ማጥፋት ስትችል ያዳንከን ሆድህ የማይጠናው ፣
ጉስቁልናን የምትለውጠው የድሆች ቀን ፣
ጎኑ ባዶ ለሆነው ጽኑ ረዳት ፣
በራሱ የሞተ ባንተ የሚድንብህ ፣
እልልታ ከቤቱ ለራቀው ዝማሬው ፣
የሚሸፍን እውነት ያለህ ከባቴ አበሳ ፣
ሸክም ለተጫነው ቅለቱና ዕረፍቱ ፣
ማዕበል ላስጨነቀው ወደቡ ፣
ያልፈለገህን በመፈለግ የከበርህ ፣
ትልቅነትህ ኩራት የሌለበት ፣
ፈቃድህ ሁሉን የሚገዛ ፣
የኑሮ ጩኸት ሲያስጨንቅ ፀጥታችን ፣
ለተመረዘች ነፍሳችን መድኃኒት ፣
የፈረሱ ቅጥሮችን የሠራህ ፣
የሄደውን ወዳጅ የመለስህ ወዳጅ ፣
ካሰቡልን ይልቅ የምታስብልን የዘመድ አውራ ፣
ምሕረትህ ቀና የሚያደርግ ቀዩ ካባ ፣
የፈለጉትን እስረኞች የምትፈታ የመኰንኖች መኰንን ፣
መቼ ነው የማርፈው ለሚሉህ የደስታ አገራቸው ፣
የሁልጊዜ ቅዱስ የማትሳሳት ፣
በማዳንህ የተደነቅህ ፣ ፈውስ ጉዳት የሌለበት ፤
በሟችና በገዳይ መካከል የምትገባ የእሳቱ ውኃ ፣
የታመኑብህን የምትክስ የፍቅር ዳርቻ ፣
አረማመድህ የማይታወቅ ጎምላላ ፣
ደጁን የምታንኳኳ ጠባቂ ፣ ጥፋት ሲመጣ አንቂ ፤
ዋጋ ለሌላቸው ዋጋቸው ፣ ውሉ ለጠፋቸው ብልሃታቸው ፤
የሚፈሱ እንባዎች የሚገደቡልህ ፣ ባለ ችንካር እጁ ፤
ሰውን ሰው የምታደርገው የመራራው ጣዕም ፣
ጥያቄን የማትፈራው የሕይወት መምህር ፣
የሐኪሙ ሐኪም ፣ የድካም ቀንን የምታውቅ ፤
የሚፈሩህን የምታከብረው ፣ ሲወዱህ የማትኮራው ፤
ለንጉሥ ንጉሥ መባልን የሰጠኸው ፣
ስላለፈው የሚጠይቁህ ብሉየ መዋዕል /ዘመን ጠገቡ፣
ስለ ነገ የሚያምኑህ ፣ የመንገድ ስንቁ …
አንተ እግዚአብሔር የእኔ አምላክ ነህ ! ተመስገን !
ሲቻል በቃል ፣ ሳይቻል በዝምታ ተደነቅ ፤
እባክህ ከምስጋና ማማዬ አልውረድ ፤
ለዘላለሙ አሜን!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 7 ቀን 2018 ዓ.ም.