የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማይናወጥ ፍቅር

“ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።” (መዝ. 45፡2 ።)

የምድር መንቀጥቀጥ ከአስፈሪና ታላላቅ ክስተቶች አንዱ ነው ። ዓለም አቀፍ ዜናዎች ፣ የመስኩ ምሁራን ትንታኔዎች ፣ የልኬት መሣሪያዎች ፣ መንስኤዎችና ጉዳቶች ከሚመዘገቡበት ተፈጥሮአዊ ክስተት አንዱ የምድር መናወጥ ነው ። በምድር መንቀጥቀጥ ምክንያት ለመቶ ዓመታት የተሠሩ ከተሞች መቶ ሰከንድ ባልሞላ ጊዜ ሊፈራርሱ ይችላሉ ። ሰው ብቻ ሳይሆን የሚኖርበት ዓለምም ከንቱነት እንደሚያጠቃው የምድር መናወጥ ይነግረናል ። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድ ጊዜ የሚሞቱት በዚህ አደጋ ነው ። ይህን አደጋ ከሰው ይልቅ እንስሳት ቀድመው የማወቅና የመሸሽ ተፈጥሮአዊ ክህሎት አላቸው ። የሰው ልጆች ቅጽበታዊነት ፣ ታይቶ ጠፊነት ፣ ውበት ወደ ፍርስራሽ መለወጥ በምድር መንቀጥቀጥ አደጋ ይታያል ። ሁሉም ሰው ከሚፈራው ነገር አንዱ የሚያምናት ምድር መክዳትዋ ነው ። በምድር መናወጥ ጎዳናዎች ለሁለት ይከፈላሉ ። ተራራዎች ይደለደላሉ ። ፍርስራሾች ይታያሉ ። የምድር መናወጥን የማይፈራ ደፋር ሰው ሊኖር አይችልም ። ይልቁንም ለሕይወቱ የገዛ ልጁን የሚጠራጠር ንጉሥ የምድር መናወጥን አልፈራም ማለት አይችልም ። ንጉሥ ዳዊት ግን እግዚአብሔርን አምላኩ ፣ መጠጊያውና ረዳቱ በማድረጉ አንፈራም ይላል ።

የመጣውን መከራ አለመፍራት አማኝነት ነው ። ያመጣነው መከራ ግን ንስሐ እስካልገባን አስፈሪ ነው ። እግዚአብሔር ማንንም አያጠፋም ። የገዛ ምርጫችን ግን ያጠፋናል ። ምድር መኖሪያችን ናት ። ምድር ምግባችን ናት ። ምድር መሰማሪያችን ናት ። ምድር ፀሐይን ለመሞቅ ፣ አየርን ለመሳብ ምክንያታችን ናት ። ምድር ለሰው ልጆች መኖሪያነት በእግዚአብሔር የተመረጠች ናት ። ከፀሐይ ትንሽ ቀረብ ብንል ትኩሳቱ ፣ አሁን ካለንበት ትንሽ ብንርቅ ብርዱ አያኖረንም ነበር ። በትክክለኛ ቦታ ላይ ያስቀመጠን የሁልጊዜው ትክክል እግዚአብሔር ነው ። ምድር መቀበሪያችን ናት ። ምድር የተገኘንባት ማኅፀን ናት ። ምድር የምንሄድባት ቀሪ መንገዳችን ናት ። አዳም ከምድር አፈር ተገኘ ፣ አዳም መሬት ነህና ወደ መሬት ትመለሳለህ ተባለ ።

እንደ ምድር የሆነ በዓለም ላይ አለ ማለት ነው ። ምድር ማለት ማኅደር ፣ ከታች መክተቻ ፣ መደበቂያ ፣ መኖሪያ ማለት ነው። ያ ምድር የተባለ የጠለለን ሊሆን ይችላል ። የሚያስጠጋ ማግኘት በዚህ የስደት ዓለም ላይ ወሳኝ ነው ። እንደ ምድር ያለ የሚያበላን የሚያጠጣን ሊኖር ይችላል ። ሰው እንደ ራሱ ካልወደደን በቀር ሊያበላን ሊያጠጣን አይችልም ። የፍቅር ሙቀት የሰጠን ፣ የተማመንበት ፣ ገመናዬን ይሸፍናል የምንለው ሊናወጥ ፣ ከስፍራው ልናጣው እንችላለን ። ብዙ ሰው ይህን ገና ሲያስበው ብርድ ፣ ብርድ ይለዋል። በዓለም ላይ ግን እንኳን የወዳጅ ክዳት የእናትም ሞት ተሰምቶ ኑሮ ይቀጥላል ።

የተማመንበት ፣ ተስፋ የሰጠን ፣ “እኔ አለሁ” ብሎ የፎከረልን ዛሬ ላይ ላይገኝ ይችላል ። ለፈጣሪው ያልታመነ ሰው ለእኔ ይታመናል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው ። ቢሆንም ፍቅር ያምናልና ሰዎችን ከመጠራጠር ማመን የተሻለ ነው ። ማመንና መተማመን ግን ይለያያል ። አይተወኝም ብለን የምንተማመነው እግዚአብሔርን ብቻ ነው ። ሰው ባስቀመጡት ቦታ አይገኝም ። ተንቀሳቃሽ ፍጡር ነው ። ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚጠቀም ብቻ ሳይሆን ተንቀሳቃሽ ፍጡርም ነው ። አላውቅህም ለማለት የሚቸኩል የጴጥሮስ ልጅ ነው ። ጴጥሮስ አብሮ እራት በልቶ ፣ ቆርቦ አላውቅህም ለማለት ቸኮለ ። ሰዎች አብረን በልተን ፣ አብረን ቆርበን ቢከዱን አዲስ ነገር አይደለም ። በእኛ የሚሆነው በጌታ የሆነው ነው ። እርግጠኛ ጠላት ባለበት እርግጠኛ ወዳጅ ማግኘት ይቸግር ይሆናል ። ለጥያቄአችን ሙሉ መልስ ሆኖ ክርስቶስ መጥቷል ። ራሱን ለእኛ ዋጋ አድርጎ ሰጥቶን ፣ በራሱ መውደድ ላይ ብቻ ተመሥርቶ ወዶናል ። ሌሊትና ቀን ይለዋወጣሉ ፣ ክረምትና በጋ ፈረቃ ይገባሉ ። የክርስቶስ ፍቅር ግን እንደ ጸና ይኖራል ። አምባ ሙሉ ፍቅር የክርስቶስ ብቻ ነው ። የሰው ፍቅር ከውስንነቱ የሚመጣ ፣ ነዳጅ እንደ ጨረሰ መኪና መንገድ ላይ የሚቆም ነው ። ሰዎች የጠሉን የተጠላን ስለሆንን አይደለም ። እኛ የእግዚአብሔር ውዶች ነን ። ሰዋዊ ፍቅራቸው ፣ ደመ ነፍሳዊ ውዳቸው ስላለቀ ብቻ ነው ። ሰው ከአንበሳ ጋር የመላመድ ፍቅር አለው ። አንበሳው እስከጠገበ ድረስ የዚያ ሰው ወዳጅ ነው ። ሲርበው ግን ያ ወዳጁ ምግቡ ይሆናል ። አራዊታዊ ፍቅር በምድር ላይ አለ ። የተጠላነው ፍቅር ስላለቀባቸው እንጂ የተጠላን ስለሆንን አይደለም ።

የታመንበት ልጅ በሞት ይንሸራተታል ። ንብረታችንን ያባከንበት ባጣን ቀን ሊያየን ይጠላል ። ዕድሜ ለእገሌ ያልንለት ዕድሜአችንን ያሳጥራል ። እንዳለ ያለ አማኑኤል ግን ከእኛ ጋር ይኖራል ። የዕብራውያን መልእክት ፀሐፊ የማይናወጥ መንግሥት አለው ይለዋል ። (ዕብ. 12 ፡ 28 ።) የማይናወጥ ፍቅር የሆነው እግዚአብሔር ምድር ብትናወጥ ፣ የተሸከሙን የመሸኛ ደብዳቤ ቢጽፉልን እርሱ ከእኛ ጋር ነው ። በእግዚአብሔር የሚታመነው የአገራችን ሰው እንዲህ ይላል፡- “ቀባሪ በፈጣሪ !” ደግሞም እንዲህ ይላሉ፡- “ሳለ መድኃኔ ዓለም!”

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 9 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ