የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማይወደደው ሲወደድ

“ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ።” መዝ 138፣16።

ገና በማኅፀን ያለውን ፅንስ የማየት አቅም ያለው ጥቂት ነው፡፡ የተወለደውን የዕለት ልጅ ለማቀፍ እንኳ ወላጆች ይፈተናሉ። በመሠራት ላይ ያለን ሕንፃ ለማየት ብዙ ሰው ፈቃደኛ አይደለም። እየተሠራ ያለ ሕንፃ ላይ ቤት ግዙ ቢባል ብዙ ሰው ይሸሻል። ይህ መዝረክረክ፣ ይህ አለማማር፣ ይህ ቆሻሻ ፣ ይህ አጥር፣ ይህ ክፍተት፣… ይስተካከላል፣ በውበት ይደመደማል ብሎ የሚያስብ ጥቂት ነው ። የሴቶች ፀጉር ቤት ወንዶች እንዲገቡ አይፈቀድም፣ የሚሠራ ነገር ሁሉ የሚጀምረው ከመፍረስ ነ ው። በሥራ ላይ ያለውን ውበት የሚያዩት ሠራተኞቹ ብቻ ናቸው ። ያለቀውን ውበት ሌሎች ያያሉ። የሚገርመው የገዛ የትዳር ጓድም ያለቀውን ውበት ብቻ ማየት የሚችል ነው። ይገርማል እየተሠራ ያለውን ጽንስ ወላጆች ማየትም መቀበልም አይችሉም። እየተሠራ ያለውን የሴቶች ውበት ባሎችም ማየት አይችሉም።

ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነሣ ያለንን ማንነት ለማየት አስቸጋሪ ነው። ዓይን በቆሻሻ፣ ፊት በማያምር ነገር ተሞልቷል። የጠዋት ምኞታችን ሳንስተካከልና ሳንፀዳ ማንም እንዳያየን ነው። ጠዋት ላይ ከእንቅልፍ ሲነሣ  ብዙ ሰው የሚያኰርፈው ዘለው እንዳያቅፉት ነው። ወዳጆችም ማየት የሚችሉት ያለቀውን ውበት ነው። ራሳችንን በመስተዋት ስናየው የማንቋቋመው ቀን ብዙ ነው። ወዲያው ውኃ ፍለጋ እንሮጣለን። በመሠራት ላይ ያለውን ሂደት ማንም ማየት አይችልም፣ ባለቤቱም ማየት አይችልም ። ገመናዬን ሰው እንዳያይብኝ እያሉ በሸተኞች ይጸልያሉ፣ ቆሻሻ የተሸከመ ሰው የሰውን ቆሻሻ ይጸየፋል ። በሽተኛው እስኪያፀጸዱት ክፍሉ ይዘጋል። ግማሹን እንኳ እኔ ላግዝ የሚል የለም። ቢልም አይታመንም። የሕፃን ወዳጆች “ማሙሽ የት አሉ?” ብለው ሲጠይቁ ሞግዚቶቹ “ቆይ እያለበስኩት ነው፣ ይመጣል” ብለው በዲፕሎማሲ ቋንቋ ይናገራሉ። ማሙሽ ግን ተበለሻሽቷል ። ስሙ ሲጠራ ከነ ቆሻሻው ለመውጣት እየታገለ ነው። ሞግዚቷ ግን ድምፅዋን ቀንሳ፣ ይህን ጉድ ሌላ እንዳይሰማው ብላ “ቆይ ማሙሽ” ትለዋለች። ሰው ለመበላሽት ቅርብ ነው። ሰው ለመጽዳትም ቅርብ ነው። ከጎዳና ላይ አንድ ጥቀርሻ የለበስ ሰውን አንሥተው በአምስት ደቂቃ እጥበት ንጹሕ  ያደርጉታል። ሲያለብሱት ያምራል። ዕድሜ ለድህነት ቦርጭና ትርፍ ሥጋ የለውም። ለማማር አምስት ደቂቃ፣ አንድ ባልዲ ውኃ የሚፈልገውን ይህን ሰው ለማየት የሚደፍር የለም። ንስሐም በደቂቃ የሰውን ታሪክ ትለውጣለች፤ የምንከስሰው የምንወቅሰው ሰው “ይቅርታ” በሚል ቃል አዲስ ምዕራፍ ሲጀምር እናያለን። ሰው ሆኖ የማይሳሳት ፣ እንጨት ሆኖ የማይጤስ የለምና።

እግዚአብሔር ግን ያየው ገና  ያልተሠራውን ማንነት ነው። እኛ ግን ማየት ያቃተን እየተሠራ ያለውን፣ ለማለቅ የጊዜ ቀጠሮ የተሰጠውን ነው።  ሱሰኛው ከሱስ ለመውጣት ትግል ላይ ነው። ዙሪያው ያሉ ግን ተስፋ በመቁረጣቸው እንኳን በሂደት ላይ ያለውን ማንነት ሊቀበሉ ቢለወጥም እንኳ አያምኑትም፤ የራሱ ጉዳይ ብለው ትተውታል። እግዚአብሔር ግን ገና ያልተሠራውን ማንነት ያያል። ያማሩ ከተሞች ሁሉ መነሻቸው የማያምር ነበረ። ያልተሠራውን አካል የሚያይ ባለ ራእይ አገኙና ዛሬ ውድ ስፍራ ሆኑ። የዛሬው የአእምሮ በሽተኛ ተስፋ የሚያደርገው ላይኖር ይችላል። እየገደለ መሳቅ ባለመቻሉ ለዚህ በሽታ እንደ ተዳረገ ማንም አያውቅም። እግዚአብሔር ግን ያልመጡ ቀኖቹን ጨብጦለታል። ሰዎች ግን ጤናኛ  ቢሆንም መቀበል ይከብዳቸዋል።

ሕፃናት ያልተሠሩ አካላት ናቸው። ያልተሠራ አካልን የሚያይ የእግዚአብሔር ዓይኖች ቢኖሩን ብዙ ዋጋ ከፍለን ብቁ እናደርጋቸዋለን።  እኔ ቋጥኝ ባይና ሚካኤል አንጀሎ ዓለት ቢያይ ለእኔ ሸክም ፣ ለእርሱ የውበት ዳር ነው። ያልተሠራ አካልን የሚያይ ባለሙያ ነ ው። ብዙዎች ርቀውኝ  ሄደዋል ፣ እኔ ገና በስመ አብ ማለት አልጀመርኩም ስለዚህ ይቅርብኝ እያልን ይሆናል። ያልተጀመረ ሩጫችንን የሚያይ ጌታ አለ። ለማመን፣ ለደግነት አይረፍድም ።

በብዙ ነገር ገና ነን። እግዚአብሔር ግን ያልተሠራ አካላችንን እያየው ነው። ውድ ወዳጄ! ሐዲስ ልደት አለህ፣ በብዙ ዓይኖች ፊት ታድጋለህ፣ በመከራ በችግር ውስጥ በድል ታልፋለህ፣ በናቁህ ፊት ከፍ ትላለህ፣ ሕመምህ ለምስክርነት ፣ ውድቀትህ ለትምህርት ይሆናል። ያልተሠራ አካልህ ፣ ያልመጡ ቀኖችህ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እየታዩ ነው። አንተ ጎበዝ ተነሣ!  ሁሉ የሚወድህ ስትስተካከል ነው፣ ሊያስተካክልህ የሚወድህ እርሱ ብቻ ነው፡፡ የተጠላሁ ነኝ ብለህ ታዝናለህ፣ ለክርስቶስ ፍቅር ግን በር ቆልፈህ ትቀመጣለህ ። ስልክ አልደወሉልኝም ብለህ ያለ መፈለግ ስሜት ያሰቃይሃል ፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ  በቃሉ ሲደውልልህ ግን እንዳልሰማ አልፈሃል።  “ስደውልላቸው አያነሡም፣ ምን አድርጌአቸው ነው?” ትላለህ፣ አንኳኳ  ይከፈትልሃል የሚልህ ግን ጌታ አለህ! ያንተ ነገ ውብ ነው ! ክርስቶስ ካበራልህ የሚያጨልምብህ ማነው? የማይወደደው ማንነትህ ተወዷል ደስ ይበልህ!

አንተ ሆይ ! ጌታ ወዳየልህ ቀን ገስግስ!

ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ