የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማዕበሉ አዛዥ

ማቴ. 8፡23-27
ጴጥሮስ ያሰበውን የሚናገር ሰው ነው ። ያሰቡት ሁሉ አይነገርም ፣ ልቡና የሚባል ማጣሪያ ፣ ኅሊና የሚባል መስተዋት አለ እያሉ አብረውት የኖሩ ሁሉ ቢነግሩትም እርሱ ግን “ተፈጥሮን ተመክሮ አያድነውም” እያለ ይተርትባቸዋል እንጂ አይሰማቸውም ነበር ። በርግጥ እርሱ ያሰበውን ቢናገርም ከቅን ልቡ የሚወጣ በመሆኑ የሚያሳዝን ነገር አልነበረውም ። እንደ ልጅ ንጹሕ ነበር ። ልጅ ዙፋን ላይ ወይም መሬት ላይ ቢያስቀምጡትም በሁለቱም ጭንቀት የለበትም ። ጴጥሮስም የሰውን ከፍታና ዝቅታ የናቀ ነበር ። ቀለል አድርጎ መመልከት ዕድሜ ያረዝማል ። መረቦቹን ሲያጥብ አብረውት ለሚሠሩት ሁልጊዜ የሚመክራቸው፡- “በሰዎች የምትጎዱት የጠበቃችሁትን ያህል ነው ። ሰዎች እንዲጎዱአችሁ አትፍቀዱላቸው ። ደክማችሁ ካልጠበቃችሁት የሚጥላችሁ ማንም የለም ። በዛሬው ዘመን እንኳን ሰው ልብም እየከዳ ነውና አትደነቁ” ይላቸው ነበር ። ሰዎች የዋህን  ሙሉ እርሱነቱን ቢቀበሉትም ምክሩን ግን ለመቀበል  ይቸገራሉ ። የዋህ ምንጊዜም እሳት ማጥፋት ፣ ነገሮችን አቅልሎ ማየት ፣ ለነገሮች የቅን ትርጉም መስጠት ጠባዩ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ አዎ ፣ አዎ ይሉታል እንጂ አዎንና አሜን ብለው አይቀበሉትም ። ሰዎች ሁሉ አዎን ይላሉ ፣ አሜን የሚሉት ግን የሚያምኑት ናቸው ።
እግዚአብሔር፡- “ምን ያህል ብቁ ነህ ?” ሳይሆን “ምን ያህል ግልጽ ነህ?” የሚል አምላክ ነው ። በቀራንዮ አደባባይ ራቁቱን የተሰቀለው ጌታ ክርስትና ግልጽነት መሆኑን ያሳያል ። ጴጥሮስ የጓዳና የሳሎን ሕይወት የሌለው ወጥ ሰው ነበር ። ከመጋረጃ ጀርባና ከመጋረጃ ውጭ የሚባል የተውኔት ኑሮ የማይስማማው ሰው ነው ። ጴጥሮስ ለውጭ አልጋ ለቤት ቀጋ የሆነ ሰው አልነበረም ። ጴጥሮስ ለማለት የፈለገውን በግልጽ ይናገራል እንጂ እንዲህ ለማለት እንዲያ አይናገርም ነበር ። የጥርስ ገበታ እያቀረበ ሰውን በመሸንገል አይታወቅም ። በይቅርታ የሚያምን ይቅርም የሚል ሰው ነበር ። የተሰማውን ቢናገርም አንዴ ተናግሬአለሁ ብሎ ለስህተቱ ታማኝ አይሆንም ነበር ። ለመታረም የሚኖር ሰው ነበር ። ሰው እስኪሞት ተሠርቶ የማያልቅ ፍጡር መሆኑን የተገነዘበ ነበር ። ጅንን ሰው ሳይሆን ተግባቢ ሰው ነበር ። ደርባባ አቡን ሳይሆን ክንፎቹ የቀለሉት ለሁሉም ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ ሰው ነው ። ለመብረር እንደ ተዘጋጀ ንሥር ጥያቄን ለመመለስ ፣ ሲጠሩት “አቤት” ለማለት ፣ ሲልኩት “ወዴት?” ለማለት ዝግጁ ነበር ። መታዘዝ ሕይወቱ እንጂ ሥራው አልነበረም ። ገና ሳይንቀሳቀስ ሲያስበው የሚደክመው ሳይሆን ሠርቶ የሚደክመው ሰው ነበር ። ሠርቶ መድከም ወግ ነው ፤ ሲያስቡት መድከም ግን የልብ ልምሾነት ነው ። ጉልበት እንደ ገንዘብ የሚጠራቀምበት ባንክ ቤት የለውም ። በሰነፍን ቊጥር እየዛልንና እየወደቅን እንመጣለን ። አማኝ ብሎ ሰነፍ የለም ።
ጴጥሮስ ያልገባውን ነገር እንደ ገባው ለመምሰል የማይሞክር እስክሞት የማላውቀው ነገር አለ ብሎ ለመማር የሚኖር ሰው ነው ። እምነቱን ወዲያው የሚለማመድ ሰው እንጂ በይደር የሚያስቀምጥ የቤት ሥራዎች የተጠራቀሙበት ሰነፍ ተማሪ አልነበረም ። እምነትን በተግባር ሲያውሉት ይበልጥ እየታተመ ይመጣል ። ለመርሳት የማንፈልገውን ትምህርት ማድረግ መልካም ነው ። መማር አሸዋ ላይ መጻፍ ፣ ተግባር ግን በዓለት ላይ መቅረጽ ነው ።
ታዲያ ጠያቂው ጴጥሮስ “ወደ ታንኳ ስንገባ ተከትለነው እንጂ እኛ ቀድመን አልነበረም ። በታንኳ ለመሳፈርም ፣ ወደ ማዶ ለመሻገርም አሳብ አላቀረብንም ። ሙሉ በሙሉ ፈቃዱ የእርሱ ሳለ እንዴት ማዕበል ገጠመን? ቀድመን ስናስከትለው ማዕበል ነበረ ፣ ይህን ስናየው ኑረናል ። አስቀድመነው ግን እንዴት ማዕበል ይገጥመናል ? ዛሬ አዲስ ትምህርት ገጥሞኛል” እያለ ያስባል ። ፊት ለፊቱ ግን በታንኳው ወለል ላይ ክርስቶስ ተኝቷል ። እርሱን እያየ ይህን አሳብ ይቀምራል ። ደግነቱ የአሳብ ሠረገላ አያስከፍልም ፣ አይወዘውዝም ፣ ኬላ የለውም ፣ ቁም አይባልም ። ከደጅ ድምፅ ሲሰማ የአሳብ ሠረገላ ጥሎን ይፈረጥጣል ። የደቀ መዛሙርቱ የጭንቀት ጩኸት ጴጥሮስን ከአሳብ መንገዱ መለሰው ። የመጣን ነገር እንዴት ልውጣው እንጂ ለምን መጣ ? እያሉ መታከት ድካም ነው ። ማዕበሉ እንደሚመጣ እያወቀ ጌታ ጉዞ መጀመሩ በዚያ ውስጥ የሚማሩት ነገር ስለነበር ነው ።
ጌታችን ቀጣይ የሚያደርገውን ቢያውቅም አልነገራቸውም ነበር ። ሁሉ ቢነገረን ሕይወት እንግዳ መሆኗ ይቀር ነበር ። ያሰብነው ቀርቶ ያሰበው ሲሆን የማትለመድ ሕይወትን እንደተቀበልን ማስረጃው ነው ። ሕይወት በመስመር እንደ ተሠራች ከተማ ሳትሆን ተፈጥሮዋዊ ጎዳናዎች ያሉባት ጥንታዊት መንደር ናት ። ዘመናዊው ከተማ በዚህ ገብቶ በዚያ እንደሚወጣ ይታወቃል ። በጥንታዊ ከተማ ግን በሰፊ መንገድ ጀምሮ በጠባብ መንገድ መጨረስ ግድ ነው ። ምክንያቱ ምንድነው ? ሲባል እዚህ ጋ የደጃዝማች ቤት ነበርና አጥራቸውን ላለመንካት ዙረው መንገድ ስለሠሩ ነው ይባላል ። ደጃዝማች ማን ናቸው ? ተብሎ ጥናት ይጀመራል ። ሕይወት እንግዳ ናት ። ጌታችን የቀጣዩን ፈተናና ድል አልነገራቸውም ። ግን አንድ ነገር ሊያስተምራቸው ፈልጓል ። በማዕበል ውስጥም የማይደፈርስ ሰላም አለ ።
ወደ ጌርጌሴኖን አገር ለመድረስ ታንኳዋን መሳፈር ነበረባቸው ። ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ታላቅ ማዕበል ገጠማቸው ። ማዕበል የተነሣው ጌታ ከእነርሱ ጋር ስለሌለ ነው እንዳይባል አብሯቸው አለ ። እንደውም እንሻገር ብሎ ቀድሞ ወደ ታንኳይቱ የገባው እርሱ ነው ። ማዕበል የገጠማቸው ውሎአቸው ጥሩ ስላነበረ ነው እንዳይባል ብዙ ተአምራት ሲያዩ የዋሉበት ቀን ነው ። ማዕበል ሰፈር አይመጣም ። መሬት ለቀው ባሕር ላይ ሲራመዱ ብቻ የሚመጣ ነው ። በሰፈሩ ሲያልፉ የማይተናኮል ማን አለ ? ማዕበል ጎረምሳ ነው ። ማዕበል ከገጠመን ቢያንስ ከምድር ለቀናል ፣ አሳባችን ላቅ ብሏል ማለት ነው ። ከማዕበሉ ይልቅ የሚደንቀው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተኝቶ ነበር ። በማዕበል ውስጥ ተኝቷል ። በሁከት ውስጥም በእኔ ሰላም እደሩ ሲል እርሱ አርአያ ሁኖ ተኛ ። ደግሞም ደካማ ሥጋን እንደተዋሐደ ሊያስረዳን ተኛ ። የማይደክመው አምላክ ደካማ ሥጋ ተዋሕዶ ደከመ ። ደቀ መዛሙርቱ የራሳቸውን ብርቱ ጥረት ሳያደርጉ አልቀሩም ። አቅጣጫ መለወጥም ማዕበሉን አላራቀውም ። ሸክም ማራገፍም ሌላው ሙከራቸው ሳይሆን አይቀርም ። ብዙ ልምድ ያላቸው ፣ በጥብርያዶስ ላይ ሁለት ፀጉር ያወጡ ቢሆኑም አሁን ግን ማዕበሉን መግራት አልቻሉም ።
በዚህ ጊዜ ወደ ጌታ ቀርበው “ጌታ ሆይ ፣ አድነን ጠፋን” እያሉ አስነሡት ። ከጥሪያቸው ድምፅ የምንረዳው ከባድ ማዕበል እንደ ነበረ ነው ። ከክርስቶስ ጋር ሆነንም ማዕበል ይኖራል ። ያውም ወደፊት እንኖራለን የሚል ተስፋችን እስኪሟጠጥ ድረስ ማዕበል ይገጥመናል ። እርሱም አጠገባችን እያለ እንደሌለ ዝም ይለናል ። ጌታን ማዕበሉ አልቀሰቀሰውም ። የደቀ መዛሙርቱ ልመና ግን ቀሰቀሰው ። ማዕበሉ ታንኳይቷን ሲያናውጥ ፣ ብድግ እያደረገ ሲያፈርጣት ጌታ አልተነሣም ። እርሱ ማዕበል አያሰጋውም ። እርሱ የሚነሣው ለጸሎት ድምፅ ብቻ ነው ። በዚህ ጊዜ “እናንተ እምነት የጎደላችሁ ስለምን ትፈራላችሁ?” አላቸው ። ምን ዓይነት ቸር ጌታ ነው ! እምነት የሌላችሁ አላላቸውም ። የጎደላችሁ አለ እንጂ ። ትንሽ ብትጨምሩበት ይሞላል ማለቱ ነው ። ጌታ ወተቱን ማጥቆር ፣ ማሩን ማምረር አያውቅበትም ። እንደ ሰው አይደለም ። ጌታ ከማዕበሉ በፊት ጥርጣሬአቸውን ገሠጸ ። ከማዕበሉ በላይ መገሠጽ ያለበት ጥርጣሬ ነው ። ጥርጣሬ ባለበት ማዕበል ሥልጣን ያገኛል ። “እርሱ አብሮን ሳለ ጥፋት አያገኘንም” ብላችሁ እንዴት አላመናችሁብኝም ማለቱ ነው ። ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ ። ታላቅ ጸጥታም ሆነ ። ባሕር ለወትሮ ሽውታ አያጣውም ፣ የማዕበሉ አዛዥ ክርስቶስ ሲናገር ግን ታላቅ ጸጥታ ሆነ ። “ነፋሳትና ባሕርስ እንኳ የሚታዘዙለት ይህ እንዴት ያለ ነው ?” ብለው ተደነቁ ። እርሱ ለማዳን እንጂ ለማስደነቅ ሥራውን ሠርቶ አያውቅም ። ሰው ግን በመደነቅ ውዳሴ የሚባል የምስጋና ወዝ ያወጣል ።
አዎ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር እንዳለ በአማኑኤል ስሙ አትሞልኛል ። ነገር ግን ማዕበል ለምን ይወዘውዘኛል ? ለምትሉ እርሱ ከእኛ ጋር አለ ፣ ማዕበልም አለ ። እርሱ እንደማይሰማ ዝም ይላል ፣ እንደማይሰጥም ይዘገያል ። ከማዕበሉ ይልቅ የእኛ አለመጸለይ ያሳስበዋል ። እርሱ ሲናገር የተባበሩት ማዕበልና ባሕር ጸጥ ይላሉ ። እኔ እገለብጣለሁ የሚለው ነፋስ ፣ እኔ እቀብራለሁ የምትለው ባሕር የአዛዡ ድምፅ ሲሰማ ጸጥ ይላሉ ። ማዕበሉን አትፍሩ ፣ አዛዡን ቀስቅሱት ።
ሰኔ 12 ቀን 2011 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ