የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሚወዱህ አሜን ይላሉ

ከሚያሳቅቀው ጨለማ ወደሚያስደንቀው ብርሃን ፣ ከጨካኝ ገዥ ወደ በጎነትህ ግብር ፣ አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ከተባለበት ባርነት የንጉሥ ካህናት ወደ መሆን ጌትነት የመለስከን ፣ ባሕረ ሞትን አሻግረህ መዝገብ ሕይወትን ያወረስከን የጸጋ ሁሉ አምላክ በዚህ ቀን ምስጋና እናቀርብልሃለን ። ከቆረጡ ጋር ቆርጠህ ፣ ከጨከኑ ጋር ለማዳን የጨከንህ ፣ የማንኖርበትን ቤት ስንሠራ ፣ ወደማንኖርበት ከተማ ስንገሰግስ ሀገረ ሕይወትን ፣ የጽዮን ተራራን ያሳየኸን ፣ ብቅ ጥልቅ ብንልም ዛሬም የምታበረታን አንተ ነህ ። ከቻሉት ጋር ኅብረት ፣ ካልቻሉት ጋር ርቀት የሌለብህ ፣ ሁሉን በፍቅር ዓይንህ የምታይ ፣ በውብ ዓይኖችህ ውብ አድርገህ የምታየን አንተ ነህ ።

በችሎታው የሚረዳህ ፣ ባለው ነገር የሚደግፍህ ማንም የለም ። የሰማዩ ሰማይ ፣ የጠባቂዎች ጠባቂ ፣ የዳኞች ዳኛ ፣ የባለ መብቶች ባለ መብት ፣ ሁሉ ያንተ ሳለ የእኔ እያለ የሚጣላውን ወገን የምታይ ፣ የጀመርከው የሚፈጸምልህ ፣ የፈጸምከው የሚዋብልህ ፣ ያስዋብከው የሚኖርልህ ፣ በበሩ ለገቡ ሰፊ መስክ ፣ ቃልህን ለሚጠብቁ ጽኑ እረኛ ፣ ፍርድህን ፍቅርህ የማይሽረው ፣ ፍቅርህን ፍርድህ የማያስቀረው ፣ የሕዝብ ሁሉ አባት ፣ የዚህ ሁሉ ወፈ ሰማይ መጋቢ ፣ እኛ ስንቆጥረው የበዛብንን የሰው ዘር አንተ እንደ አንድ ልጅ የምታይ ፣ መልቀም ለሚወዱ ጎተራ በረከት የምትሰጥ ፣ ቃርሚያ ለወጡ እርሻውን ባለ ርስት አድርገህ የምትሰጥ ፣ ረጅሙን ጉዞ በአንድ እርምጃ የምታስጀምር ፣ ለይቶ የወደደህን በቃል ኪዳን የምታከብር ፣ ራሱን ለሰጠህ ዘሩን የምትባርክ ፣ ጎረቤት ለሌለው ጎረቤቱ ፣ ከተማው ላደመበት ወገኑ ፣ ወልዶ መሐን ለሆነው እውነተኛ ልጁ ፣ ትዳር ለሌለው የቤቱ ራስ ፣ አቅም ሲደክም ምርኩዝ ፣ ሲመሽ መብራት ፣ ዓይን ሲከዳ መሪ አንተ ነህና የቀኑን ምስጋና ፣ የሰንበትን ዘለላ ላንተ እናቀርባለን ። የሚወዱህ ሁሉ አሜን ይላሉ ። አሜን ያለህም በአማን በረከት ይባረካል ። አሜን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 24 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ