በአዋቂዎች ፣ እንኳን አልተራመድኩ ብለው በወደቁት ይስቃሉ ። እውቀት ከሌለው ጨዋነት መሳሳት ያለበት የእውቀት ንግግር ይሻላል ። ብዙ ጊዜ ለመሳሳት የማይደፍር ተመራማሪ መሆን አይችልም ። ቤተ ሙከራ የምንለው ስፍራ የመሳሳቻ ስፍራ ነው ። ብዙ ስህተቶች ግን አንድ እውነትን ያወጣሉ ። በዕድሜ እየበሰልን ስንመጣ መውደቃችንን እየወደድነው እንመጣለን ። 

በጉዞአችን ላይ ተቺዎች አራት ዓይነት ትችቶች ይሰነዝሩብናል ። የመጀመሪያው ትችት የርኅራኄ ጥያቄ ያለበት ነው ። ያገለግላሉ ግን ደመወዝ ይላሉ ፣ ይጽፋሉ ግን ውድ ገንዘብ ይጠይቃሉ ። እንዴት ለሕዝቡ አያዝኑም ? የሚል የርኅራኄ ጥያቄ ያነሣሉ ። መንፈሳዊ ሰዎች ሳሉ እንዴት ውድ ቤት ፣ እንዴት ውድ ልብስ ያስፈልጋቸዋል ፣ ብዙ ድሆች አሉ አይደለም ወይ ? በማለት በርኅራኄ ስም ጥያቄ ለማሥነሣት ይሞክራሉ ። ይሁዳ ለጌታ በተረጨው ውድ ሽቱ ተቃዋሚ ነበረ ። ተቃውሞው ግን መንፈሳዊ ካባ የለበሰ ነበር ። “ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው? አለ።” ዮሐ. 12፡5 ። መጽሐፉ ግን ሲመልስ እንዲህ ይላል፡- “ይህንም የተናገረ ሌባ ስለ ነበረ ነው እንጂ ለድሆች ተገድዶላቸው አይደለም፤ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለ ነበረ ነው።” 

እነዚህ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ሲሠራ ዋናው ሰው መሠራት አለበት የሚሉ ፣ ቀለም ሲቀባ እኛ አገራችን በሰማይ ነው የሚሉ ፣ ለአገልጋዮች በጎ ሲደረግ ዓለም ዓለም ሸተተ የሚሉ ናቸው ። እግዚአብሔር ግን ልብን የሚመዝን አምላክ ነው ። 

በጉዞአችን ላይ የሚነሣው ሁለተኛው ትችት የፍቅር ጥያቄ ያለበት ነው ። ሁሉን በእኩል አያዩም ፣ ላለውና ለሌለው እኩል አይደርሱም ፣ የቀደመውን ሰው ኋላ በመጣ ሰው ይለውጡታል ። ቅድሚያ ለመጣው ክብር የላቸውም  የሚሉ ትችቶች ይነሣሉ ። ይህ የፍቅር ጥያቄ ያለበት የሚመስል ነው ። ነገር ግን የማያድጉ ፣ ከአንቀልባ የማይወርዱ ፣ ሁልጊዜ እሹሩሩ ከሚወዱ ሰዎች የሚመነጭ ትችት ነው ። የቱንም ያህል ጠንቃቃ ብንሆን ከሰዎች ነቀፋ ነጻ አንሆንም ። እነዚህ ሰዎችም የቀደሙ የሚሏቸውን ሰዎች ያስተባብሩና የመብት ጥያቄ መጠየቅ ይጀምራሉ ። ባንቀጥልም አፈራርሰን እንሄዳለን ብለው ይነሣሉ ። ለእኔ ያልሆነ ለማንም አይሁን ብለው በቅናት ጥላሸት ይቀባሉ ። 

በጉዞአችን ወይም በራእይ መንገዳችን ላይ የሚገጥመን ሦስተኛው ትችት የክብር ነው ። የበላዮቻቸውን አያከብሩም ፣ በእውቀት ለሚበልጡአቸው ንቀት አለባቸው ፣ ያሳደጉአቸውን የሚገድሉ ናቸው ፣ ለመንፈሳዊነት ዋጋ አይሰጡም ፣ ባለሥልጣናትን ይንቃሉ የሚል ክብር መሳይ ያለበት ትችት ይነሣል ። ይህ ትችት ከምሑራንና አቅም ካላቸው ባለሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የሚውል ነው ። ጌታን ይሰሙ ከነበሩ ሕዝቦች መካከል ጥቂቶቹ ከአፉ ቃል ለቅመው ለአይሁድ የሃይማኖት አባቶች ፣ ለሮማ የፖለቲካ መሪዎች ለመክሰስ ነበር ። ይህኛው ትችት ስደት ፣ መከራና ሞት ለመጋበዝ የሚነሣሣ ነው ።

በመንገዳችን ላይ የሚገጥመን አራተኛው ትችት የሞኝነት ስድብ ያለበት ነው

። ከፈተናውና ከመከራው የተነሣ ሁሉን ትተን ስንቀመጥ ፣ ይስፋችሁ ብለን ወንበሩን ጥለን ስንሄድ ፣ አንደበታችንን ለዝምታ ፣ እጆቻችንን ጽሑፍ በቃኝ ለማለት አሳልፈን ስንሰጥ ምን ዓይነት ሞኞች ናቸው ? ይሉናል ። አባቶች ስንቱን ታግሠው ነው ለክብር የበቁት በማለት ግብ የለሽ ሰው መሆናችንን ለማወጅ ይፈልጋሉ ። ጥለው ወደቁ ፣ አስክደው ካዱ ፣ ደብድበው ተመረሩ ፣ አውግዘው ወጡ እያሉ የሚተቹ ሰዎች አሉ ። ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ እንደሚጮኽ የእኛን ጩኸት እየቀሙ የሚጮኹ አሉ ። 

አዎ ሰው የሚለውን አያጣምና መንገዳችንን መሄድ ፣ እግዚአብሔር ያሳየንን መፈጸም ይገባናል ። ከዚያ በተቃራኒ በዘመናዊው ዓለም ድርጅቴን ተቹልኝ ተብለው የሚከፈላቸው ፣ ጉድለትን አጥንተው የሚያቀርቡ ተቋማት አሉ ። ጉድለትን በፍቅርና ከመፍትሔው ጋር የሚያሳውቅ ካለ ልንከፍለው ይገባል ። ያላየነውን ላሳዩን ዓይኖችም ምስጋና ማቅረብ አለብን ። 

ጌታ ሆይ የጥሪህን ድምፅ እንጂ የተቺዎችን ትችት እንዳልሰማ እርዳኝ ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 27 ቀን 2012 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ