የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የምድረ በዳው ወዳጅ

ያዕቆብም ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ” ማቴ. 1፡2 ።
“ያዕቆብ” የሚለው ቃል የሚደንቅ ነው ። ያዕቆብ አቅሙንና ጭምትነቱን እያሰበ ብዙ ዘመን ይህችን ዓለም የፈራ ሰው ነው ። በእናቱ ነጠላና በቤቱ ጣራ በታች ተሸፍኖ የኖረ ፣ ፍርሃትም ያደራበት ሰው ነበር ። እንዴት ከዚህች ዓለም ጋር ታግዬ እንጀራ እበላለሁ ብሎ ቢፈራም የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ እንደምታደርግ ያምን ነበር ። ስለዚህ በምስር ወጥ የወንድሙን ብኵርና አባቱን በማታለልም የወንድሙን ምርቃት ወስዷል ። ምርቃትና በረከትን ይዞ ከአባቱ ቤት ተሰደደ ። ገንዘብ ይዞ የተሰደደው የጠፋው ልጅ ሲመለስ ድሀና ጎስቋላ ነበር ። ሉቃ. 15፡17 ። ምርቃት ይዞ የተሰደደው ያዕቆብ ግን ሲመለስ ባለጠጋ ነበር ። እግዚአብሔር በምርቃትና በበረከት መንገድ ይሠራል ። ምርቃትና በረከት የመጀመሪያው ተመራቂውና ተባራኪው አባት እንዳለው ያሳያል ። ለመመረቅና ለመባረክ አባት የግድ ያስፈልጋል ። አባት የሌለው አባት እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው ይባላል ። አባት ማለትም በሥጋ የወለደ ብቻ ሳይሆን በወንጌል የወለዱ አባቶች ማለትም ነው ። ሁለተኛው ምርቃትና በረከት እግዚአብሔር የሚሠራበት ሰንሰለት ነው ። ምርቃቱና በረከቱ ሳይቋረጥ መሄድ ወደ ትውልድ መውረድ አለበት ። ይህ የበረከት መንገድ በአዲስ ኪዳንም “አንብሮተ ዕድ” ወይም እጅ መጫን በመባል ትልቅ ስፍራ ተሰጥቶታል ። ለመባረክ አስደሳች ልጅ መሆን ያስፈልጋል ። ሁለተኛ በመስመሩ ላይ መገኘት ያስፈልጋል ። አባት ካለ ልጅ መሆን ፤ መምህር ካለ ደቀ መዝሙር መሆን ግድ ያስፈልጋል ።
ከሃያ ዓመታት የስደት ዘመን በኋላ ሲመለስ ሌጣው ያዕቆብ ብዙ ፣ ድሀው እስራኤል ባለጠጋ ፣ ምስኪኑ ይሹሩን ተፈሪ ነበር ። “ያዕቆብም” የሚለው ቃል በውስጡ ትልቅ ምሥጢር አለው ። የዘመናት ታሪክ በአንድ ፊደል ውስጥ ተሸሽጓል ። “እግዚአብሔር ይመስገን” ስንል በውስጡ ብዙ ነገሮች አሉ ። “እርሱ ያውቃል” ስንል በውስጡ ብዙ እንፋሎት አለ ። “እግዚአብሔር አለ” ስንል ብዙ ተግዳሮት ከፊት እንደ ቆመ ያሳያል ። “እግዚአብሔር ይመስገን” ስንል ለሰው ሰላምታ የሰጠነው መልስ ይመስላል ። ስለሆነውም ስላልሆነውም ነገር እያመሰገንን ነው ። “እግዚአብሔር ያውቃል” ስንል ጨለማችንንና ተራራችንን እየተናገርን ነው ። “እግዚአብሔር አለ” ስንል ያስፈራንን እያስፈራራን ነው ።
ብዙ ቅዱሳን ከአገራቸው ይልቅ እግዚአብሔርን በባዕድ ምድር ላይ አግኝተውታል ፣ አገልግለውታል ። እግዚአብሔርም ስደትን እንደ ማሰልጠኛ ጣቢያ ይጠቀምበታል ። ስደት እንደ ገዳም የሆነላቸው በቀንና በሌሊት በቃሉ የሚረሰርሱ ብዙ ወገኖች አሉ ። እነዚህ ሰዎች ከዘመድ ሲርቁ ወደ እግዚአብሔር በጣም ተጠጉ ። ከአባት ሲርቁ እግዚአብሔርን አባት ማድረግ ፣ ከዘመድ ሲርቁ ያለኸኝ አንተ ነህ ማለት ግድ ነው ። ያዕቆብም ባዶውን ወጥቶ በበረከት ተመለሰ ። ያገኘው ነገር እርካታ እንዳልሰጠው ታሪኩ ይነግረናል ። መርካት በእግዚአብሔር ብቻ ነው ። ያቀፉት ነገር አያረካም ፣ ያቀፈን እግዚአብሔር ብቻ ያረካል ። የገባንበት መኪና አያስደስትም ፣ በልባችን የገባው እግዚአብሔር ግን ያስደስታል ። መኪና ልብ ውስጥ ለመግባት ግዙፍ ነው ፣ እግዚአብሔር ልባችን ውስጥ ለመግባት መንፈስ ነው።
ያዕቆብ ብቻውን ቢወጣም 12 የነገድ አለቆችን ወለደ ። እነዚህ እስራኤልን የመሠረቱ ናቸው ። እነዚህ የ12ቱ ደቀ መዛሙርት ምሳሌ ናቸው ። እግዚአብሔር እንዲህም ይባርካል ። ስደተኛንም ይሰበስባል ። ብልሃት ለሌላቸውም እርሱ ይጠበብላቸዋል ። ለካ ሞኞችም ብልህ አምላክ አላቸው !? ከ12ቱ የያዕቆብ ልጆች ክርስቶስ በሥጋ የመጣው ከይሁዳ ነገድ ነው ። ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ የተባለለት እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ራእ. 5፡5 ። ሁላችንም ብንሆን ክርስቶስ ከይሁዳ ነገድ ከሚመጣ ከደጉ ከዮሴፍ ነገድ ቢመጣ እንመርጣለን ። እግዚአብሔር ግን የሚፈልገውን ሰው ፣ ማንም አይመርጥለትም ። እኛ ብንሆን ያደላደልነው ጴጥሮስን የአሕዛብ ፣ ጳውሎስን የአይሁድ መምህር እናደርግ ነበር ። የእግዚአብሔር ሥራ ግን ከችሎታ ይልቅ በጸጋ የሚሠራ ነው ። ዛሬ ትልቅ ችግር የመጣው ባለሙያዎች ባለጸጋዎችን በመግፋታቸው ነው ። አንዳንዶችም በዓለም ባካበቱት እውቀት ቤተ ክርስቲያንን መምራት እንችላለን በማለታቸው ነው ። በብርሃን ላይ ያየንበትን እይታ ጠብቀን በጨለማ ውስጥ ማየት እንችልም ። በጨለማ ውስጥም ብርሃን ያስፈልጋል ። በዓለም ውጤታማ በሆንበት ነገር በአገልግሎት ውጤታማ መሆን ፣ መንፈሳዊውን ውጊያ ማሸነፍም አይቻልም ።
የይሁዳ ነገድ ነገሥታት የሚወጡበት ነገድ ነው ። የነገሥታት ንጉሥ ክርስቶስ ከዚህ ዘር ስለሚወለድ ይህ ነገድ የነገሥታት መውጫ ሆነ ። ይሁዳ ክርስቶስን ንጉሥ አላደረገውም ፣ ክርስቶስ ግን ይሁዳን የነገሥታት መውጫ አደረገው ። እኛም ለእግዚአብሔር ክብር አንጨምርለትም ፣ ብንዘምር ብንቀደስ ክብር ይጨመርልናል እንጂ ። ጨው ሆይ ለራስህ ስትል ጣፍጥ አሊያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል ።
ስደተኛው ያዕቆብ በምድረ በዳ ወዳጅ አገኘ ። እርሱም እግዚአብሔር ነው ። በስደት ያላችሁ ከዘመድ እንጂ ከእግዚአብሔር አልራቃችሁምና ደስ ይበላችሁ !
ዘመናችሁ ይባረክ !
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ