የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማይጨቃጨቅ

 “እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤… የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ” 1ጢሞ. 3፡2-3
ሙግት የሚወድና ፍርድ ቤትን እንደ ቤተ ክርስቲያን ካልተሳለመ ደስ የማይለው አንድ ሰው ዳኛው “አግብተሃል ?” ብለው ሲጠይቁት “አዎ ትዳር አለኝ ፣ ያገባሁት ሴት ልጅ ነው” ብሎ መለሰ ። ዳኛው በመገረምና በቊጣ “ታዲያ ልታገባ የምትችለው ሴት መሆኑ የታወቀ ነው ፣ ለምን እንዲህ ያለ መልስ ትሰጣለህ ?” ቢሉት “አይ የእኔ እኅት ያገባችው ወንድ ነው” አለ ይባላል ። ነጋ ለነገር ፣ ጠባ ለጭቅጭቅ የሚሰለፉ ፣ ካልተጨቃጨቁ የኖሩ የማይመስላቸው ፣ ዝም ያሉ ቀን የሞቱ የሚመስላቸው ብዙ ሰዎች አሉ ። ሴትየዋ ሰፈሩን በነገር ቀጥ አድርገው ያቆሙት ፣ ዕረፍት አጥተው ዕረፍት ያሳጡ ነበሩ ። የአዲስ አበባ መንደሮች እየፈረሱ ወደ አዲሱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከተወሰዱ መካከል እኚህ ሴት አንዷ ናቸው ። እዚያ ፎቅ ላይ በመስኮት የሚያዩት በዚህ በኩል መንገደኛ ሲያልፍ በግቢው በኩል ዘበኛው ሲንጎራደድ ብቻ ነው ። ጎረቤታቸው ማን መሆኑን አያውቁም ። ወደ ቀድሞ ሰፈራቸው በንዴት መጡ ። ከሩቅ እየተሳደቡ ሲመጡ “ደሞ መጣሽ” ቢሏቸው “ይቅር በሉኝ እዚያ ፎቅ ላይ ተሰቅዬ እንኳን የምሰድበው የሚሰድበኝ አጣሁ” አሉ ይባላል ። የሚያጣላ ነገር ቢያጡ በሰላምታ የሚጣሉ ፣ “እንደምን አደራችሁ ?” ሲባሉ “ባድር ባላድር ምን አገባችሁ ?” የሚሉ አያሌ ናቸው ።

የሚጨቃጨቁ ሰዎች ብዙ ጊዜ ለቤቱ አንድ ልጅ ይሆኑና የሁሉ ዓይን እነርሱ ላይ ያርፋል ። የሚፈልጉትን ነገር ሳይጠይቁ ያገኙታል ። ቆንጆና ጎበዝ ተብለው ይወደሳሉ ። አትንኩት ተብለው በሁለት ፊት ያድጋሉ ። በዚህ ጊዜ ሁሉም ነገር የማይጥማቸው ተሳዳቢና ደፋር እየሆኑ ይመጣሉ ። ሁለተኛ ልጅ ቢወለድም ራሳቸውን የሚያስቡት እንደ ብቸኛ ነው ። ሁለተኛውን ልጅ ወንድማቸው መሆኑን ከመቀበል ልጃቸው አድርገው መቀበል ይቀላቸዋል ። ተጨቃጫቂነት ያለ እኔ አይሆንላቸውም ብሎ ከማሰብ የሚመጣ ነው ። የእኔን ድርሻ ሌሎች ይሥሩልኝ ብሎ ሸክም የመሆን ዝንባሌ ነው ። ተጨቃጫቂዎች ስድባቸውን እንደ ትልቅ መሣሪያ ያዩታል ። እንግዳ ሲመጣ እየገነኑ ይመጣሉ ። ብቻቸውን መኖርና መብላት ይፈልጋሉ ። ዕድሜአቸው ቢገፋም ገና ሕፃን ነኝ ብለው ያስባሉ ።
ተጨቃጫቂነት በተለያየ መንገድ ይመጣል ። ማዘዝ የሚወዱ መሥራት ግን የማይችሉ ሰዎች ተጨቃጫቂ ናቸው ። ለመሥራት ሙያና የልብ ቆራጥነት የላቸውም ፣ የማዘዝ ግን ብቃት አላቸው ። የሚጨቃጨቁት ስንፍናቸውንና ሙያ ቢስነታቸውን ሰው እንዳያውቅባቸው ነው ። ጭቅጭቅ ሽፋን መስጫ ነው ። በሱስ የተያዙ ፣ በትዳራቸው ላይ የሚማግጡ ሰዎች ጭቅጭቅ ሊያበዙ ይችላሉ ። ሁልጊዜ በስህተታቸው ፊት ስለሚኖሩ ታወቀብኝ የሚል ስጋት ውስጥ ይገባሉ ። በዚህ ምክንያት መጨቃጨቅ ይወዳሉ ። የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎችም መጨቃጨቅን እንደ አትኩሮት ማግኛ ይጠቀሙበታል ። የተረሱ ስለሚመስላቸው አለሁ የሚሉት በመጨቃጨቅ ነው ። የማይረኩ ሰዎችም በጭቅጭቅ የታወቁ ናቸው ። እነርሱ ብቻ ጎበዞችና አሳቢዎች እንደሆኑ ያስባሉ ። ሌላውን ሰው ሰነፍና ሞራል የሌለው እድርገው ይስላሉ ። ጭቅጭቃቸው ሌሎችን በእነርሱ አለመርካት ውስጥ ለመክተትና ጓደኛ ለማግኘት ነው ። አለመርካት ትልቅ የጭቅጭቅ ርእስ ነው ።
ሙያ ከእኔ ወዲያ ለሐሳር ብለው የሚያስቡ ሰዎችም ተጨቃጫቂዎች ናቸው ። ሌሎች የሠሩት ነገር አይጥማቸውም ፣ ሲቀመጡ ደግሞ ለምን ? ይላሉ ። በጣም ጎበዝ መሆንም ተጨቃጫቂ ያደርጋል ። አሳባቸው በዝቶ አቅማቸው ያነሰባቸው ሰዎችም በጭቅጭቅ የታወቁ ናቸው ። ተጨቃጫቂዎች አንድን ነገር ደጋግመው የሚናገሩ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር ጸሎትን የሚሰማው በመጨቃጨቅ ይመስላቸዋል ። ሳይታክቱ በትዕግሥት መጸለይና መጨቃጨቅ ልዩነት አለው ። የሚፈልጉትን የማያውቁ ሰዎችም ይጨቃጨቃሉ ። የብዙ ሰው ችግር የሚፈልገውን ነገር በትክክል አለማወቁ ነው ። ትምህርት እያለ ያስብ ነበር ተማረ ፤ ነገር ግን አሁንም እርካታን አላገኘም ። ትዳር ይሻ ነበረ ፣ አገኘ ፤ አሁንም ደስተኛ አይደለም ። ይህ ሰው የሚያስደስቱ ነገሮችን እንጂ ራሱን ደስታን እየፈለገ አይደለም ። የሚያስደስቱ ነገሮችን መፈለግ ደስታን አያስገኝም ። ደስታ ራሱ ግን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው ። ካላስደነበሩአቸው የአገሬ ሰዎች አይሠሩም ብለው የሚያምኑም ሰዎች ይጨቃጨቃሉ ። የአለቅነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች መሪ እስኪሆኑ ድረስ መጨቃጨቅን አይተዉም ።
ሆዳቸውን የሚወዱ ሰዎች ጨቅጫቃ ናቸው ። የቤት ወጪ በቅጡ የማያወጡ ነገር ግን ወጥን በማጣጣም የታወቁ ናቸው ። ስጡ ሲባሉ አይሰጡም ፣ ትችት ግን ጎበዝ ናቸው ። ሆድን መውደድ አንድ ቀን ገደል ይከታል ። በትዳራቸው ላይ ሌላ ትዳር መሳይ የሚይዙ ሰዎች የሚታለሉት በሆዳቸውና በሱስ ነው ። እንደ ዔሣው ሆዳቸውን የሚያመልኩ ፣ ወጥ አሳዳጆች ጨቅጫቃ ናቸው ።በርግጥ ሁሉም ሚስት ባለሙያ ላይሆን ይችላል ። ይህ ሰው ራሱ መሥራት ቢለምድ ወይም ይሥሩ የሚላቸውን ሰዎች ሙያ ትምህርት ቤት ልኮ ቢያስተምር በቀጣይ ዘመን ከመጨቃጨቅ ይድናል ።
አዲስ ፍቅር የያዛቸው ሰዎች ጨቅጫቃ ናቸው ። ሰው በሃምሳ ዓመቱ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ፍቅር ቢጀምር የሃምሳ ዓመት ልምዱ ለዚህኛው ሕይወት አይረዳውም ። መልሶ እንደ ወጣት ይሆናል ። ቅናት በውስጣቸው ያደረ ሰዎች እገሌ እግርሽን አየ እያሉ ይጨቃጨቃሉ ። ሚስቴን ተመኝተሃታል ብለውም ከሰው ይጣላሉ ። ልምድ ማጣትና ቅናት የጭቅጭቅ መነሻ ናቸው ።
የነሐሴ ዝናብ እኝኝ ብላ ይባላል ። ተጨቃጫቂ ሰውም እኝኝ ብላ ነው ። እኝኝ ብላ ከጠዋት እስከ ማታ እስከ ሦስት ቀንም የሚቀጥል የማያስወጣ የማያስገባ ዝናብ ነው ። ጨቅጫቃ ሰው ይሰለቻል ። ሁሉም ሰው አመሉ ነው እያለ የሚናገረውን ነገር ያፈስሰዋል ። ወዳጅነቱና ትዳሩም ይፈርሳል ። እርሱም በራሱ ሰላም የሌለው ይሆናል ። ምን መሆን እንዳለበት የማያውቅ ፣ ሰዎች እንዴት እንዲሆኑ እንደሚፈልግ የማይገነዘብ ሰው ነው ። ጨቅጫቃ ሰው ነዝናዛ ሰውም ይባላል ። የሚነዘንዝ የሌሊትና የክረምት ቊስል ነው ። ጨቅጫቃ ሰው ጤና አጥቶ ጤና የሚያሳጣ  ነው ። አንዳንዶቹ ነዝናዛዎች ሱሰኞች ስለሆኑ ጤና አያጡም ። ሲነዛነዙ ደስ ይላቸዋል ።
ጨቅጫቃ ሰዎችን መሾም ሥራን መበደል ነው ። ጨቅጫቃ ሰዎችን ልናተርፋቸው የምንችለው የሚጠሉትን ነገር በመለየት ፣ ጠባያቸው መጥፎ መሆኑን በመንገር ፣ ይልቁንም ትዕግሥትን እንዲሰጣቸው በመጸለይ ነው ። ምንም ሳይሆኑ ብዙ እንደሆኑ እየተሰማቸው ባልተጨበጠ ነገር የተጨበጠ ሁከት ውስጥ የሚገቡ አያሌ ናቸው ። ልናዝንላቸው ይገባል ። እኛም በመሰልቸት እንዳንርቃቸው ትዕግሥትን መለማመድ አለብን ።
ኤጲስ ቆጶስ የማይጨቃጨቅ ሊሆን ይገባዋል ። ነገር አፍቃሪ ሁኖ ፍርድ ቤት ሥራው እንዳይሆን ፣ አንድን ነገር በቃልና በተግባር ከማስተማር በመጨቃጨቅ አስጨብጣለሁ እንዳይል መጠንቀቅ አለበት ። ቀድሞውኑ የሚጨቃጨቅ ሰው ኤጲስ ቆጶስ ሊሆን አይገባውም ። በመጨቃጨቅ እየተሰለቸ ይመጣል ። አብረውት የሚሠሩትን አገልጋዮች ያሰድዳል ። ሰዎች ያለ ጥፋታቸው ራሳቸውን እንዲጠራጠሩ ያደርጋል ። ደግሞም በእግዚአብሔር ረድኤት እንጂ በእርሱ ቊጣ ሰዎች አይለወጡም ። ጨቅጫቃ ከሆነ ግን ሰውን በቊጣዬ እለውጣለሁ ብሎ የመንፈስ ቅዱስን ድርሻ ይወስዳል ። የሰዎችን ነጻ ፈቃድ ይጋፋል ። ይህ ደክሞ ማድከም ነው ።
ምስክርነትን ጭቅጭቅ የሚያደርጉ ሰዎች አሉ ። ያማረውን ቃለ ወንጌል ሰዎች እንዲጠሉ ያደርጋሉ ። ስብከትን ጭቅጭቅ ፣ ምክርን ንዝንዝ ማድረግ አይገባም ። ብዙ ልጆች ከቤት የሚወጡት በዚህ ምክንያት ነው ። አንድን ነገር ደጋግሞ ማውራት ፣ አዲስ አሳብ ማምጣት አለመቻል ጭቅጭቅ ነው ።ዘወትር አንድ አዲስ ነገር ለማወቅ መጣር ከጭቅጭቅ ያድናል ።
አቤቱ ሆይ ፈውሰን ።
1ጢሞቴዎስ 41
ጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ