መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የማትጠፋ ስማችን

የትምህርቱ ርዕስ | የማትጠፋ ስማችን

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ምስጋናህ እንዴት ይዘመራል? ውለታህ በምን ቃል ይገለጣል? ብቸኝነት እንዳይሰማን በአማኑኤል ስምህ መጣህ፣ ሞት እንዳያስገብረን ኢየሱስ የሚለው ስምህ ተገለጠልን፣ ከሹመት የተሻርን መስሎ እንዳይሰማን ክርስቶስ መሆንህ ተሰበከልን፣ በምን አቅሜ መሥዋዕት ላምጣ እንዳንል እነሆ የእግዚአብሔር በግ ብሎ ዮሐንስ ጠቆመን፣ ዕድሌ ዝግትግት አለ ስንል በሩ እኔ ነኝ አልከን፣ ምንደኛ ደመወዝተኛ በዝብዞ ጨረሰን ብለን ዓለምን ስንከጅል የበጎች እረኛ እኔ ነኝ አልከን::

መጀመርም መፈጸምም ሲያሳስበን መንገዱ እኔ ነኝ ብለን አረጋጋኸን፣ ታይቶ ጠፊነት ሲያሰጋን ሕይወት ነኝ ብለህ ከከንቱነት አዳንከን፣ ተለያይተን ልንቀር ስንል የማዕዘን ራስ ሆነህ አጋጠምከን፣ የኢየሩሳሌም መቅደስ ሲፈርስ በተዋሕዶህ ከአባትህ ጋር ኅብረት ሰጠኸን ፣ መሥዋዕት የሚያቀርብ አሮን ቢሞት መሥዋዕት የምትሆን የዘላለም ካህን ደረስክልን፣ ጦር አምጪ ነገሥታት ዘር ቢያሳጡን ፣  ንጉሠ  ሰላም ሆነህ ዘር አተረፍክልን ::

አቅማችንን ስንጠራጠር፣  በዙሪያችን ተስፋ ሰጪ ዘመድ  ስናጣ ኤልሻዳይ ነኝ ብለህ የልባችንን ፍርሃት ገሠጽህልን ፣ ሕልም እልም በዝቶ የሚኖር ነገር ስንከጅል ያህዌ  እኔ ነኝ አልከን ፣ አንተ ለራበው እንጀራ፣ ለበረደው ልብስ ነህ። አንተ ቀኑ ለጠረረበት ጥላ፣ ለተጠቃ ጋሻ ነህ። አልባሼ አጉራሼ አንተ ነህ። ዕውር አሞራን ቀላቢ፣ የሞኙ ብልሃት አንተ ነህ። አንተን ጠርቶ ያፈረ፣ አንተን ጥሎ ያፈራ ማንም የለም። ለስሌት ሩቅ ነህ፤ ለእምነት ቅርብ ነህ ። ሕፃናት እያወቁህ ሊቃውንት ያጡሃል። አንተ እጅግ ግልጥ ነህ፣ አንተ እጅግ ስውር ነህ:: የመጨረሻውን መጨረሻ ታውቀዋለህ፣ ጓዳ ሲሟጠጥ ትደርሳለህ። ያስቀመጥከውን አትረሳም፣ የቀባኸውን አታስደፍርም። ያለ አጥር ትጠብቃለህ፣ ያለ ወገን ትከባለህ፣ ያለ መቅረዝ ታበራለህ፣ ያለ መድኃኒት ትፈውሳለህ። ችለህ ማስቻል ልማድህ ነው፣ ከከበሩት ይልቅ ክቡር ነህ። አንተን የማይፈልግ፣ የማታስፈልገውስ ማን አለ? ማሳለፍ ትችላለህና  ይህን  ቀን አሻግረን !

የማትጠፋ ስማችን አንተ ነህ !

ስም ባጣን ቀን ስም በሆነን ስምህ፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አሜን!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ