የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የምሕረቱ አደባባይ ነኝ

“ስለዚህ ግን ፥ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግሥቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ፥ ምሕረትን አገኘሁ ።” 1ጢሞ. 1፡16
ደብተራ ኦሪት የተባለችው የመጀመሪያይቱ መቅደስ ሦስት ክፍሎች ነበሩአት ። የመጀመሪያው አደባባይ ሲባል ፣ ሁለተኛው ቅድስት ፣ ሦስተኛው ቅድስተ ቅዱሳን ይባላል ። አደባባዩ ዐውደ ምሕረት ነው ። ሁሉ የሚያየው ነው ። አደባባዩ ሁሉም ማለት ምእመኑና ካህኑ የሚረግጡት ነው ። አደባባዩ ወደ ቅድስትና ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ማለፊያና መዘጋጃው ነው ። በአደባባዩ ላይ ሁለት ንዋያተ ቅድሳት አሉ ። የመጀመሪያው የናሱ መሠዊያ ሲሆን ሁለተኛው የመታጠቢያው ሰን ነው ። የናሱ መሠዊያ የኃጢአትና የምስጋና መሥዋዕት የሚቀርብበት ነው ። የናሱ መሠዊያ ላይ ያለው ፍም በቅድስት ውስጥ ያለው የዕጣኑ መሠዊያ ላይ የሚቀርበው ዕጣን የሚጤስበት ነው ። በመሠዊያው በኩል የማያልፍ እንደሌለ በክርስቶስ ቤዛነት በኩል ካላለፈ ማንም ወደ ሕይወት መቅረብ አይችልም ። ምእመኑም ካህኑም በመሠዊያው በኩል ያልፋሉ ። ንጹሕ ኅሊና ለማግኘት በመሠዊያው በኩል ማለፍ ግድ ይላል ። የክርስቶስ ደም የቆሸሸ ኅሊናን የሚያነጻ ፣ የደፈረሰ ሰላምን የሚመልስ ነው ። በደሙ በኩል ካልሆነ ማንም ሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም ። መሠዊያው ጋ ሲደርስ ሁሉም ሰው ኃጢአቱና የእግዚአብሔር ምሕረት ትዝ ይለዋል ። እንዲሁም የክርስቶስ መስቀል ፊት ስንቆም ማንነታችን በልኩ ይታየናል ። ወዲያውም ልባችን ለንስሐ ዘንበል ይላል ፣ የፈሰሰው የክርስቶስ ደምም ስርየትን ይሰጠናል ። በቅድስት ውስጥ ያለው የዕጣኑ መሠዊያ በጠዋትና በማታ ዕጣን ይጤስበት ነበር ። ይህም የጸሎት ምሳሌ ነው ። ዕጣኑ ግን የሚጤሰው በመንደር እሳት ሳይሆን በናሱ መሠዊያ ላይ መሥዋዕትን ባሳረገው ፍም ነው ። ጸሎትም አምልኮትም ሊቀርብ የሚገባው በቀራንዮ ፍቅር ነው ። በመንደር እሳት በዘመናዊ አምልኮ እግዚአብሔር አይከብርም ። የናሱ መሠዊያ ላይ የኃጢአትና የምስጋና መሥዋዕቶች ይቀርቡ ነበር ። መሠዊያው ስርየትና ምስጋናን ያውጃል ። የክርስቶስ መስቀልም ስርየትና ምስጋናን ያሳስባል ።

ዐውደ ምሕረቱ ወይም የምሕረት አደባባዩ ላይ የምናገኘው ሁለተኛው ንዋየ ቅዱስ የመታጠቢያው ሰን ነው ። የመታጠቢያው ሰን መስታወትና ውኃ ነበረው ። በመስታወቱ ቆሻሻውን ያየው ካህን በውኃው በመታጠብ ለአገልግሎቱ ብቁ ይሆናል ። አንድ አገልጋይ ራሱን በቃሉ ማየትና በመንፈስ ቅዱስ ንጹሕ ልቡናን ገንዘብ ማድረግ ይኖርበታል ። ዐውደ ምሕረቱ ይህን ሁሉ ይናገራል ። ዐውደ ምሕረቱ ሽፍንፍን የሌለው ሁሉ የሚያየው ነው ።
የደብተራ ኦሪት ዐውደ ምሕረት ዛሬ የለም ። ሐዋርያው ጳውሎስ የእኔ ሕይወት ዐውደ ምሕረት ነው ። የእግዚአብሔርን ምሕረት የሚያውጅ ነው ይላል ። እግዚአብሔር አሳዳጁን ተሰዳጅ ፣ ገዳዩን አዛኝ ፣ ሽፍታውን ባሕታዊ ፣ ሌባውን መጽዋች ፣ አመንዝራውን ንጹሕ ሲያደርገው ፣ የተለወጠው ሕይወት ዐውደ ምሕረት ነው ። ሰዎች ጳውሎስን ሲያዩ የእግዚአብሔር ምሕረት እንደገና ዕድል እንደሚሰጥ ይገነዘባሉ ። ከትላንት በደላቸው የዛሬ መመለሳቸው ዋጋ እንዳለው ያውቃሉ ። ካፈርሁ አይመልሰኝ ብሎ ለጥፋት ታማኝ መሆን ሞኝነት መሆኑን ይገነዘባሉ ። እውነትን በተረዱበት ሰዓት መኖር የባከነውን ዘመን መካስ መሆኑን ያውቃሉ ። ጳውሎስ የመሰለው ነገር ክርስቶስ የኦሪት ተቃዋሚ ሁኖ ነበር ፣ እውነቱ ግን የኦሪት ፈጻሚ ነው ። በመሰለንና በእውነቱ መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ የጳውሎስ ሕይወት አደባባይ ሁኖ ያሳየናል ። በዐውደ ምሕረቱ ላይ የመታጠቢያው ሰን አለ ብለናል ። የጳውሎስ ሕይወትም መስታወት ሁኖ አጉል ቀናተኝነታችንን ያሳየናል ። ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ቀንቶ የእግዚአብሔርን ወንጌል አሳደደ ። ሐዋርያው ጳውሎስ የጥንቱን ከአዲሱ ኪዳን ለማስታረቅ በዐረብ ምድር ለሦስት ዓመት ጊዜ ሰጥቶ አጥንቷል ። የሰማውን ቶሎ የሚናገር ሳይሆን የሚያሰላስል ነበር ። ለአገልግሎት ብቁ ለመሆንም የሰሙትን ከማወጅ በፊት በቅጡ ማየት አስፈላጊ ነው ። ይህን ሁሉ የሚነግረን የጳውሎስ ሕይወት ዐውደ ምሕረት ስለሆነ ነው ።
“የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን” ይላል። የዘላለም ሕይወት ለማግኘት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ያስፈልጋል ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታሪክ ውስጥ የተከሰተ ድንቅ መምህር ነው ብለው የሚያምኑ አሉ ። የሞራል አብዮትን ያመጣ የፍቅር ሰው እንደሆነም የሚናገሩ አሉ ። እርሱ ግን አምላክ በመሆኑ አዳኝ ፣ ቤዛ በመሆኑም ሕይወትን ከጥፋት የሚጋርድ ነው ። ብዙ ኦሪታውያን ለሕጋቸው ቀንተው ክርስቶስን ሰቅለውታል ። ሐዋርያው ጳውሎስም ምናልባት በዚያ ሸንጎ ላይ ሳይኖር አይቀርም ። በዓይኑ አይቶ የገፋውን ክርስቶስ በራእይ ቢያየው በደማስቆ መንገድ ላይ ተማረከለት ። ጌታችን ካረገ ከስምንት ዓመት በኋላ ሐዋርያው ወደ ክርስትና ተመለሰ ። ሕይወቱን እያዩ ብዙዎች ወደ ወንጌል ቢመለሱ ሐዋርያው ናፍቆቱ ነው ። ምሳሌ እንድሆን ይላል ። ሰው ምሳሌ የሚሆነው ባደረገው መልካም ነገር ነው ። ሐዋርያው ግን በተቀበለው ምሕረት ምሳሌ እንድሆን ይላል ። እግዚአብሔር የሐዋርያውን ሕይወት የምሕረት ማስተማሪያ አደረገው ።
“ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግሥቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ፥ ምሕረትን አገኘሁ” ይላል የኃጢአተኞች ዋና ነኝ ማለት ትልቅ ትሕትና ነው ። የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነውና ሐዋርያው ራሱን ለማጽደቅም አልፈለገም ። ዝቅተኛውን ቦታ መርጧልና የጋበዘው ጌታ ትልቁን ወንበር ሰጥቶታል ። አይገባኝም ብሏልና ይገባሃል ተብሎ ተሹሟል ። ትዕግሥቱን በእኔ አሳየ ይላል ። እስኪመለስና እስኪያውቀው ድረስ በተስፋ ጠብቆታልና ትዕግሥቱን ያደንቃል ። ከተመለሰ በኋላ የተቀበለውን ምሕረቱን ሊያመሰግን ይነሣሣል ። ሐዋርያው ይህን ሁሉ የሚናገረው የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ ወድደው ምሕረቱ ለሰብአ ዓለም ነው ፣ እኛን ግን በሥራችን ዋጋ ይክፈለን ለሚሉ ተግሣጽ እንዲሆን ነው ።
ብዙዎቻችን ክርስትናን የምንኖረው በታላቅ ደስታ አይደለም ። ልንተወው ሲገባን ያልተውነው ክፉ ነገር አለ ። ልናደርገው ሲገባን ያላደረግነው መልካም ነገር አለ ። በዚህ ምክንያት ሕይወታችን ለሌሎች ምሳሌ አይደለምና በእግዚአብሔር ደስ ቢለንም በራሳችን እናዝናለን ። ይህ ተገቢ ኀዘን ነው ። ባደረግነው ምሳሌ ባንሆንም በተደረገልን ነገር ምሳሌ ሆነናልና እግዚአብሔር ይመስገን ። እገሌ እንኳ ፣ እገሊት እንኳ የእግዚአብሔር ሰዎች ሆኑ ብለው ሰዎች እኛን በማየት የእግዚአብሔርን ምሕረት ያደንቃሉ ። ሕይወታችን የምሕረቱ አደባባይ ሁኖ ለማመን ድፍረት ያጡትን ኃጢአተኞች ያደፋፍራል ። አዲስ መድኃኒትን መውሰድ ሰው ሁሉ ይፈራል ። ብዙዎች ሲሞክሩት ግን ለመውሰድ ይደፍራል ። ጳውሎስን ያዳነው መድኃኒት እኔንም ያድነኝ እስኪሉ የሐዋርያው ሕይወት ምሳሌ ሁኗል ።
ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ ለመታየት ባንፈልግም ፣ አስቀድሰን በቶሎ ውልቅ ብንልም ፣ ሰዋራ ቦታ ሂደን ብንቆርብም ፣ በድብቅ ምጽዋት ብንሰጥም ፣ ሰው ሳያየን ብንጸልይም ፣ ምንም ምልክት ሳይታይብን መጽሐፍ ቅዱስን ብናጠናም ያለነው በእይታ ውስጥ ነው ። ጌታችን የክርስቲያንን ሕይወት ተራራ ይለዋል ። መደበቅ አይችልም ።   በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም” ብሏል ። /ማቴ. 5፡14/ ። ሰዎች ሲያዩን ለእግዚአብሔር ከመሥራታችን በፊት እግዚአብሔር የሠራልንን ያያሉ ። እኔም ተስፋ አለኝ ብለው ለመዳን ይከጅላሉ ። እያንዳንዱ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ወይም የምሕረቱ አደባባይ ነው ።
ገቢና ወጪያችን ሳይመጣጠን ስንኖር ይህን ያደረገው ምሕረቱ ነው ። ድጋፎቻችን ተሰብረው ያልወደቅነው በምሕረቱ ነው ። የሚዝቱብን በዝተው ያልጠፋነው በምሕረቱ ነው ። አለቀላቸው ስንባል እንደገና አዲስ ሰው የሆነው ከምሕረቱ የተነሣ ነው ። የነደደው እሳት ወላፈኑ አጠገባችን ያሉትን ሲገድል ፍሙ ግን ልብሳችንን እንኳ ያላጠቆረው ከምሕረቱ ተነሣ ነው ። “የምጣዱ ሳለ የእንቅቡ ተንጣጣ” እንዲሉ እሳቱ የሚነድብን እኛ ታግሠን ፣ በሩቅ ያሉት የሚጮኹት ምሕረቱ ስላስቻለን ነው ። ያለ ቀልባችን ሁነን ስንበርር አደጋውን ያለፍነው በምሕረቱ ነው ። በረሀብ ዘመን የጠገብነው ፣ በሚቻልበት ዘመን ያጣነውን በማይቻልበት ዘመን ያገኘነው በምሕረቱ ነው ። ዘመድ ያላቸው ሲሸበሩ ምልምል ዛፍ የተባልነው እኛ የተረጋጋነው በምሕረቱ ነው ። ያገር ልጅ ጠላት ሁኖን ባዕድ የተዛመደን በምሕረቱ ነው ። ሕይወታችንና ኑሮአችን የምሕረቱ አደባባይ ነው ። እግዚአብሔር ማን እንደሆነ ለማወቅ እኔን ተመልከቱ እስክንል ድንቅ የተደረገልን ፣ በጥበቡ የኖርን ነን ።
እነዚያ የባቢሎን ምርኮኞች ፣ አገር አልባ የሆኑት ፣ መጽናኛ መቅደሳቸው የፈረሰባቸው ፣ ንጉሥና ካህና የራባቸው ፣ ሽማግሌ አጥተው የትላንቱ መስተዋት የተሰበረባቸው እንዲህ ብለው ዘመሩ፡- ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው ርኅራኄው አያልቅምና ።” /ሰቆቃወ ኤር. 3፡22/

በምሕረትህ ባለጠጋ የሆንኸው ፣ ዛሬም እኔን ለመሸከም ያልሰለቸኸው ውድ አምላኬ ተመስገን!
1ጢሞቴዎስ /18/
ኅዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ