መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የሚያውቁኝን አሰንብታቸው

የትምህርቱ ርዕስ | የሚያውቁኝን አሰንብታቸው

በማላውቃቸውና በማያውቀኝ መካከል መኖር ከባድ ነው ። ብዙ ኖሮ ባይተዋር መሆን የሚገርም ነው። ሊያውቅህ የማይፈልግ ሁልጊዜ እንደተዋወቀህ ይኖራል።  እባክህ ጌታ የሚያውቁኝን አሰንብታቸው። የኋላ ወዳጅ የፊቱን አያውቅም፣ ቢቀርብም በፍርሃት እንጂ በፍቅር አይሆንም። እነዚያን ስወለድ ያዩኝን፣ ማርያም ማርያም ብለው የተማጸኑልኝን እባክህ አሰንብታቸው። አባት እናቴ ባይኖሩ ምትክ እንዳደርጋቸው እነዚያን የጠዋት ወዳጆቼን ክርስቶስ ሆይ እባክህ በሞቴ አቆያቸው። ሰፈሩ ጭር እንዳይል፣ መንደሩ ሞገስ እንዳያጥረው እነዚያን ደጋግ እባክህ አቆያቸው።

ስድህ መሬት ላይ ተቀምጠው ያገዙኝን፣ እንድራመድ እጆቿን የያዙትን፣ የእናቴ ጡት ሲነጥፍ አጥብተው ያሳደጉኝን እነዚያን ሩኅሩሆች እባክህ ዘመን ጨምርላቸው። “ልጄን አትምታብኝ” ብለው ከአባቴ ጋር የታገሉትን፣ “እርሱን የነኩ እንደሆነ እቀየመዎታለሁ” ብለው እናቴን ያስፈራሩትን እነዚያን በቀሚሳቸው የተደበቅሁባቸውን እናቶች እባክህ አቆይልኝ። የዛሬውን ጉድ እንዲያረክሱልኝ፣ የጠብ ያለ የሚለውን ዘመን እንዲያስረሱኝ እነዚያን ቡሩካን እባክህ አትንካብኝ።

ሊሸጡት ካስቀመጡት ጥቢኛ ላይ “ብላ” ብለው የሰጡኝን፣ ከልጃቸው እኩል አንጥፈው ያስተኙኝን፣ አዝለው ያሳደጉኝን፣ ወላጆቿ እስኪመጡ ለሳምንት ለወር የያዙኝን እነዚያን የአደራ ልኮች እባክህ አሰንብትልኝ። ከድሀ የተወለደ ቶሎ አያገኝም፣ ድሀ ምን ትሠራለህ? እንጂ ምን ትበላለህ? የሚለው የለም። እጄ እስኪሞላ ሞት እንዳይነጥቅብኝ እነዚያን ባለ ውለታዎቼን እባክህ አቆይልኝ። ለሰው ሁሉ “ልጄ ነው የሚመስለኝ” ብለው የሚያወሩትን ፣ ሲያዩኝ እንባ እንባ የሚላቸውን እነዚያን የኢትዮጵያ ወላጆች እባክህ አሰንብታቸው። ከሌላቸው ላይ የሰጡኝን፣ የሩቅ ዘመድ ሳይደርስ የደረሱልኝን፣ የማይወደደውን ማንነቴን የወደዱትን፣ “እስቲ ና ቆሻሻህን ልጥረግልህ” ያሉትን እነዚያን አይፀየፌ እባክህ አቆይልኝ። የአንዱ ቀን መንገድ ዓመት እየፈጀብኝ፣ ለሌላው የቀለለ ለእኔ ከባድ እየሆነብኝ እንዳላረፍድና እንዳላጣቸው እባክህ ጌታዬ አሰንብታቸው። ምን ቢያገኙ አብሮ ከተቸገረ ጋር ካልበሉት አይጣፍጥም። እንጀራዬን ከመራራ ቅጠል ጋር እንዳልበላው እባክህ አምላኬ እነዚያን የረሀቤን መድኃኒት አሰንብታቸው ።

ዛሬ ሲመሸ ከቤት ይወጣል። “አልመሸም ወይ ? ወደ ቤትህ ግባ” የሚሉኝን የምሽቱን አውሬ ቀድመው ያዩልኝን እባክህ አሰንብትልኝ። ዛሬ ልጅ ቢያጠፋም የሚቆጣው፣ ቢስት የሚመልሰው የለም። ልጅ ሁሉ የእኔ ነው ብለሁ ያምኑ የነበሩትን እነዚያን ሆደ ሰፊዎች እባክህ አሰንብትልኝ። ልፈልጋቸው ስሄድ ሁሉም የሉም። በራቸውን ሳንኳኳ ቤቱ ተሽጧል ይሉኛል። አንድ ወላጅ ያቆየውን ቤት አሥር ልጅ መጠበቅ እንዴት ያቅተዋል? ገንዘብን እንጂ ክብርን የማያውቁ ልጆችን እነዚያ ደጋግ እንዴት ወለዱ? የአገሬ ወላጅ በጣር አሳድጎ ለማረፍ ለምን አልታደለም? የልጁን ሬሳ በአደባባይ ወድቆ እንዳላየ ትራፊ ልጁ ሲዳር ለምን አልቆየም?

እባክህን ጌታዬ የሚያውቁኝን አሰንብታቸው። አነሰ በዛ ብዬ እንዳልዘገይባቸው፣ ዕድሉ አምልጦኝ ቁጭቱ እንዳይጎዳኝ እኔንም አፍጥነኝ። ዓይን ነው ዘመዱ ለመተያየት አፍጥነኝ። ምን ይዤ ሲሉ ነው ተቆራርጠው የሚቀሩት እባክህ ዓይኔን ግለጥልኝ። በሙሉ ዓይን አላየውም የሚሉትን፣ ልጄን ሰስቼ እንዳልበላው ብለው እንትፍ የሚሉትን፣ ንጉሥ እንደመጣ የሚሯሯጡልኝን ፣ እነዚያን የወላጅ ምትኮች እባክህ አሰንብትልኝ። የቤት ልጅ አልነበርኩም፣ ሁሉ ጠባቂዬ ነበርና የሀገር ልጅ ነበርሁ፡፡ ሁሉ ቤት አድራለሁ፣ ሁሉ ቤት እበላለሁ ፣ አባት እናቶቼ ሺህዎች ነበሩ። እንዲህ አድርገው አገር ያቆዩትን እነዚያን ደጎች አሰንብታቸው።

አንተ ስትወለድ እንዲህ ተፈጸመ እያሉ የሚያወሩትን የሚያውቁኝን አሰንብታቸው። ማነው ሳይሉ ለወደቀው ሰው ደረታቸውን መትተው እንጀራ የሚሰጡትን፣ ዘሩ ምንድነው ? ሳይሉ ላዩት ሬሳ የሚያለቅሱትን እነዚያን አዋቂዎች ፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን አሰንብታቸው። ስታመም የሚደነግጡ ፣ ስሞት የሚያለቅሱ እነርሱ ናቸውና ዋጋዬን የሚያውቁትን እነዚያን ጽንፍ የለሽ እባክህ አቆያቸው። ማለፋቸውን እፈራዋለሁ። በአፍሪካ ምድር ከወጣት ሞት በላይ የአዋቂ፣ የትልቅ ሰው ፣ የአረጋዊ ፣ የወላጅ  ሞት ያስጨንቃል። ትልቅ ቤተ መጻሕፍት ይቃጠላል።  እነርሱ ያለቁ  ቀን ኑሮ ቁስ እንጂ ጣዕሙን ያጣል። ልጅም ታሽጎ ያድጋል። ጓደኝነት በገንዘብ ይለወጣል። ለሞተ የሚያለቅስ ይጠፋል። ሰው ቁጥር ሆኖ ስንት ሰው ሞተ?  ይባላል።

አንተ የምወድህ ጌታዬ የሚያውቁኝን አሰንብታቸው!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጳ ጒሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ