የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማን ሐዋርያ ነን ?

“የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ” 1ጢሞ. 1፡1
ሐዋርያ ማለት ሂያጅ ፣ ገስጋሽ ፣ መልእክተኛ ማለት ነው ። በምሥጢራዊ ፍቺው ደግሞ በሥልጣን የተላከ ማለት ነው ። ሐዋርያ ንጉሣዊ መልእክትን ፣ የነጻነት ብሥራትን ይዞ ልዩ ልዩ ድንበሮችን ፣ ባሕሎችን ፣ ሕዝቦችን ለማብሠር የሚጓዝ ነው ። ሂያጅ ነው ስንል ዓላማ አድርጎ የሚጓዝ ነው ፤ የተላከ ነው ስንል የሕይወት መልእክትን የያዘ ነው ማለታችን ነው ፤ የሚሄዱ ከርታቶች ፣ የሞት ድምፅ የያዙ መልእክተኞች አሉና ። ሐዋርያነት በጉባዔ የሚሰጥ ሹመት ፣ ለራስ የሚያፈስሱት ቅባት አይደለም ። ሐዋርያነት ትእዛዝ ነው ። የትእዛዙም ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ትእዛዙም ወደ አሕዛብ ሁሉ ሂዶ ወንጌልን መስበክ ነው ። ንጉሣዊ ትእዛዝ ነውና ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ የምንልበት ነው ። 1ቆሮ. 9፡16 ።

በሁሉም ሥርዓት አለሁ የሚሉ ፣ ራሳቸውንም የለውጥ ሐዋርያ ብለው የሚጠሩ ፣ ለአሙቁልኝ የሚጠሩ ፣ የራሳቸው ልቅሶ ባይሆንም ተከፍሎአቸው የሚያስለቅሱ ፣ ደረት ሳይመቱ የሰው ደረት በግጥምና በዜማ የሚያፈርሱ ሰዎችን ዓይናችን ጠግቧል ። የዘመን ሎሌ መሆን የማይሰለቻቸው ፣ ለመጣው ሁሉ የሚያዜሙ አያሌ ተለዋዋጮችን ምድር ተሸክማለች ። የዘመን ሎሌዎች ሲገለበጥ እየተገለበጡ ፣ እንደ እባብ እየተሸለቀቁ ፣ እንደ ንሥር ጠጉራቸውን እያደሱ የሚነሡ ናቸው ። ሐዋርያው “የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ” ብሎ ራሱን ሲጠራ የዘመን ሐዋርያ አይደለሁም ማለቱ ነው ።
የሌሎች ሕይወት እየጠፋ የእነርሱ ደመወዝ ሲቆረጥ የሚያማቸው ፣ በሌሎች ላይ የሚተኮሰው ከባድ መሳሪያን እንደ ቀላል እያዩ እነርሱን የወጋቸውን መርፌ ግን አጋነው የሚያወሩ ሰዎች አሉ ። ዓለም በሱናሚ እየጠፋ እነርሱ ግን እግራቸውን ጭቃ ስለነካው የሚያማርሩ ራስ ተኮር ሰዎች አሉ ። ምን አገኛለሁ እንጂ ምን እሰጣለሁ ? የማይሉ ፣ ማንንም ሰው ተጠቅመው የሚጥሉ ፣ ወላጆቻቸውን ሳይቀር ለጥቅም ብቻ የሚፈልጉ ራስ ወዳዶች እነዚህ የራሳቸው ሐዋርያ ናቸው ። በሄዱበት ሁሉ የሚያወሩት እኔ ፣ እኔ እያሉ ነው ። እነርሱ ያላማሰሉት ወጥ አይጣፍጥም ፣ እነርሱ የሌሉበት ውሳኔ አይጸድቅም ብለው የሚያምኑ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች በመንፈሳዊ ቤት ሲኖሩም አደባባዩን የራሳቸውን ገድል በማውራት ያጣብቡታል ። ለራሳቸው ያላቸው ግምት ከፍ ያለና ፣ ሰይጣን በነፋስ የሞላው ትልቅ ፊኛ ነው ። የቴሌቪዥን መስኮት ባለበት ለመታየት አንገታቸውን የሚያሰልሉ ፣ ካልታዩ የሚሞቱ የሚመስላቸው ናቸው ። ስለ ግል ጥቅም እንጂ ስለ ጋራ ፍቅር ማሰብ እንኳ አይፈቅዱም ። ቀድመው ቦታ መያዝን ፣ ምርጡን ለእኔ ማለትን ተክነዋል ። ንጹሕ ልብስን እንጂ ንጹሕ ልብን ገንዘብ አላደረጉም ። በፈገግታ መሸኘት እንጂ ለሌላው መሥዋዕት መሆንን አይፈቅዱም ። ሁሉንም ነገር በስሌት እንጂ በእምነት ለማድረግ ይቸገራሉ ። እነዚህ ሰዎች ምድርን ያጎሳቁላሉ ። ልባቸውን ለማግኘት የመንፈቅ መንገድ መጓዝ ይጠይቃል ። የራሳቸው ሐዋርያ በመሆናቸው ስለ ራሳቸው አውርተው አይጠግቡም ። በክብራቸው አይደራደሩም ። ትልቅ ነን ብለው ያስባሉ ። የአገር ቁንጮም እንደሚሆኑ ይተነብያሉ ። ዝቅ አላሉምና ጌታ ሊያቀናቸው ይቸገራል ። ትልቅ ናቸውና አምላክ አያዛቸውም ። ቅዱስ ጳውሎስ ራሱን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ሲል የራሴ ሐዋርያ አይደለሁም እያለ ነው ።
አንዳንድ ሰዎች በደስታ የሚውሉት ሰው ፈገግ ካለላቸው ብቻ ነው ። ለማሳቅ ወጥቶ ሰው ያኮረፈበት ቀልደኛ እንደሚጨነቅ እነዚህ ሰዎችም ሰላማቸውን የመሠረቱት በሰዎች ስሜት ላይ ነውና የጠቆሩ ፊቶችን እንደ ጠቆረ ሰማይ ያያሉ ። ምድር ስትከዳቸው እግዚአብሔር እንደሚቀበላቸው ማመን ይቸገራሉ ። ቀትር ሲጨልምም ክርስቶስ እንደማይተዋቸው ይዘነጋሉ ። በዙሪያቸው ያሉት ሰዎች ሲበተኑ ግራ ይጋባሉ ። ስለዚህ ዘወትር የሚያጠኑት ስለ ሰው አያያዝ ነው ። ሰውን ከማጣት እግዚአብሔርን ማጣት ይመርጣሉ ።የሚያገለግሉትም የእግዚአብሔርን አሳብ ሳይሆን የሰዎችን ደስታ ነው ። ሐዋርያው ራሱን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ብሎ ሲጠራ የሰው ሐዋርያ አይደለሁም እያለ ነው ።
“እልህ ምላጭ ያስውጣል” ይባላል ። ተገቢ ግን አይደለም ። ለእልህ እሞታለሁ የሚሉ ብዙዎች ናቸው ። እልህ ሁሉ እውነት አይደለም ። በእልህ ያመኑትን መካድ ፣ በእልህ የካቡትን መናድ ፣ በእልህ ያፈቀሩትን ማርከስ ፣ በእልህ የሾሙትን መሻር የብዙ ሰዎች ጠባይ ነው ። እልህ ቆጥቦ አይጣላም ፣ እስከ መጨረሻው ይጣላል ። እልህ መዋደድ እንዳለ መጣላት ፤ መጣላት እንዳለ መዋደድ መኖሩን ይዘነጋል ። እልህ ቊጣ ያለበት ስሜት ነው ። በእልህ የሚሰብኩ ፣ በእልህ የሚዘምሩ አሉ ። እልህ በረከት የለውምና ቆይቶ ደስተኛ አይደሉም ። እልህ ግን እርካታ አለው ። ክፉ እርካታ ። የእልህ ክፉ እርካታን ከመንፈስ ቅዱስ እርካታ የማይለዩ ሰዎች እየገፉበት ይመጣሉ ። በእልህ አገር ይፈርሳል ። በእልህ ሌቦች ለሹመት ይታጫሉ ። እልህ ሞቼም ላሰቃያቸው ይላልና ጠቡ ከመቃብር ወዲያም ነው ። በእልህ የሚያመነዝሩ ፣ በእልህ በሽተኛ የሆኑ ፣ እንዳናደዱኝ ላናድድ ብለው የተቃጠሉ ብዙ ናቸው። ሐዋርያው ራሱን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ሲል የእልህ ሐዋርያ አይደለሁም ማለቱ ነው ።
እኛስ የማን ሐዋርያ ፣ የማን መልእክተኛ ፣ ምን ይዘን የምንገሰግስ ነን ?
1ጢሞቴዎስ /3/
ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ