የሰው ልጆች የማደግ ፍላጎት አላቸው ። በደግ መታወቅ ያቃታቸው ሰዎች በክፋት ታዋቂ የሚሆኑት ይህ የማደግ ፍላጎት ስላላቸውና መንገዱ ስለ ጠፋቸው ነው ። የሰው ልጅ በማያቋርጥ ዕድገት ውስጥ ነው ። በሥራ ካላደገ በስንፍና እያደገ ይመጣል ። በክብር ካላደገ በውርደት እያደገ ይመጣል ። በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ ሞገስ የሚያሰጥ ዕድገት ሁለንተናዊ መሆን አለበት ። የሰው ልጅ አካላዊ ፣ ሥነ ልቡናዊ ፣ ሞራላዊ ፣ ማኅበራዊ ዕድገት ያስፈልገዋል ። አካላዊ ዕድገቱ በምግብ ፣ በስፖርት ፣ በሥራ ይገኛል ። ሥነ ልቡናዊ ብርታቱ የቀደሙትን የሃይማኖትና የአገር ጀግኖችን በማወቅ ፣ ክብሩን በመረዳት ፣ እውቀትን በመሰብሰብ ይገኛል ። ሞራላዊ ዕድገቱ ከመሥዋዕትነት ልብ የሚመነጭ ሲሆን ለሌሎች መኖር የሚያስደስተው ማንነት ነው ። ማኅበራዊ ዕድገቱ በዙሪያው ላሉትና እየመጡ ላሉት ትውልዶች አሻራ ማስቀመጡ ነው ።
“የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንዲሉ የሚያጠግበውም እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል ማለት ነው ። የልጆችን ፍላጎት ፣ የወጣቶችን ክህሎት መገምገም አለብን ። የምንፈልገውን ሳይሆን የሚያስፈልጋቸውን መስጠት ያሻል ። እኛ ያቃተንን ነገር እነርሱ እንዲፈጽሙት መፈለግ ፣ ደመላሽ እያሉ መሰየም ተገቢ አይደለም ። እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ እንዲገለጡ ማበረታታት አለብን ። ታዲያ የሚያድጉ ሰዎች ምልክት ምንድነው ( ማለት ያስፈልገናል ። እነዚህን ሰዎች ለመርዳት ያመቸናልና ምልክቱን ማወቅ አለብን ። እነዚህ የማደግ ምልክቶች ያሉት ሰውም በተስፋ ደስ ሊለው ጅምሩን መልካም ፍጻሜ ሊሰጠው ይገባል ። የሚያድጉ ሰዎች፡-
ጥበብን ይፈልጋሉ
ዋዛ ፈዛዛ ነገር የጥበብ ጠላት ነው ። ሁልጊዜ አድናቂ መሆንም ተደናቂ ሥራ ከመሥራት ያግዳል። አያቴ እንዲህ አድርጓል እያሉ መኩራራትም ሞቶ መኖርን ያመጣል ። እኛ ሌሎችን ለመተረክ አልመጣንም ፣ የራሳችንን ሩጫ ለመፈጸም ወደዚህ ምድር ተቀላቅለናል ። የቀደሙት አርአያዎቻችን እንጂ ሕይወታችን ሊሆኑ አይችሉም ። ታላቁ እስክንድር ዓለምን የገዛው ከፈላስፎች ባገኘው ጥበብ ተመርቶ ነው ። እርሱ ከሞተ ኋላ እንኳ ለ1ሺህ ዓመታት ተጽእኖ ነበረው ። ዛሬም አሻራውን ማጥፋት አልተቻለም ። በዓለም ላይ የሰለጠነው ሥልጣኑ ሲያበቃ፣ ያስተዋወቀው የግሪክ ባሕል ግን አሁን ድረስ አለ ። ስለ ሰው ፣ ስለ ጥበብ ፣ ስለ ዲሞክራሲ ፣ ዓለምን ስለ መናቅ ያሉት ፍልስፍናዎች ከግሪክ ጓዳ የሚቀዱ ናቸው ። የዓለማችን የጥበብ ፣ የአመራር ፣ የሕክምና ቋንቋዎች የግሪክ ናቸው ። ጥበብ ሞተን እንድንኖር ታደርጋለች ። በጥበብ ዱላ ብንመታ ሰዎች አየወደዱን ይማራሉ ። የሚያድግ ሰው ጥበብን ይፈልጋል ። ራሱ እግዚአብሔር ጥበብ ነውና ወደ እርሱ የሚቀርቡ ጥበበኞች ናቸው ። ጥበብ በጸሎትም እንደሚገኝ ከንጉሥ ሰሎሞን ታሪክ እንረዳለን ፣ ያዕቆብም ጥበብ የጎደለው እንዲለምን ያሳስባል (ያዕ. 1፡5) ። ጥበብ እንደ ኩል አጥርቶ ማየትን ይሰጣል ። ጥበብ ሁለት ጊዜ ማየት ነው ። ጥበብ ከመምህራን ፣ ከሽማግሌዎች ይገኛል ። ገንዘብ ከሚያወርስ አባት ጥበብ የሚያወርስ መምህር ይበልጣል ። ዳግም ልደት በፍልስፍናም ፣ በመንፈሳዊ ጓዳም አስፈላጊ ነው ። በመጀመሪያው ልደት ብቻ ይህንንም ያኛውንም ዓለም ማየት አይቻልም ።
የሚያድጉ ሰዎች እውቀትን ይፈልጋሉ ። የአበላልን ሳይሆን ሌሎችን የሚያበሉበትን ጥበብ ይሻሉ ። በመቆረስ ውስጥ ያለውን ደስታ ያጣጥማሉ ። ማስታወሻ ይይዛሉ ፣ ከለማኝም ከንጉሥም የሚነገረውን ቃል አይንቁም ። ጆሮዎቻቸው የከበሩ ቃላትን ማጣጣም ይችላሉ ። የቋንቋን ስርገት ፣ የቅኔን መንገድ ለማወቅ ከበሰሉት ጋር መዋል ይገባል ። እኩያ የእውቀት እኩያም ነውና አዳጊ ሰው የሚበልጠውን መፈለግና ማገልገል አለበት ። ጥበበኞች ከቃላቸው ይልቅ ሕይወታቸው አስተማሪ ስለሆነ በጥበበኞች ሰላማዊ ጎጆ ማደር ይገባል ። በዚያ ጮማ የለም ፣ ሰላም ግን አለ ፤ በዚያ የሐር ምንጫፍ የለም ፣ እንቅልፍ ግን አለ ። የሚያድግ ሰው የሚበልጡትን የሚፈልግ ፣ ተግሣጽን የማይንቅ ነው ። ትልቅ ትልቅ ነው ። ክቡር ያከብራል ። የዱርዬ ዕድር ግን በውርደት ይጠናቀቃል ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 29 ቀን 2018 ዓ.ም.