መምሰል
መምሰል ማስመሰል አይደለም ። ክርስቲያን ሁሉ ክርስቶስን እንዲመስል ተጠርቷል ። ክርስቶስን መሆን አይችልም ፣ መምሰል እንዲችል ግን ጥሪ ደርሶታል ። ክርስትና ማለት ልክ እንደ ክርስቶስ በዓለም ላይ መገለጥ ነው ። እርሱ በረገጠው የእግር ፈለግ ላይ አስተካክሎ ማሳረፍ ፣ በጻፈው ጽሕፈት ላይ ማድመቅ የአንድ አማኝ መንፈሳዊ ግዴታ ነው ። መምሰል አርአያ ባደረጉት መምህር ፣ ጀግና ፣ ጸሐፊ መመሰጥ ነው ። አነጋገሬ እንደ እርሱ ፣ አጻጻፌ ልክ እንደ ብዕሩ ነው ወይ ( ብሎ ጓጉቶ መጠየቅ ነው ። የዚያን ትልቅ ሰው ወንበር ለመውረስ መምሰል ትልቅ መወጣጫ ነው ። አባቶች ለልጆቻቸው የሚያወርሱት ስለሚመስሏቸው ነው ። ጀግኖችና አዋቂዎችም የሚመስሉአቸውን ሲያገኙ ያለ ስስት ያወርሳሉ ። ሞትን የሚበቀሉት በደቀ መዝሙር መሆኑን ይረዳሉ ። ለመምሰል የዚያን ሰው አቋም ፣ አኗኗር ፣ ውሳኔ ፣ ቍርጠኛነት ፣ የዕድገቱን ምሥጢር ማወቅ ያስፈልጋል ። የሚያድጉ ሰዎች ምልክት መምሰል ነው ።
ምንም እንኳ ወጣትነት ይህን ልበስ የሚል አምሮት ቢኖረውም የሚያድጉ ሰዎች ግን ወጣትነትም ቀሪ መሆኑን አውቀው የሚያከብሩትን ሰው በአለባበስም ይመስላሉ ። እጅ ጽሕፈታቸው የእርሱን እንዲመስል ይፈልጋሉ ። ልጆች በልጅነታቸው የሚወዱትና ትልቅ አድርገው የሚስሉትን ሰው ከኋላ ከኋላው እየሄዱ ልክ እንደ እርሱ ይራመዳሉ ። የሚያነክስ ከሆነ ማንከስንም ይወርሳሉ ። መምሰል መልካሙን መውሰድ ነው ። የምናደንቀው ሰው የራሱ የሆነ ብርታትና ድካም አለው ። ድካሙ ለእርሱ የጸሎት ፣ የንስሐና የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ የሚጠይቅበት ደወሉ ነው ። ከእርሱ መውሰድ የሚገባን መልካሙን ነው ። በአጠቃላይ ግንኙነታችን ከራእዩ እንጂ ከግል ሕይወቱ ጋር መሆን የለበትም ።
ትልቅ ቦታ የደረሱ ሰዎች የራሳቸው የሆነ የሕይወት ዕንቈ ነበራቸው ።
አመጋገባቸው
አመጋገባቸው የተመጠነ ነው ። መብል የምንበላው ብቻ ሳይሆን የሚበላንም ነው ። ለመኖር ምግብ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ሞትንም የሚያፋጥነው ልክ የሌለው አመጋገብ ነው ። ትልቅ ቦታ የደረሱ ሰዎች የማሰብና የመሥራት አቅማቸውን ላለማጣት ብዙ አይጠግቡም ፣ አይራቡምም ።
የሰዓት አጠቃቀማቸው
በጊዜ ወደ መኝታቸው የሚሄዱና ማልደው ከእንቅልፍ የሚነሡ ሰዎች ትልቅ ቦታ የሚደርሱ ናቸው ። ትልልቆች ሁሉ ይህ ልማድ አላቸው ። ከቀኑ የማለዳውን ሰዓት በትክክል ሲሠሩበት ከሰዓት በኋላውን ራሳቸውን ለማሳረፍና ተጨማሪ እውቀትን ለመቅሰም ያውሉታል ።
እንቅስቃሴ
በአብዛኛው የእግር ጉዞ ማድረግ ለማሰላሰል ፣ ለድርሰት ፣ ከራስ ጋር ለማውራት ፣ ለድብርት በጣም ይረዳል ። ትልልቅ ሰዎች ይህ ልማድ አላቸው ። ከተፈጥሮ ጋርም ግንኙነት ያደርጋሉ ። አበቦችን መንከባከብ ፣ አካባቢውን ማጽዳት እፎይታ ይሰጣቸዋል ። ማኅበራዊ ኑሮአቸውም አግባብ ባለው መንገድ ያከናውናሉ ። ያመኑበትን ፍቅር ተግባራዊ ለማድረግ ማኅበረሰቡ መኖር አለበት ።
የሚያድጉ ሰዎች ምልክት መምሰል ነው ። አዋቂዎችን ጥያቄ ይጠይቃሉ ። ለመማርም ዝቅ ይላሉ ። ገና የማያውቁት ነገር እንዳለ ያምናሉ ። የሕይወትን ፍቺ ለማወቅ ገና አይጠብቁም ፣ ኑሮን ከኖሩት ሰዎች ይማራሉ ። የታላላቅ ሰዎችን ግንዛቤ ፣ መልካምነት እያሰሱ ለመምሰል ይሞክራሉ ። ትምህርት የሚገኘው ጊዜ በመስጠትና አዋቂዎችን በማገልገል ነው ። የሚያድጉ ሰዎች ከእኩዮቻቸው ይልቅ ትልልቆችን ጓደኛ ያደርጋሉ ። እነርሱንም በጉልበት በማገዝ የነፍስ ጥማታቸውን ያረካሉ ። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ራሳቸውን አያራቁቱም ። ፎቶአቸውን አይለቁም ። ለወደፊት ትልቅነታቸው እየተዘጋጁ ስለሆነ በጥንቃቄ ይጓዛሉ ። የጊዜ አጠቃቀማቸው ውብ ነው። ዋዛ ፈዛዛ ነገርን አይወዱም ፣ ጓደኛ አያበዙም !
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም