የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሚያኮራ ሰንሰለት

“ስለዚህም አሕዛብ ስለ ሆናችሁ ስለ እናንተ የክርስቶስ ኢየሱስ እስር የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ለእግዚአብሔር እንበረከካለሁ ።” ኤፌ. 3፡1 ።

በአገራችን ብዙ ሰው የደነበረ ስሜት ውስጥ ያለ ይመስላል ። በመደናገርም የሚወስነው ውሳኔ ራሱንና የአገርን ሚዛን የሚነካ ይሆናል ። በመደናገር አገር ለቅቆ ስደት ትርፉ ይሆናል ። በመደናገር ቤት ንብረቱን ሸጦ የትላንት ባለቤት ፣ የዛሬ ተንከራታች ይሆናል ። በመደናገር ከወዳጆቹና ከዘመዶቹ ጋር ይጋጫል ። በመደናገር አእምሮውን ለጭንቀት ፣ አቅሉን ለነፋሱ አሳልፎ ይሰጣል ። እምነት ማለት ከጊዜ ፣ ከቦታና ከሁኔታ በላይ ማሰብ መቻል ነው ። ባለማመን ወራት ፍርሃት ያጠላል ። ከነፍስ ዋስትና የዕቃ ዋስትና መፈለግ ይታያል ። የኤፌሶን ምእመናን በአረማዊነት ዘመናቸው የተደናገሩ ነበሩ ፣ አሁን ግን በክርስቶስ የዘላለም ኑሮአቸውን ስላሳመሩት ዕረፍት ውስጥ ናቸው ። የተደናገረ ወገን ድምፁን ከፍ አድርጎ ለመናገር ሁሉ ነጭ ለባሽ/ሰላይ ወይም ጆሮ ጠቢ መስሎ ይታየዋል ። የገዛ ግድግዳው እየቀረጸው ስለሚመስለው የልቡን መናገር አይችልም ። ሲራመድም ያለ አባራሪ ውስጡ እያባረረው በፍርሃት ነው ። የራሱን ነገር በነጻነት መጠቀም እያቃተው ፣ የበዪ ተመልካች ፣ በቤቱ አፍሮ እንግዳው የሚጋብዘው ይሆናል ። ሁሉም እንቅስቃሴና ንግግር የሕይወት ዋጋ የሚያስከፍለው እየመሰለው ይሸበራል ። ቀን በአሳቡ ፣ ሌሊት በሕልሙ አባራሪ ያሳድደዋል ። ከአሳቡ መለስ ፣ ከቅዠት ንቅት ሲል ይጸልያል ፡- “ጌታ ሆይ እባክህ ይቅር በለኝ” ይላል ። ይጠብቀኛል የሚለውን ፖሊስ ሲፈራ ፣ የገዛ መንግሥቱ የባዕድ መንግሥት ያህል እንኳ ዋስትና የማይሰጥ ሲሆንበት “በርሬ የት አርፋለሁ?” እያለ ይዋትታል ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ ሁሉ መቅበዝበዝ ያድናል ። የኤፌሶን ምእመናን ያለማመን ሕይወታቸው ይህን ይመስል ነበር ። እኛም ያመንን እንደማያምኑ ስንሆን እንደገና ማመን ፣ እንደገና “እንዳምንህ እርዳኝ” ብለን መጸለይ ይገባናል ።

ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈው በሮም እስር ቤት ውስጥ ሁኖ ነው ። አንዳንድ ሰዎች መታሰራቸውን ሰው ባይሰማ ይመርጣሉ ። መታሰራቸውና በሠሩት ቤት መኖር አለመቻላቸው እያሳፈራቸው ድብቅ ቢሆንላቸው ይመኛሉ። ሐዋርያው ግን በእስራቱ ይኮራ ነበር ። ጠጥቶ ሰው በመረበሽ ፣ ሰርቆ በመክበር ፣ ገድሎ በመሰወር አልተጠረጠረም ። በእውነቱ የተከሰሰ ፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት ወኅኒ የወረደ ነው ። እርሱ ያስተማራቸው ብዙ ሺህ ሕዝቦች ጨዋ በመሆናቸው እንኳ ፖሊስን ከጥበቃ ፣ አገርን ከሁከት ፣ ትዳርን ከመፍረስ አድነዋል ። በማኅበራዊ ሰላምና ዋስትና ላይ ባመጣው ተጽእኖ መሸለም ይገባው ነበር ። ዓለም ግን ምንም ብትሰለጥን የክርስቶስ እውነትን በተመለከተ ፍርደ-ገምድል ናት ።

ዛሬ በሮም የሃይማኖት ከተማና ግዛት “ቫቲካን” በሚል ስያሜ ይገኛል ። በእያንዳንድ መታጠፊያ ድንቅ ካቴድራሎች ይታያሉ ። እነዚህ ሁሉ የእስረኛው የጳውሎስ ፍሬዎች ናቸው ። እኛ አደባባይ እንድንወጣ እስር የወረዱልን አባቶች አሉ ። እርካሽ ሕይወት ሳይሆን ዋጋ የተከፈለበት ኑሮ አለን ። እንደ አውስትራሊያ ባሉ አገሮች ሰዎችን ሰብስቦ የሃይማኖት ትምህርት የሚያስተምር ማኅበረሰቡን እየለወጠ ነውና እገዛ ይደረግለታል ። የፖሊስና የደኅንነት ወጪን ስለቀነሱ ሰባኪዎችና ወንጌላውያን ሊከፈላቸው ይገባ ነበር ። የማኅበረሰብ አንቂዎች የሚባሉ ሕዝቡን በደንብ ባስተኙበት ዘመን ወንጌላውያን አባቶችን መንግሥት ማገዝ ያስፈልገው ነበር ። በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የሃይማኖት አባት የትራፊክ መብራት ቢጥስ አይከሰስም ። ነፍስ ለማዳን እየሄደ ነው ተብሎ ይታሰባል ። ሃይማኖት በገነነባት በእኛ አገር የእሳት አደጋ መኪና ያህል እንኳ የጳጳስ መኪና አይከበርባትም ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ