የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማታ ጀምበር

 

አቤቱ በዋጋ የገዛኸው የሰው ልጅ በነጻ ሲሞት ዝም አትበል ! መርጦ ሳይወለድ ተመርጦ ለተገደለው ጌታ ሆይ እዘን !

ወዳጄ ሆይ !

ደስታ የሰላም ውጤት ነው ፤ ሰላምም የሚገኘው በእውነተኛ ፍቅር ውስጥ ነው ። ካዘኑት ጋር ካላዘንህ የስብራትህ ቀን ሲመጣ አጽናኝ አታገኝም ። ጭፍን ፍቅርህ ጭፍን ፍርድ እንድትሰጥ ያደርግሃል ። እኔን ካልነካኝ ብለህ ስትቀልድ ሩቅ ያየኸው ቅርብ ይሆናል ። ሰው ሲወድቅ ሰው የሆነ ያዝናል ። በገንዘብ ቁማር የሚጫወትን ስታወግዝ ነፍስ አሲይዞ የሚቆምርን ዝም ካልህ እውነት ትፈርድብሃለች ። 

ወዳጄ ሆይ !

ሙሴ ቀድሞ ያስከተለ መሪ ነው ። በረሃውን አርባ ዓመት ኖሮበት አርባ ዓመት ሕዝቡን በምድረ በዳ መራ ። መሪ ካልቀደመ አለቃ ይሆናል ። የማያስከትል ይነዳል ። ለበጎ ነገር ጎንህን ሳታይ ስትነሣ እግዚአብሔር ይባርክሃል ። መከራን ቀድሞ የሚያሳይህ በዚያ መንገድ እየመጡ ያሉትን እንድትረዳቸው ነው ። ስለምትሄድበት መንገድ የሚነግሩህ አብረውህ የሚጓዙ ሳይሆኑ የሚመለሱት ናቸው ። አዲስ መከራ ያስለፈልፋል ፣ ክለሳው ግን ያስገርማል ፤ ሥለሳው ግን ያስቃል ። አንዳንድ የድሀ ልጅና አንዳንድ የሀብታም ልጅ አይራሩም ። የድሀ ልጅ የማይራራው የሰማውን መከራ ከራሱ የችግር ዘመን ጋር እያነጻጸረ “ይሄማ ቀላል ነው” በማለት ነው ። የሀብታም ልጅ የማይራራው ችግሩ ምን እንደሆነ ስላልገባው ነው ። አንዳንድ ድሀ ይራራል ፣ የእርሱ የጉዳት ዘመኑ ትዝ ይለዋልና ። አንዳንድ የሀብታም ልጅ ይራራል ፣ እርሱ ጋ ትርፍ የሆነው እዚያ ጋ ዋና ሆኗልና ። 

ወዳጄ ሆይ !

አስታርቃለሁ ብለህ ስትሸመግል እንዳትሸነግል ተጠንቀቅ ። እውነት በሌለበት ህርቅ የለም ። ህርቅ የፍቅር ፍርድ ይፈልጋልና ። እግዚአብሔር ችሎን ነበር ፣ እኛ ግን መቻቻል አቃተን ። እግዚአብሔር ከቀሰፈን ራሳችንን የቀሰፍነው ይበዛል ። እግዚአብሔር የሰጠንን እኛ ካልያዝነው እርሱ አይጠብቀውም ። መዛል የጨበጥከውን ያስጥላል ፣ መሰልቸትም ሞተህ እንድትኖር ያደርግሃል ። ዓለም ሰፊ መቃብር የምትሆነው ተስፋ ለቆረጡት ነው ። ተስፋ መቍረጥ ተንቀሳቃሽ ሬሳ ያደርጋል ። ተስፋ የሚደረጉ ነገሮች ስላሉ ሳይሆን እግዚአብሔርን አይቶ ተስፋ ማድረግ እርሱ ትክክለኛው ተስፋ ነው ። ተስፋ አይቶ መናገር ሳይሆን አምኖ መደሰት ነው ። 

ወዳጄ ሆይ !

ግትር ሰው መሆን እውነተኛነት ሳይሆን እኔ ብቻ አውቃለሁ ባይነት ነው ። የሰማኸውን አትካድ ፣ አንድ ቀን ይህ ጆሮህ መስማት ያቆማልና ። ያየኸውን አትካድ ፣ አንድ ቀን ይህ ዓይን ይፈስሳልና ። አባት ሆነህ ሩኅሩኅ ካልሆንህ ልጅ አለኝ ብለህ አትናገር ። የምታስተምረው ሳይኖርህ አስተማሪ ፣ የምትሰጠው ሳይኖርህ አባት አትሁን ። በጉባዔ ቅዱስ የተባለ መልሶ ርኩስ ይባላል ። በሰማይ ቅዱስ የተባለ ግን እውነተኛ ቅዱስ ሆኖ ይኖራል ። የድጋፍ ድምፅ ቢኖርህም መሞትህ አይቀርም ። የታመመ እንጂ የሞተ አይጠየቅም  ። 

ወዳጄ ሆይ !

ተቀምጠህ ካየኸው ሁሉም ሰው ትልቅ ፣ አንተ ግን ትንሽ የሆንህ ይመስልሃል ። ስትቆም አንተም ትልቅ መሆንህን ትረዳለህ ። ስትራመድም ሰዎች ከደረሱበት ትደርሳለህ ። የተስፋ ቃል ያሻግራልና በክፉ ቀን ለራስህ ንገረው ፣ ቀን ለከፋባቸውም ንገራቸው ። ማጽናናት መጽናናት ነው ። የሰማይ ደጅ ማለት የድሆች ሆድ ነው ። የልዑሎች ልዑል የሆነውን አምላክ ይዘህ አትፍራ ። እግዚአብሔርን አምነው የሰጡህን አደራ መካድ በምድር በሰማይ ስደተኛ መሆን ነው ። እጅግ የተጠየፉ ሰባት ሰዎች አሉ  ። እነርሱም፡- ትዳራቸውን ለገንዘብ የሚለውጡ ፣ ጉቦ በልተው ፍርድ የሚያጣምሙ ፣ ወልደው የሚረሱ ፣ በሐሰት የሚመሰክሩ ፣ በሰው ደም የሚቀልዱ ፣ በጽድቅ ጀምረው በኃጢአት የሚፈጽሙ ፣ ተቀብለው የማያመሰግኑ ናቸው ። 

ወዳጄ ሆይ !

ጥልቁን ያላየ ምጥቀት ላይ ቢወጣ እንደ ቀላል ይቆጥረዋል ። የሁሉም ነገር መነሻም ያ እየመሰለው አያመሰግንም ። መጨረስ ያልቻሉትን አትውቀስ ፣ አንተ ገና አልጀመርህምና ። የሸመገሉትን አትሳደብ ፣ ትደርስበታለህና ። ልጅነትህን አትውቀስ አትመለስበትምና ። በጥቁር ፀጉርህ ትዝታ አትኑር ፣ ሽበቱን አታጌጥበትምና ። በሚያዝኑት አትሳለቅ ፣ አንተ ትንሹ ቢደርስብህ ትወድቃለህና ። በሚሰደዱት አትፍረድ ፣ አንዳንዴ አገር ከሲኦል ይከፋልና ። በባዕድ አትቀየም ፣ ወገንህ እየገደለህ ነውና ። ወጣቶችን ኰናኝ አትሁን የሰጠሃቸው የለምና ። 

ወዳጄ ሆይ !

ሕግን እንዲያስከብር የተቀመጠ ድርሻው ሕግ ማስከበር እንጂ መታገሥ አይደለም ። የሚታገሥ የተበደለ ሲሆን የሚፈርድ መንግሥት ነው ። የሙሴ መሪነትን የአሮን ክህነት ይረዳዋል ። የአሮን ክህነት በሙሴ መሪነት ቅርጽ ይይዛል ። ሙሴ የሌላቸው አሮኖች ወርቅ አምላኪዎች ናቸው ፤ አሮን የሌላቸው ሙሴዎች የተስፋይቱን ምድር ተመኝተው የማያዩአት ናቸው ። ትላንት በሠራኸው መልካም ሥራ ብቻ ከኮራህ ወደፊት መራመድህ ይቀራል ። ሙሴ ስለፈርዖን አንድም ቀን አላወራም ። ፈርዖን ሞቶ እግዚአብሔር ሕያው አምላክ ሆኖለታልና ። 

ወዳጄ ሆይ !

እያንዳንዱ ቀንን የሚኖሩ በሽተኛና ንጉሥ ናቸው ። እነዚህ በዓመት ሳይሆን በየዕለቱ ልደታቸውን ያከብራሉ ። ቀኑ ዋጋ ያለው ጦርነት ላለበት ሰው ነው ። ዓመፅ እንዳይነሣ አድርገህ ሥራ እንጂ ዓመፅን ለማብረድ አትሥራ ። ጦርነትን የምታስቀረው ሁልጊዜ ጦርነት እንዳለ ሆነህ ስትኖር ነው ። 

አቤቱ በዋጋ የገዛኸው የሰው ልጅ በነጻ ሲሞት ዝም አትበል ! መርጦ ሳይወለድ ተመርጦ ለተገደለው ጌታ ሆይ እዘን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ