“እንቍራሪቶች ከበሬ የበለጠ ሊጮኹ ይችላሉ ። ነገር ግን እርሻ መሬት ላይ ማረሻ መሳብ ወይም መጥመቂያ መሣሪያ ማሽከርከር አይችሉም ። ቆዳቸውም ጫማ ለመሥራት አያገለግልም ።” /ካህሊል ጂብራን/
ሰው የሚሠራን አይወድም ። ከበሬ ይልቅ አንበሳን ያከብራል ፣ ከአህያ ይልቅ የሜዳ አህያን ፎቶ ያነሣል ። በሬ ክብሩን ያጣው በማገልገሉ ፣ አህያም የቆሸሸችው በሰው ሸክም መሆኑን ማንም አይገነዘብም ። ይቅር ባዩን ሰው በሬ ፣ ቻዩን አህያ ብሎ መስደብ የተለመደ ነው ። በሬ ብለው ከሰደቡን ትልቅ ምርቃት ነው ። በሕይወትም በሞትም የምናገለግል ነን ማለት ነው ። በሬ በቁሙ ያርሳል ፣ መጓጓዣ ይሆናል ፣ ዘር ይሰጣል ፣ በተዘዋዋሪ ወተት ያስገኛል ። ሙቶ ሥጋው ይበላል ፣ ቆዳው ልብስና ጫማ ይሆናል ። ኩሱ እንኳ ማገዶ ይሆናል ። አህያ ተብሎ ቢሰደብ የሚከፋው ካለ አላዋቂ ነው ። አህያ ትዕግሥተኛ ፣ ሽቶ ለመሸከም ብላ የቆሸሸች ፣ እህል ለማድረስ ብላ ዱቄት የመሰለች ፣ እየሄደች ስትደበደብ ፣ እየሠራች ስትሰደብ የቻለች ፣ ለውለታዋ ሌላ ጭነት ሲጫንባት የማትከፋ ፣ ትንሽ ተቀብላ ብዙ የምትሰጥ ፣ ሥልጣኔዎች ሳይመጡ የሰውን ድካም ያገዘች ናት ። ከሁሉ በላይ አህያ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የተሸከመች ፣ የሰላም ማብሰሪያ ፣ የጥንት ነገሥታት የምሥራች መንገሪያ ናት ። ለሚሠራ ሰው ክብር ስለሌለን ወረኞችን እየፈለፈልን ነው ። መዋሸትን እንደ ሥልጣኔ ስለቆጠርን ቀጣፊዎችን እያበዛን ነው ። የወደድነውን ሰው እጅ እግሩን አጣምሮ ቢኖርም መቀለብ አይሰለቸንም ፤ ከጠላነው ደግሞ ተራራ አቀበት ቢወጣ ፣ ሸለቆ ቁልቁለት ወርዶ ቢሠራ አንፈልገውም ። ሚዛናችን ሐሰተኛ ፣ ፍርዳችንም የተዋረደ እየሆነ ነው ። እግዚአብሔር ሁሉን ቢፈጥርም ሰዎች ካልሠሩ ሁሉም ነገር እየራቃቸው ይመጣል ። ለስንፍና ሁሉም ነገር ጠረፍ ፣ ለሥራ ግን ዳሩ መሐል ነው ። ሥራን የሚያከብር ፣ ሠራተኞችን የሚሸልም አገር ከፍታው አይደረስበትም ። ጠላቱም አሻቅቦ እያየው ሲታክት ይኖራል ። የማይሠራ ሕዝብ ዘረፋን ፣ እየገደለ የማክሰኞ ገዳይ ፣ የሐሙስ ገዳይ ተብሎ ሲወደስ መኖር የሚፈልግ ነው ። የዱር አራዊትን የጨረሰ ሰነፍ ሰው ነው ። የዱር ዛፎችን የጨረሰ ታካች ሰው ነው ። ቁጭ ብሎ መመገብን የሚወድ ፣ በሌላው ደም ወተት የሚጠጣ ገብር ሀካይ የተባለው ሰው ነው ።
በሬ ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው ወደ ማረጃው ስፍራ ሲወስዱት እየተቻኮለ የሚሄድ ነው ። ይህ ሁሉ ታታሪነቱ እውቀት ያንሰዋል ። ሥራ እንጂ ሴራ አያውቅም ። በሬ ካራጁ ይውላል እንዲሉ ።
አያ በሬ ሆይ ፣
ሞኙ በሬ ሆይ ፣
ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ ፣
እልም ካለው ገደል ወደቅህብን ወይ ?
አንዳንድ ቀና ሰዎች ፣ ሥራ ሥራ የሚሉ ታታሪዎች ፣ እኔ ደግሞ ምን ጠላት አለብኝ የሚሉ ሁሉ ወዳጄ ነው ባዮች ፣ በእጃቸው ቅቤውን እያንጠባጠቡ ካላጎረሱ የሚከፋቸው ደጎች ፣ ወድቀው ለመማር የሚኖሩ ዘመን አባካኞች የክፉዎች ዒላማ ይሆናሉ ። በቁማቸው ጉልበታቸውን ይጠቀሙባቸዋል ። ወደ መታረጃቸውም ቄራ ፣ ወደ መውደቂያቸው ገደል ይነዱአቸዋል ። ከሞቱ በኋላም እነዚህ ጠላቶቻቸው አይተኙላቸውም ። ብዙ ክፉ አማካሪዎች ፣ ወዳጅ መስለው ወዳጅ የሚያሳጡ ምጽዋተኞች ፣ የዘላለሙን ክደው ለዕለት ያደሩ ምንደኞች ፣ ቀን ከሌሊት ላበላቸው ሳይቀር ጉድጓድ የሚቆፍሩ የማይለምዱ አውሬዎች ፣ እሳት ለኩሰው ሌላው ሲቃጠል ለመሞቅ የሚከጅሉ ሕሊና ቢሶች የአገር መሪዎችን ፣ የቀረቡአቸውን ወዳጆች ፣ ማኅበራዊ ኑሮን ያተራምሳሉ ። ታታሪነትን እንደ በሬ መያዝ ብቻ ሳይሆን እንደ እባብም ብልህነትን መያዝ ይገባል ። ፍጥረታት እግዚአብሔር እኛን የሚያስተምርበት ክፍሉም ፣ የማስተማሪያ ቁሳቁሱም ናቸው ።
መጮህ የሚችሉ መሥራት የሚችሉ አይደሉም ። ብዙ ኃይል የሚባክነው በአፋችን በኩል ነው ። ብዙ አቅም የሚዳብረውም በጆሮዎቻችን ነው ። ተፈጥሮአችንም አንድ አፍ ፣ ሁለት ጆሮዎች ያሉት ነው ። እንቍራሪቶች ይጮኻሉ ። ድምፃቸው ግን እለቁ ፣ እለቁ የሚል ፣ ሰላም የሚነሣ ነው ። የሚጮኹትም አደባባይ ወጥተው ፣ አትሮኖስ ተደግፈው አይደለም ። በውኃ ውስጥ ሰጥመው ፣ በጭቃ ውስጥ ላቁጠው ፣ በጢሻ ውስጥ ተሸሽገው ነው ። ሲጮኹ የሚውሉ ሰዎች ድምፃቸው ሰላማዊ አይደለም ። የሚረብሽ ወሬ ከሌለ ሥራ ያጣሉ ። ሥራ ሲያጡም የገዛ ወዳጃቸውን ቀደው ይሰፋሉ ። ልፋተኞች እነዚህን ወረኞች እየቀለቡ ቁጭ ብለው እንዲበሉ ያደርጓቸዋል ። የሚጮኹ ሰዎች በኢንተርኔት ጫካ ውስጥ ተሸሽገው እንጂ ገሀድ ወጥተው አይደለም ። ሠርተው ማሳየት አይችሉም ። ለሚሠራ ሰው ግን እንደ ቅንቅን ሆነው ዕረፍት ያሳጣሉ ። በጓዳ ተቀምጠው ስንቱን በረሃ ይሰዳሉ ፣ ከልጆቻቸው ጋር እየተጫወቱ ወላድን መሐን ያደርጋሉ ። ቀዝቃዛ ትኩስ እየተጎነጩ ሌላውን በረሀብ ያስጨርሳሉ ።
እየሠራን ከሆነ ብዙ አንጮኽም ። ምክንያቱም ሥራው ከሚናገረው በላይ መናገር አንችልምና ። የሚጮኽ ሰው መሥራት የማይችል ነው ። በሬ ዝም ብሎ ያርሳል ። እንቍራሪት ግን ብትጮህም ምንም ጥቅም አትሰጥም ። በሬ ሙቶም ቆዳው ጫማና ልብስ ይሆናል ፣ እንቍራሪት ግን ምንም ጥቅም አትሰጥም ። ለፍትሕ የሚጮኹ የተከበሩ ናቸው ። ራሳቸውንም መሥዋዕት የሚያደርጉ ናቸው ። ለሥራ የሚያነቃቁ የተከበሩ ናቸው ። ከፊት ቀድመው የሚያስከትሉን ናቸው ። መልእክት የሌለው ጩኸት የሚጮኹ ፣ የመናገር ግዴታ ያለባቸው እየመሰላቸው በማይመለከታቸው አስተያየት ሲሰጡ የሚውሉ ሰነፎች ናቸው ። አገር በተግባር እንጂ በወሬ አትነሣም።
የብርሃን ጠብታ 18
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም.