የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የምድሪቱ ሰንበት

እንኳን ለጾመ ነነዌ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ !
 “እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው ፡- ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው ። እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር ሰንበት ታድርግ ። ስድስት ዓመት እርሻህን ዝራ ፥ ስድስት ዓመትም ወይንህን ቍረጥ ፍሬዋንም አግባ ። በሰባተኛው ዓመት ግን ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ፥ ለእግዚአብሔር ሰንበት ፥ ትሁን እርሻህን አትዝራ ፥ ወይንህንም አትቍረጥ ። የምድራችሁን የገቦ አትጨደው ፥ ያልተቈረጠውንም የወይንህን ፍሬ አታከማች ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ዓመት ይሁን ። የምድርም ሰንበት ለአንተ ፥ ለወንድ ባሪያህም ፥ ለሴት ባሪያህም ፥ ለምንደኛውም ፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ለመጻተኛም ምግብ ይሁን ። ለእንስሶችህም ፥ በምድርህም ላሉት አራዊት ፍሬዋ ሁሉ መኖ ይሁን ።”/ዘሌዋ. 25፥1-7/ ።
ዘሌዋውያን ምዕራፍ 25 ድንቅ ክፍል ነው ። ስለ ምድሪቱ ሰንበትና ስለ ዓመታት ሰንበት እንዲሁም ስለ መቤዠት የሚናገር ምዕራፍ ነው ። እግዚአብሔር አምላክ ይህን ዓለምና በውስጡ የሚኖሩትን የሰው ልጆች ሲፈጥር በማረፍ እንዲታደሱ አድርጎ ነው ። ሰውና በምድር ላይ የሚገኙ ፍጥረታት በማረፍ ለቀጣዩ ጊዜ አቅም ይሰበስባሉ ። ዳግመኛም ስለ ሌሎች ከርታቶች ለማሰብ ጊዜ ያገኛሉ ። የእግዚአብሔርንም በረከት ያውቃሉ ። እግዚአብሔር የሚያኖር አምላክ ነው ።እግዚአብሔር እንኳን ስለ ሰው ልጅ ስለ ምድሪቱም ግድ ይለዋል ። ጨርሰው እንዳይበሏት ያዝንላታል ። አዎ መሬት መርገጫ ቦታ ፣ ርስት ጉልት ሀብት ፣ መሮጫ ሜዳ ፣ መመገቢያ ገበታ ፣ መቀበሪያ ዓለም ናት ። ምድር ማለት ማኅደር ማለት ነውና ሁሉን ከድናለች ። ሁሉንም አሳድራለች ። ላሟ የደረቀ ጡቷን ሲመጠምጡት ጥጆቹን ዞር ያደርጓቸዋል ። እንዳይገድሏት ያዝኑላታል ። መሬትም ጨርሳ እንዳትሞት እግዚአብሔር አዘነላት ። ሰዎች መጥምጠው እንዳያጠፏት አዘዘ ።
ፍጥረት ተደጋግፎ የሚቆም በመሆኑ የአንዱ ማዝመም የሁሉም መውደቅ ሊሆን ይችላል ። ፍጥረት ሚዛናዊነትን ካልጠበቀ ሕይወት በምድር ላይ ቀጣይ አይሆንም ። ፍጥረት ተመጋጋቢ ነው ። አንዱ አንዱን ይጠብቃል ። እጽዋትን ስንጠብቅ ፣ ምድሪቱን ከብክለት ስንከላከል ካደረግነው እጥፍ በረከት እንቀበላለን ። ፍጥረት ለጋስ ነውና ከሰጠነው በላይ ይሰጠናል ። ፍቅር ስንሰጣቸው እንስሳቱ ከሰጠናቸው በላይ ይወዱናል ። ስንንከባከባቸው ከበሉት በላይ ወተት ይሰጡናል ። ፍጥረት የያዘውን አይለቅም ። እንደ ሰው መዋዠቅ የለበትም ። ጌታው ማን እንደሆነ እንስሳው ካወቀ ፣ ደህና መሬት ላይ አበባው ካደገ እነዚህ ሁሉ የያዙትን አይለቁም ። ሁለት መቶ ዓመታት የሞላቸው ዛፎች አሉ ። ሁሉም በስፍራው አለ ። ሁሉም በክልሉ ይኖራል ። ወፎች በሰማይ ፣ ከብቶች በምድር ላይ ፣ ዓሦች በባሕር ላይ … ይኖራሉ ።
የእስራኤል ልጆች ገና የተስፋይቱን ምድር ሳይወርሱ እግዚአብሔር ስለ ተስፋይቱ ምድር ሕግጋት ይነግራቸዋል ። እግዚአብሔር ፍጻሜው ላይ ሁኖ ያዋራቸዋል ። የእግዚአብሔር ተስፋ የሕዝቡ ኃይል ነው ። የእስራኤል ልጆች በግብጽ 430 ዘመን በባርነት ኑረዋል ። እግዚአብሔር ያለ ዕረፍት የኖሩበትን ዘመን ፣ የሠሩበትን ዓመታት አሰበና 40 ዓመት በምድረ በዳ አሳረፋቸው ። ወደ ከነዓን ሲገቡ በቀጥታ ሥራ ይገጥማቸዋል ። እግዚአብሔር ግን የእፎይታ ጊዜ አደረገላቸው ። እርሱ በመዓቱ ውስጥ ምሕረት ፣ በቊጣው ውስጥ ትዕግሥት አለው ። አዎ ከግብጽ ሳይወጡ ደመወዛቸውን አሰጣቸው ። የግብጻውያንን ወርቅና ብር በዘበዙ ። እግዚአብሔር የሠራተኞች መብት አስከባሪ ነው ። አሁን ደግሞ የዓመት ፈቃድ ወጥተው አያውቁምና በምድረ በዳ 40 ዓመት እያበሰለ አሳረፋቸው ። እነርሱ እንዳረፉ ምድርን ያሳርፏት ዘንድ አዘዘ ። እግዚአብሔር በዚህ ምድረ በዳ ላይ የሚያዝዛቸው በተስፋይቱ ምድር ስለሚጠብቁት ሕግ ነውና ተስፋውን መውረሳቸው እርግጥ ነው ። እርሱ መጀመሪያው ላይ ስለ መጨረሻው ይናገራል ። ነገር ግን የጠላት ብዛት ከተስፋው ምድር አላስቀራቸውም  ። የራሳቸው አለማመን ግን አስቀራቸው ።
 የምድሪቱ ሰንበት ምንድነው ስንል ? ስድስት ዓመት ያርሱና በሰባተኛው ዓመት ምድሪቱን አያርሷትም ፣ ያሳርፏታል ። የምድሪቱን ሰንበት የሚያከብሩት በአራት ምክንያት ነው ፡-
1-  ምድሪቱ እንድታገግምና የበለጠ ፍሬ እንድትሰጥ ፤
2-  ለድሆችና ለጦም አዳሪዎች ምግብ እንዲሆን ፤
3-  የእግዚአብሔርን በረከት እንዲያዩና እንዲለማመዱ
4-  ባሮችና አሽከሮች የዓመት ፈቃድ እንዲያገኙ ነው ።
1- ምድሪቱ እንድታገግምና የበለጠ ፍሬ እንድትሰጥ ፤
ስድስት ዓመት ሙሉ የታረሰችው ምድር በሰባተኛው ዓመት ስታርፍ ራሷን ታድሳለች ። የዶማ ፣ የማረሻ ስለት ካልነካት በሚረግፉት ፍሬዎች እርሷ በተራዋ ተመጋቢ ትሆናለች ። አንድ ዓመት ዐርፋ ስትነሣ እንደገና ለስድስት ዓመት ታጠግባለች ። አሊያ ሰባተኛውን ዓመት ጨምረው ቢያርሱባት ለጊዜው እያጣጣረች ትመግባቸዋለች ። ቆይቶ ግን ትጨነግፋለች ። እግዚአብሔር ለእኛ ስለ ፈጠራት ምድር ግድ ካለው ለእኛማ ይበልጥ ግድ ይለዋል ። የምድሪቱ ሰንበት በሰባተኛው ዓመት ሲሆን የሰው ሰንበት ግን በሰባተኛው ቀን ነው ። ምክንያቱም ምድሪቱ ማረሻ የሚነካት በዓመት ሁለት ጊዜ በመሆኑ በሰባት ዓመት ማረፏ ተገቢ ነው ። በየቀኑ የኑሮ ማረሻ የሚነካው የሰው ልጅ ደግሞ በየዕለቱ ቃሉን ፣ በየሰንበቱ ኅብረት ማግኘት አለበት ። ምድሪቱ ሳይነኳት እንዲሁ ለራስዋ ሲተውአት ታገግማለች ። ለሌሎች የምትሰጠውን ኃይል ለራስዋ ታደርገዋለች ። እንዲሁም የሰጠችውን ፍሬ መልሳ ስትመገብ ብስባሹ እንደገና ያድሳታል ። በየዕለቱ የምትመግብ ምድር በሰባት ዓመት ልመገብ ትላለች ። ብዙ ሰጥታ ጥቂት ቢሰጧት ወጉ አይደለም ወይ ?
ሰው ከአፈር የተሠራ ነው ። ምድሪቱ እንደሚያስፈልጋት እርሱም ያስፈልገዋል ። አፈር ነውና ። አፈር ድንጋይ አለው ፣ ሰውም አጥንት አለው ። አፈር ሣር አለው ሰውም ፀጉር አለው ። አፈር ሥር አለው ሰውም ጅማት አለው ። አፈር ውኃ አለው ፣ ሰውም ደም አለው ። አፈር ወይም ምድር ሦስት አራተኛው ውኃ ነው ፣ ሰውም ሦስት አራተኛው ውኃ ነው ። ሰው ራሱን የሚያይበት ጊዜ ያስፈልገዋል ። ጽሞና ያሻዋል ። ምድሪቱ የሰጠችው ፍሬ መልሶ ሲረግፍባት እንደምትበረታ እንዲሁም ሰዎችም የሰጡንን ፍቅር ፣ የሰጡንን ማጽናኛ መልሰን ስንሰጣቸው ይበረታሉ ። ከእርሱ የሰማሁት አይደል መልሼ እንዴት እሰጠዋለሁ አትበሉ ። እውነት ዘወትር አዲስ ናት ። እውነት ደግሞ የማንም የግል ሀብት አይደለችም ። እውነት እንደ ምድር የጋራ ሀብት ናት ።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን በሰባተኛው ዓመት ላይ ሙሉ ዓመት ያርፋሉ ። ለዕረፍት ለምርምር እንዲውልላቸው ነው ። አሊያ አንዴ ያወቁትን ብቻ አውቀው ይኖራሉ ። ጊዜ ባገኝ ይህን እሠራ ነበር የሚሉትን ነገር እንዲሠሩም ይረዳቸዋል ። እግዚአብሔር ከሩጫችን ከወከባችን ወጥተን እንድናርፍ ይፈልጋል ። በዚያም እውቀታችን ይሰፋል ። ይህም ባደርግ ኑሮ እያልን ቅር የሚለንን ነገር ለማድረግ እንችላለን ።
እግዚአብሔርን ማገልገል መልካም ነው ። ትልቅም ተግባር ነው /1ጢሞ. 3፥1/ ። ሁልጊዜ እንድንሮጥ ግን አልተፈቀደም ። ራሳችንን የምናይበት ፣ ስንጎድል የምንሞላበት ጊዜ ያስፈልገናል ። ሐዋርያው ጳውሎስ ፡- “ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ።”  ብሏል /1ቆሮ. 9፥27/ ። አሥራ አራት መልእክታትን የጻፈ ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ወንጌልን የሰበከ ፣ … ሰው ከሥጋ ጥድፊያ ተለይቶ መንፈሱን የሚመግብበት ጊዜ ነበረው ። መኪና ያለ ማቋረጥ ሊነዳ ይችላል ፣ ነገር ግን ዐረፍ ብሎ የማይጠገን ከሆነ አደጋ አለው ። በየአምስት ሺህ ኪሎ ሜትር ደኅንነቱ የማይመረመር ከሆነ ፣ የተጎዳ ቀን ወጪው ከፍ ያለ ነው ። ዕረፍት የሌላቸው የኑሮና የአገልግሎት መስኮች በግድ ማረፍ የመጣ ቀን ለማገገም አስቸጋሪ ናቸው ። “ካለቀ ቁጠባ ፣ ከከሱ ቅለባ” አይሆንም ። ንሥር በአርባ ዓመቱ ራሱን ያድሳል ። ራሱንም የሚያድሰው ጭው ባለ ሸለቆና ገደላማ ስፍራ ላይ ነው ። በዚያም ያረጀውን የአካል ክፍል በሙሉ ነቃቅሎ ይጥላል ። ንሥር ራሱን ባያድስ ዐሥር ዓመት በጉልበት መኖር ይችላል ። ራሱን ካደሰ ግን ዐርባ ዓመት መኖር ይችላል ። ለራሳችን የጽሞና ጊዜ ካልሰጠነው ኃይላችንን አሟጠን ትንሽ መሄድ እንችላለን ። ከቆምን ግን አደገኛ ነው ። ነዳጁ ያበራበት መኪና መጓዝ ይችላል ። የሚጓዘው ግን ጥቂት ርቀት ነው ። ነዳጁ ፍጹም አልቆ አየር ከሳበ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው ። ሰው ሠራሽ ነገሮች ሁሉ ከሰው በመነሣት የተሠሩ ናቸው ። ሰው ሁለት ዓይን አለው ፣ መኪናም እንዲሁ አለው ። መኪና መስተዋቱን የሚያጸዳበት ውኃና መጥረጊያ አለው ፣ ሰውም ዓይኑን የሚያጥብ ጉም መሰል ነገር አለው ። መኪና ነዳጅ ይወስዳል ፣ ሰውም ይመገባል ። ሰው ሠራሽ ነገሮች በአብዛኛው ከተፈጥሮ የተኮረጁ ናቸው ።
የእስራኤል ልጆች የምድሪቱን ሰንበት ለተወሰኑ ዓመታት አከበሩና ከዚያ በኋላ ተዉት ። ለ490 ዓመታት ያህል ምድሪቱ ሰንበቷን አላከበረችም ነበር ። የ490 ዓመታት የምድሪቱ ሰንበት 70 ዓመት ይመጣል ። ሰባ ዓመት የፈጀው የባቢሎን ምርኮ ምድሪቱ ሰንበቷን እንድታከብር የተደረገ ሰማያዊ ፍርድ ነው ። “በኤርምያስም አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል እንዲፈጸም ፥ ምድሪቱ ሰንበትን በማድረግዋ እስክታርፍ ድረስ በተፈታችበትም ዘመን ሁሉ ፥ ሰባ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ፥ ሰንበትን አገኘች ።” ይላል /2ዜና 36፥21/። የሕይወታችንን ሰንበት ካላከበርን እንዲህ ሊፈጸም ይችላል ። ብዙ አውታታዎች ፣ እግዚአብሔር ብዙ በረከት የሰጣቸው ከርታቶች ማረፍ ባለመቻላቸው ይኸው በአልጋ ላይ አርፈዋል።  ይኸው በእስር ቤት ተቀምጠዋል ። ስግብግቦች ያላቸውን ይወረሱና እንዲያርፉ ይደረጋል ።
2- ለድሆችና ለጦም አዳሪዎች ምግብ እንዲሆን ፤
ምድሪቱ ሰንበቷን ማክበር ያለባት በሰባተኛው ዓመት የሚወድቀው ፍሬ ፣ የሚበቅለው እህል ለመጻተኞችና ለእንግዶች ምግብ እንዲሆን ነው ። መጻተኞች አገሬ እገባለሁ እያሉ ዘመን የተራዘመባቸውና ያልሞላላቸው ናቸው ። እንግዶች የኖሩበት አገር እንደ ጋለ ነሐስ አላስቀምጥ ብሏቸው ባርፍ ብለው ዞር ያሉ ናቸው ። ድሆች በአገር ውስጥ ያሉ ነገር ግን የገዛ አገራቸው ፊቱን ያዞረባቸው ናቸው ። ድሆች ሳይሰደዱ የተሰደዱ ናቸው ። እግዚአብሔር እነዚህ መጻተኞች ፣ እንግዶች ፣ የአገር ልጅ ድሆች አስቡ አለ ። ምክንያቱም እናንተም በግብጽ ስደተኞች ነበራችሁና ስደተኞችን ውደዱ በማለት ነው ። እግዚአብሔር ችግርን ፣ ስደትንና ረሀብን የሚያሳየን እንድናዝን እንጂ እኛ ካሳለፍነው ጋር እያነጻጸርን እንድንጨክን አይደለም ። አንድ አገር ላይ ሄደን መንገድ ሲጠፋብን ለማሰብ እንኳ የሚከብድ ግራ መጋባት ይገጥመናል ። እንግድነት የአንድ ዓመታቱን መከራ በአንድ ቀን ዕረፍት ለመካስ የሚደረግም ጥረት ነው ። ዕረፍት ላሻቸው ዕረፍት መስጠት ትልቅ ነገር ነው ። የምድሪቱ ሰንበት ያስፈለገው እነዚህን ምስኪኖች ለማሰብ ነው ።
ብዙ ምስኪኖችና ጦም አዳሪዎች ዛሬም አሉ ። ብዙ ሥርዓቶች የተለዋወጡት ድህነትን ከምድር ላይ እናጠፋለን ብለው ነው ። ማኅበረሰባዊው ርእዮተ ዓለም ፣ የዓለምን ሀብት በእኩል ማካፈል አልቻለም ። ሁሉንም ድሃ አድርጎ አስቀመጠው ። መዋዕለ ንዋይን አፍስሱ የሚለው ርእዮተ ዓለምም ጥቂቶችን የምድር ጌቶች አድርጎ ድሆችን ረመረማቸው ። ድህነትን ለማጥፋት የተጀመረው ርእዮተ ዓለም ሁሉ ድሃን በማጥፋት ተደመደመ ። ድህነት ቅነሳ ድሃ ቅነሳ ሆነ ። አስቀድሞ የዛሬ ሦስት ሺህ ዓመት እግዚአብሔር አምላካችን ፡- ድሆች ከምድሪቱ አያልቁምና ብሎ ተናግሮ ነበር ። ይኸው ዛሬም እየበዙ ነው ። ስለ ሰው መብት ያወሩ የነበሩ ስልጡን አገራትም በድሆች ላይ ሰማይ ጠቀስ አጥር ሠርተው አናስገባም አሉ ። ስለ ድሆች ማውራትና ማድረግ በጣም የተለያየ ነው ። ለድሆች ስለ ሠራን መስጠት በቂ አይደለም ፤ ለመስጠት መሥራት ያስፈልጋል ። የአንድ ዓመት ሥራዬ ለድሆች ነው ማለት ይጠይቃል ። የሰውን ረሀብ ሲሰሙ ቤታቸውን ሸጠው የሰጡ እንዴት የተባረኩ ነበሩ ። እኔ ተከራይቼ መኖር እችላለሁ ፣ እነርሱ ግን ከዛሬ በኋላ መኖር አይችሉም ያሉ ወገኖች በርግጥም የተባረኩ ናቸው ። በድሃ የሚጨክን ድሃ ነው ። ለዚህም ጭቁን የነበሩና ስለ ጭቆና ደከምን ያሉ የአፍሪካ ሰዎች መልሰው ድሃ አስጨናቂ ሲሆኑ ማየት ማመን ይከብዳል ። ሌላው ዓለም ከሌላው አገር እየሰረቀ አገሩን ይመግባል ፣ እነርሱ ግን የአፍሪካን ንብረት ወደ ባለጠጋ አገራት ያግዛሉ ። ንብ ማር የምትሠራው ለሰው ብላ አይደለም ። አንድ ቀን ዐርፌ እበላዋለሁ ብላ ነው ። ግን አትበላውም ። እነዚህም ወገኖች አይበሉትም ። ድሆችን የረሳች አገርና ቤተ ክርስቲያን ዕድሜአቸው እየተቀጨ ይሄዳል ።
እናንተ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ድሆች አስፈላጊ ናቸው ። ባለጠጎች የእናንተን ስብከት ለመስማት ጊዜ የላቸውም ። ከቃለ እግዚአብሔር ይልቅ አጫዋች ሰው ይፈልጋሉ ። እናንተ የምድር ነገሥታት ቤተ መንግሥቶቻችሁን የሚጠብቁ ወታደሮች ድሆች ናቸው ። እናንተ ባለጠጎች የድሆች አንድ ብር በባንክ ተጠራቅሞ ነው እናንተ የምትበደሩት ፣ ሀብታም የምትባሉት ። ድሆች በረከቶቻችን ናቸው ። ዝቅ ብለው የሚያጸዱልን ፣ ድንጋይ ተሸክመው ቤታችንን የሚሠሩልን ድሆች ናቸው ። ስንሞት የሚያለቅሱልን ፣ ሬሳችንን የሚሸከሙልን ድሆች ናቸው ። ለድሆች ይህ አይገባቸውም ። አዎ የምድሪቱ ሰንበት ተራ ትእዛዝ አይደለም ፣ ለድሆች ስለ ማሰብ የሚናገርም ነው ።  የእስራኤል ልጆች ይህን የምድሪቱን ሰንበት ስላላከበሩ አራት መቶ ዘጠና ዓመት ድሆችን ጨቆኑ ። በግብጽ ምድር 430 ዓመት ባሪያ ነበሩ ። ያንን በድሆች ደገሙት ።
3-የእግዚአብሔርን በረከት እንዲያዩና እንዲለማመዱ ነው
እግዚአብሔር በስድስተኛው ዓመት በረከት እንደሚያኖር የሚያውቁበት ነው ። ሁልጊዜ የሚኖሩት ስለ ሠሩ ይመስላቸዋል ። መሥራት መልካም ነው ። ነገር ግን የሚያኖር እግዚአብሔር ነው ። ስለዚህ ስድስቱን ዓመታት በዓመቱ በረከት ይኖሩና በሰባተኛው ዓመት በእግዚአብሔር እንደሚኖሩ ያምናሉ ። የዓመቱ ለሁለት ዓመት ይበቃቸዋል ማለት ነው ። እግዚአብሔር የእኛን እምነት የሚጨምረው እኛን በማቆምም ነው ። ተኝተን በአልጋ ፣ ታስረን በወኅኒ ባሳለፍነው ዘመን እግዚአብሔር ቤተሰባችንና እኛን ሲያኖር አይተናል ። እኛ ከቆምን የሚቆም የመሰለን ነገር ሁሉ ሲቀጥል ራሳችንን እንታዘባለን ፣ እምነትን እንለማመዳለን ። ከሥራ ከወጣሁ ቤተሰቤ ምን ይሆናል ? እንላለን ። እኔ ከሞትሁ ልጆቼ እንዴት ያድጋሉ ? እንላለን ። እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን አለማመን አይወደውም ። ከእኛ ይልቅ ለፈጠረው ያዝናል ።
4-ባሮችና አሽከሮች የዓመት ፈቃድ እንዲያገኙ ነው
በሰባተኛው ዓመት ምድሪቱ ታርፋለችና የሚያርሱ ፣ የሚቆፍሩ ፣ የሚያርሙ ፣ የሚኮተኩቱ ዕረፍት ያገኛሉ ። በምድሪቱ ላይ የቀረው በረከትም የእነርሱ ይሆናልና የጥጋብ ዓመታቸው ነው ። እግዚአብሔር ያለ ዕረፍት ስለሚሠሩ ሠራተኞች ግድ ይለዋል ። መቼ ነው ባለጠጎች ዓመት ሙሉ ያስተናገዱአቸውን ሠራተኞች አንድ ቀን ቆመው የሚያበሏቸው ? ይህ ዓመት የዕረፍት ዓመት ነውና ከዘመዳቸው ርቀው ያሉ ሠራተኞች አንድ ዓመት መገናኘት ይችላሉ ።
አዎ የምድሪቱ ሰንበት ዛሬም ሊከበር ያስፈልገዋል ። ዛሬም አሳሳቢ ነገር አለ ፡-
·       ጥቂቶች ብቻ እየደከሙ በዚያው እያለቁ ነው ። ዓለም መቅረዟ ሊጠፋ ጥቂት እየቀራት ይመስላል ። ሰንበት ይከበር ። የመገቡን ይመገቡ ፣ ያጽናኑን ክብር ይሰጣቸው ።
·       ድሆች የባለጠጎች ዒላማ ከሆኑ ሰንብተዋል ። የድሆችን ጣራ አናይም ፣ አርቁልን የሚሉ አዲስ ግልብጦች ፣ የሀብት አብሾ ናላቸው ላይ የወጣ ዛሬም አልበረዱም ። የድሆችና የባለጠጎች ከተማና መንደር እየተከፋፈለ ነው ። ይህችን ዓለም ያለ ጊዜዋ የሚያጠፋት ይህ ድንበር ነው ። ባለጠጎችና ድሆች ተመጋጋቢዎች ናቸው ። ይፈላለጋሉ ። የመንግሥትም ዓላማ የባለጠጎችን ሀብት መጠበቅ ሳይሆን ድሆችንና ባለጠጎችን ማቀራረብ ነው ።
·       የብዙ ሰው እምነቱ እየላላ ነው ። ከስግብግብነት ባቡር ተሳፍሮ መቆም ያቃተው አያሌ ነው ። መውረጃ ፌርማታውን አጥቶ በሠራው ቤት ማረፍ ፣ የወለዳቸውን ልጆች መልክ መለየት ያቃተው እየበዛ ነው ። እምነት ስለ ጠፋ ነው ሌብነት የበዛው ።
·       የድሆች መከራ ዕለት ዕለት እየጨመረ ነው ። ብዙ ዕንባ እየፈሰሰ ነው ። እግዚአብሔር መስፈሪያውን ይዞ የሰፈረልን ቀን ይከብደናል ።
 አዎ የምድሪቱን ሰንበት እናክብር ። ጾመ ነነዌን ስንጾምም ብሔራዊ ንስሐ እያደረግን ፣ እርስ በርስ እየታረቅንና እየተዛዘንን ይሁን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ