የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማያስወቅስ ክፉ ስም

“…ቀራጩ ማቴዎስም፥…” ማቴ. 10፡3 ።

ብዙ ሰው የኋላ ታሪኩን ለመደበቅ ከራሱ ጋር ትግል ውስጥ ይገባል ። ሀብቱ ከድህነት የጀመረ ሳይሆን በወርቅ ምንጣፍ ላይ እንደ ተወለደ ለማስረዳት ይሞክራል ። ሥልጣኑ ከሎሌነት የጀመረ ሳይሆን በማኅፀን የተቀባ መሆኑን ለመግለጽ ይዳዳዋል ። ቅድስናው በስርየት የጀመረ እንደሆነ ፣ ይቅር የተባለ ኃጢአተኛ መሆኑን ከመግለጥ የእናቴን ጡት ያልጠባሁ ፍጹም ፣ መምህር ያላስተማረኝ አማኒ ነኝ ለማለት ሩብ ጉዳይ ይቀረዋል ። በርግጥ በሀብት ላይ የተወለዱ ፣ አልጋ ወራሽ ተብለው በማለዳው የተሰየሙ ፣ በጠዋቱም ወደ እግዚአብሔር ቤት የገቡ ጥቂት ሰዎችን መጥራት እንችል ይሆናል ። የብዙኃኑ ሕይወት ግን ተራራ መውጣት ፣ ሸለቆ መውረድ ያለበት ነው ። ሰው ኖርኩ ካለም ሁሉንም የሕይወት ክፍል ቢያይ ታሪክ አለው ይባላል ።

ያለ ትላንት ዛሬ የለችም እንደሚባለው ዛሬ በዓሉ ከሆነ ዋዜማው አድካሚ ነበር ። ዛሬ የክብር ልብስ ቢለብሱም ዋዜማው ግን የጭስ የጠጣ ጨርቅ ነበረው ። ዛሬ ገንዘብ ቢነሰንሱም ትላንት ግን የሌሎችን ድጋፍ ይፈልጉ ነበር ። የዛሬው ቅላት የትላንት ጥቁረት ውጤት ነው ። እንደ ጌታ የሚበሉ እንደ ባሪያ የሠሩ ናቸውና ። አንድ ቀን የሚባለው ሃያ አራቱ ሰዓት ቀዳሚው አሥራ ሁለት ሰዓት ጨለማ ያለበት ነው ። ደስታን ከደስታ ቦታ ቢፈልጉ አትገኝም ። ደስታ የምትገኘው ኀዘንን ሲሻገሩ ነው ። በጥንተ ተፈጥሮ ሌሊት ይቀድማል ፣ ቀኑ ይከተላል ። ብርሃኑ ጨለማ አለው ። ጨለማውም ብርሃን አለው ። ሰው በዛሬው ሁነት ይገመግመን ፣ እንዲህ የኖርን ይመስለው ይሆናል ። የመጣበትን የሚያውቀው ግን የባለቤቱ አእምሮ ብቻ ነው ። ሸለቆውን ካልወጡ ተራራውን ማግኘት አይቻልም ። ጨለማ የብርሃን ዋዜማ መሆኑን ብዙ ሰው አያስተውልም ።

ትላንት በኃጢአት አብረውን የደከሙትን መጸየፍ ፣ በራሳችን እንደ ወጣን አድርገን በአደባባይ እኒያን መውቀስ የግብዝ አእምሮ ተግባር ነው ። የቻልነው ባስቻለን ጌታ እንጂ የሚችል ሥጋ ስለተሸከምን አይደለም ። መጣር ጥሩ ነው ፣ ከእኛ ይልቅ የጣሩ ግን ዛሬም ተራራ እየገፉ ነው ። የምንቆርሰው እንጀራ የረሀብ ዘመንን ያስተናገደ ፣ የምናዝዝበት እልቅናም የመገፋት ዋዜማ ያለበት ነው ። የእስራኤል ልጆች በየዓመቱ ከግብጽ የወጡበትን በዓለ ፋሲካ ሲያከብሩ በጉን ከመራራ ቅጠል ጋር እንዲበሉ ታዝዘው ነበር ። መራራውን ዘመናቸውን በማሰብ ለተጎዱት እንዲያዝኑ የሚያሳስብ ነበር ።

መጽሐፍ ቅዱስ የመጽናናት መጽሐፍ ነው ። ኃጢአተኞችን ባለ ተስፋ የሚያደርግ ፣ እኔንም ይቅር ይለኛል ብሎ ወደ እግዚአብሔር የሚያንደረድር መጽሐፍ ነው ። ስለ ዳኑ ኃጢአተኞች ፣ ስለነጹ ለምፃሞች ፣ ስለከበሩ ድሆች ፣ ስለጸኑ ሸምበቆዎች የሚናገር መጽሐፍ ነው ። አገልጋዮች የብርታት ታሪካችንን ብቻ ስለምንናገር “እኔማ ዋጋ የለኝም” ብለው ምእመናን ተስፋ እንዲቆርጡ እናደርጋለን ። ብርታታችን ድካም ነበረው ። ሕይወታችን ሁለት ገጽ የሚኖረው እግዚአብሔርን ስናገኝ ብቻ ነው ። ከዳተኛው ጴጥሮስ ሰባኪ ፣ አሳዳጁ ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን ማኅቶት የሆኑት ታሪክን በሚቀይረው እግዚአብሔር ነው ። ድካማቸው የተጻፈልን ለወቀሳ ለከሰሳ ሳይሆን እኔ አልድንም ለሚሉ ኃጢአተኞች ተስፋ እንዲሆን ነው ።

በቅዱስ መጽሐፍ ላይ በቀድሞ ስማቸው የሚጠሩ የእግዚአብሔር ምርጦች አሉ ። ስሙ ክፉ ነው ፣ የተጠቀሰው ግን ጌጥ ሆኖ ነው ። የዛሬውን ትልቅ ሹም “ሌባው እገሌ” እያልን በቀድሞ ታሪኩ ብንጠራው በአንገታችን ከረባት ሳይሆን ሰይፍ አንጠልጥለን መሆን አለበት ። የቀድሞ ፋይሉን ሊያጠፋ ደፋ ቀና የማይል ሹም ጥቂት ነው ። መጽሐፍ ቅዱስ በቀድሞ ስማቸው የሚጠራቸው ፣ ስማቸው የአሁን ሕይወታቸው ሳይሆን የቀድሞ ታሪካቸው በመሆኑ ነው ። ለመውቀስ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ምሕረት ለማግነን የቀረበ ስም ነው ። ለማሳነስ ሳይሆን ለአናሳዎች ሞራል ለመስጠት ያልተሰረዘ ስም ነው ። ሰው በቀደመ ስሙ ሲጠራ ፣ ራሱ በሚያፍርበት የቀደመ ግብሩ ሲሰየም ይከፋዋል ። በቀጥታ ራሱን “ቀራጩ ማቴዎስ” ያለው ግን ወንጌላዊው ነው ። ስሙ ክፉ ነው ፣ የማያስወቅስ ክፉ ስም ነው ። ጌታን ሲከተልም ድግስ ደግሶ ነው ። የቁም ተዝካሩን አውጥቶ ጌታን ተከተለ ይላሉ አባቶች ። ማቴ. 9፡10።

ማቴዎስ ራሱን ቀራጭ ብሎ ሲጠራ ያለው በሮማ ግዛት ነውና የከዳ ሠራተኛ መባልን ደፍሮ ነው ፣ ቀራጭን በሚጸየፉት አይሁዳውያንም ዘንድ የታሪኩን መለወጥ ሊያበስር ፈልጎ ነው ። ቀራጭ ማለት ለዚያ ዘመን አስተሳሰብ ባንዳ ፣ ከወገን እየበላ ወደ ጠላት የሚውጥ ማለት ነው ። ቅዱሱ መጽሐፍ ሐዋርያውን “ቀራጩ ማቴዎስ” ይለዋል ። ይቅር የተባለ ኃጢአት ያልተሠራ ያህል ነው ። እግዚአብሔር የኃጢአተኛን ኃጢአት ይቅር ሲል ከበደሉ በፊት ከነበረው ንጽሕና በላይ በማክበር ነው ። ይቅር የተባልሁ ኃጢአተኛ ነኝ ለማለት ራሱን “ቀራጩ ማቴዎስም” እያለ ይጠራል ። እግዚአብሔር ይቅር ያለውን ማን ይከስሰዋል ? ልክ እንደዚሁ “ጋለሞታይቱ ረዓብ” ፣ “ለምጻሙ ስምዖን” በማለት በቀደመ ክፉ ስማቸው የተጠሩ አሉ ። (ዕብ. 11 ፡ 31 ፤ ማቴ 26 ፡ 6 ።) ስሙ ክፉ ነው ፣ ግን የማያስወቅስ ስም ነው ።

ይቅር ተብለሃልና በቀደመ ስምህ ቢጠሩህ ደስ ይበልህ ። በጥፋትህ ላይ የእግዚአብሔር ምሕረት ገኗልና የምሕረቱ አደባባይ ሆይ ሐሤት አድርግ ።

ዕለተ ብርሃን 11

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መስከረም 19 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ