የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማይጠፋ ዋጋ (ማቴ. 10÷42)

      የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ                          ማክሰኞ ነሐሴ 20/ 2006  ዓ/ም

ዘመን ረዝሟል፣ ጊዜውም ከሕልም ይልቅ ሩቅ ሆኗል፣ የኖሩበት ሥፍራም በትክክል ይህ ነው ማለት ያስቸገል፣ የመቃብራቸውም ሥፍራ በውል አይታወቅም፣ ዘሮቻቸውን አግኝተን መጠየቅ አንችልም፣ ያስቀመጡትም ሀብት ዛሬ የለም፣ ፎቶ ስላልነበረ መልካቸውን ለይተን ማወቅ አንችልም፣ ስለ እነርሱ የምንሰጠው አስተያየትም በ‹‹ይሆናል›› ነው፣ ጀግንነታቸውንና ታሪካቸውን ለትውልድ እንናገራለን፣ በስዕል ችሎታችን መልካቸውን እንጭራለን፣ የሐውልት ችሎታችንንም በእነርሱ ቅርፅ እናስመርቃለን፣ ልብ ወለዶችን በስማቸው ዙሪያ እናቀናብራለን፣ እነዚያ ጀግኖችና ስመ ጥሮችን ግን በዚያ ጊዜ በነበረው አመለካከት እንጂ በዛሬው ሚዛን ውድቅ ናቸው እንላለን፡፡
አዎ ጳውሎስን እናውቀዋለን፣ ጳውሎስን ያሳደዱ የነበሩትን ግን ስማቸውን አናውቅም፡፡ ምንም በወቅቱ ብርቱዎች ቢሆኑ አናስባቸውም፡፡ የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስን እናስበዋለን፣ የፈረደበት ጲላጦስን ግን ስሙን እንኳን አንጠራውም፡፡
እግዚአብሔርን የማገልገል ዋጋ ብቻ አይወድቅም፡፡ ዓለም ወንጌልን ሲገፋ ይኖርና ሁሉም ነገር ጠባብና ጭንቅ ሲሆን ቤተ ክርስቲያንን ይፈልጋል፡፡ እውነት በመጨረሻይቱ ሰዓት እንኳን አትደክምም፡፡
ሰዎች ዓይኔን በዓይኔ በማለት የሚወልዱት በሚቀጥለው ትውልድ ለመታወስ ባላቸው ጥማት ነው፡፡ እነርሱ ግን ስለ አባታቸው እንጂ ስለ አያታቸው አያስቡም፡፡ የእነሱም ታሪክ ከአንድ ትውልድ እንደማያልፍ ይረሳሉ፡፡ ላለ መረሳት ፎቶአቸውን አባዝተው ይበትናሉ፡፡ ቋሚ ማስታወሻዎችን ይሠራሉ፡፡ ለዛሬ ትውልድ ይጠቅማል ብለን ካልሠራን በሚቀጥለው ዘመን ለመታወስ ብንሠራ እውነተኞች አይደለንም፡፡ መልካምነት ሕይወታችን እንጂ ሥራችን ሊሆን አይገባም፡፡ ሥራ ግድ ነው፣ ሕይወት ግን ውድ ምርጫ ነው፡፡ ሥራ በሰዓት ነው፣ ሕይወት ግን የማያቋርጥ ነው፡፡ ሥራ ያደክማል፣ ሕይወት ግን አይጠገብም፡፡ መልካምነት ሕይወት የሆነላቸው ለሁሉ ሲደርሱ ጊዜም፣ ጉልበትም፣ ገንዘብም አያጥራቸውም፡፡ መልካምነት ሥራ የሆነባቸው ግን የጊዜ፣ የጉልበት፣ የገንዘብ ምስኪን ናቸው፡፡


ከኑሮአቸው አልፈው ለቀብራቸው የተጨነቁ፣ መቃብር ቤታቸውን በዕብነ በረድ የሠሩ እነዚያ መኳንንት በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ዘመድ እንኳ አልቅሶ ሳይቀብራቸው ቀርተዋል፡፡ ሰው ተወለደበትን ቦታ እንጂ የሚሞትበትን ቦታ አያውቀውም፡፡ ከድሃው ቀምተው የሠሩት ያ የዘላለም ሐውልት የመሰላቸው ቤታቸው ዛሬ እነርሱን እንኳ በቅርብ የሚያውቅ ሰው የለበትም፡፡ ያለፉ ያልጣሩበት ይዘሉበታል፡፡
ዓለም የተዋቀረችበት ትልቁ የእግዚአብሔር ሥርዓት ማለፍ ነው፡፡ ሁሉም ያልፋል፡፡ ጉብዝናም ይቀራል፣ ውበትም ይረግፋል፣ ሥልጣንም ይሻራል፣ ጀግንነትም ሞት ይውጠዋል፣ ማጌጥም ይረግፋል፣ ክብርም ይጠወልጋል፣ ወጣትነትም ይሸመግላል፣ ደፋርነትም ይከዳል፣ ሀብትም ይበተናል፡፡ ዓለም ከየት እንደ መጣች እንጂ ወዴት እንደምትሄድ የሚያውቅ የለም፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ግን ፀንቶ ይኖራል፡፡
ሰውየው ምንም ነገር ሲደርስበት ‹‹ይህም ያልፋል›› ይላል፡፡ ስሙም ‹‹ይህም ያልፋል›› ሆነ፡፡ ሊሞት ሲል መቃብሩ ላይ ‹‹ይህም ያልፋል›› ብላችሁ ጻፉልኝ ብሎ ተናዘዘ፡፡ እነርሱም ተናደው ከሞትህ ወዲያ ደግሞ ምንድነው የሚያልፈው? ብለው ነቀፉት፡፡ ኑዛዜ ነውና ሐውልቱ ላይ፡- ‹‹ይህም ያልፋል›› ብለው ጻፉ፡፡ ከወራት በኋላ በመቃብሩ ላይ መንገድ ያልፍ ነበርና መቃብሩ ፈረሰ፡፡ በዚህ ጊዜ እነዚያ ሰዎች፡- ‹‹ሁሉም ያልፋል›› ብለው ተጽናኑ፡፡
ጌታ ኢየሱስም የማይጠፋ ዋጋ ያለው የእርሱን አገልጋዮች መቀበል መሆኑን ተናገረ፡፡ ለእነርሱ የሚደረገው ቀዝቃዛ ውሃ እንኳ በእርሱ ዘንድ አይረሳም፡፡ እኛ ግን ቤታቸው ላይ ተቀምጠን ስንቶቹን እናሴርባቸዋለን፡፡ ልብሳቸውንም እየተጋፈፍን ገበናቸውን እናወራባቸዋለን፡፡ ብድራቸውን ከፍለን ሳንጨርስ ሌባ እንጠራባቸዋለን፡፡ የኮሚኒስት ሥርዓት ከጣለብን ውድቀት አንዱ ውለታ ቢስነት ነው፡፡ የምናመልከው ጌታ ግን የአንድ ብርጭቆ ውኃን ውለታ እንኳ አይረሳም፡፡
የማይጠፋ ዋጋ መቀበል ነው፡፡ መቀበል የተደረገልንን በጎ ነገር ዋጋ መስጠት ነው፡፡ ትልቁ በደል ውለታ መርሳት ነውና፡፡ መቀበል ሰዎች የራሳቸው አመለካከት እንዳላቸው መረዳት ነው፡፡ ትልቁ ቀውስ የሚከሰተው ሰዎች እንደ እኔ ያስቡ ስንል ነውና፡፡ መቀበል እኔ ብቻ ትክክል ነኝ የሚለውን ግትርነት መጣል ነው፡፡ እኛ ብቻችንን ስለ ሕይወት ሙሉ ዕውቀት የለንምና፡፡ በደሳሳው ጎጆአችን እንግዶችን፣ በተረበሸው ልባችን ክርስቶስን እንቀበል፡፡ እኛስ መቀበል ከብዶን ይሆን? መቀበል የማይጠፋ ዋጋ አለው፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ