የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሮብዓም ጉባዔ

ከቢጤዎችህ ጋር አትምከር ፡፡ የሚነግሩህ የምታውቀውንና የትዕቢትን ምክር ነውና ፡፡ የቀድሞ ወዳጆችህን አትርሳ ፣ የአባትህን ወዳጅ ጠይቅ ፡፡ የተሾመን ሰው አውቀዋለሁ ብለህ አትናገር ፡፡ ካልፈለገህ በቀርም ደጅ አትጥናው፡፡ ካልፈቀደልህም ስለ ጠባዩና ኑሮው ለማንም አትናገር ፡፡ ሁለት ጆሮ ያለህ አንተ እንኳ የምትባለውን ትሰማለህ ፣ ሺህ ጆሮ ያለው ሹም የሚባለውን አይሰማም ብለህ አትሞኝ ፡፡ የዕድሜና የእውቀት እጥረት ካለባቸው ጋር አትምከር ፡፡ ባለጌን ስለ ወደደህ ብቻ አታቅርበው ፡፡ የሚሰድበው ያጣ ቀን አንተን ያዋርድሃልና ፡፡ ብልግና ሱስ ነው ፣ ሱሰኛ ዘመድ አይሆንም ፡፡ ጥሩ ድግስን አሳላፊና ባለጌ ያበላሸዋልና አሳላፊህንና ተጋባዥህን ለይ ፡፡ ፊት የልብ አደባባይ ነውና ሁሉንም ቅሬታህን ፊትህ ላይ አታስነብብ ፡፡ ጠላቶችህ ፊትህን እንጂ ልብህን እንዲያዩ አትፍቀድ ፡፡ ለስድባቸው ስድብ አትመልስ ፣ ይህ ሰምቻችኋለሁ ማለት ነውና ፡፡ ምንም ቢሆን አሁን የተሰማህን አትናገር፡፡ ከራስህ ጋር ሳትመክር ከሰው ጋር አትመካከር ፡፡ ለአንድ አሳብ የሦስት ቀን ዕድሜ ስጠው ፡፡ ባዕድ ባለበት ስለ ቤትህ አታውራ ፡፡ ለግቢህ አትጥር ፣ ለቤትህ በር ፣ ለሕይወትህ ምሥጢር ይኑርህ ፡፡ የተሻልህ ሳይሆን የበለጥህ ሁን ፡፡
የዛሬን ድል ከፈለግህ ዛሬ ማሸነፍ ትችላለህ ፣ የነገን ድል ከፈለግህ ዛሬ ተሸነፍ ፡፡ ልብን የሚስታብዩ አወዳሾችና ነቢያተ ሐሰትን ተጠንቀቅ ፡፡
በተወደድክበት ዘመን የሚጠሉህን ፈልግ ፡፡ በተወደስክበት ቀን የሚሰድቡህን አድምጥ ፡፡ ወዳጅ ከነጉድለት ይስማል ፡፡ ራስን ለማወቅ ጠላት ይጠቅማል፡፡ የአባትህ ጠላት የከረመ ጠላት ነውና በጥንቃቄ ያዘው ፡፡ አባትህ የቀማውን መልስ ፣ የበደለውን ካስ ፡፡ ጠላቱ የማያውቀውን የአባትህን ምሥጢር አውጥተህ ይቅርታ አትጠይቅ ፡፡ የሞኝ ይቅርታ ጠብ መቀስቀሻ ነውና ፡፡ በዙሪያህ ሽበታሞች መኖራቸውን አረጋግጥ ፡፡ በትልቅ አደባባይ ስለ ትንንሾች አትናገር ፡፡ በስኬትህ በጣም አትደሰት ፣ በውድቀትህ በጣም አትዘን ፡፡ ሁኔታ ይለወጣል ፡፡ ደስታና ኀዘንም ስሜት ናቸውና ያልፋሉ ፡፡ እውነት ግን ጸንቶ ይኖራል ፡፡ ብዙ ሰው የሚሰማው የምትናገረውን ሳይሆን ራሱ የሚያስበውን ነው ፡፡ ስለ ጠብ እያሰበ ከሆነ ስለ ፍቅር እየተናገርህ የሚሰማው ጠቡን ነው ፡፡ ስለ መንደር እያሰበ ከሆነ ስለ ዓለም እየተናገርህ የሚሰማው ያንን ነው ፡፡

በሰነፎች ዘመን ጠቢብ ሁን ፡፡ ሰነፍ የተባሉትም ክፋታቸው ከልካይ የሌለው ፣ ሞታቸውን የማያስቡና በንዋይ ብቻ እንኖራለን ብለው የሚስቡ ናቸው ፡፡ በፍቅር ፍትሕን አትርሳ ፣ በፍትሕ ፍቅርን አታስቀር ፡፡ ዳሩን ስትሰበስብ መሐሉ እንዳያመልጥ ከመሐሉ ጀምር ፡፡ የገዛ ቤትህ ሸፍቶ ዓለሙን ብታተርፍ የሩቅ ደስ ቢለውም አንተ ግን ዋጋ ትከፍላለህ ፡፡ የቤቱ ሲያምን ግን ተዋጊህ ሳይሆን አጋርህ ይሆናል ፡፡ የቤት ድል ቢያረፍድም ጠብቀው ፡፡ የደጁ የሚያከብርህ በቤትህ ድል ነውና ፡፡ ባለጌ ቢሻለው እንጂ አይድንምና ተሳዳቢዎችን ተጠንቀቅ ፡፡ የቤትህን ምሥጢር ሁሉንም ለእግዚአብሔር ብቻ አሳይ ፡፡ እግዚአብሔር በሰጠህ ዘመን ብቻ አገልግል እንጂ ሌላ ዘመን አትመኝ ፡፡ ሽማግሌ የሌለበት የሮብዓም ጉባዔ ነውና እውነተኛ ሽማግሌዎችን ጠይቅ ፡፡ ልቡ የጎረመሰ ሽማግሌ ፣ ልቡ የሸመገለ ወጣት እንዳለም አትርሳ ፡፡ አራቱ ጉባዔ አራት ዓይና የተባሉ ሊቃውንት የዋሉበትና ያደላደሉበት ነው ፡፡ አምስተኛው ጉባዔ ጨዋታ ነውና ብዙ አትዘን ፡፡
ለእያንዳንዱ ነገር የንዴት ዋጋ ከከፈልህ ለማበድ ተዘጋጅ ፡፡ ለምን ተሰበረ ብቻ ሳይሆን እንዴት ይጠገን የሚለውን አስብ ፡፡ ከልጅና ከባለጌ ጋር አትቀልድ ፡፡ ዘመን ከሾመው ጋርም አትጣላ ፡፡ ከካህን ጋርም አትጋጭ ፡፡
የሮብዓም ጉባዔ ከፍቅር ለእልህ ይኖራል ፡፡ በመጨረሻም ራሱን ብቻ ይዞ ይቀራል ፡፡ ከእርሱ የሚለዩትም መልካሙን ጠባያቸውን ጥለው ከፍቅርና ከአምልኮተ እግዚአብሔር የተለዩ ይሆናሉ ፡፡ ሮብዓም በአካል ቢለዩትም ጠባዩን ያወርሳልና ተጠንቀቅ ፡፡ ክፉውን በክፉ መመለስ የባሰ ክፉ መሆን ነው ፡፡ የሮብዓም ጉባዔ ለጊዜው መለያየት ፣ በፍጻሜው ጥፋትንና የተበረዘ ትውልድን ማንነቱን የከሰረ ወገንን የሚያመጣ ነው ፡፡ እንደ ሮብዓም ትንሹ እሺታ ዳገት ፣ የተከበረው ትሕትና ውርደት አይሁንብህ ፡፡ ከክፉና ከደግ ብቻ ሳይሆን ከሁለት መልካምም አንዱን እየመረጥህ መጓዝ የሕይወት ግዴታ ነው ፡፡ አንዱን ስትመርጥ አንዱን እንደምታጣ አስብ ፡፡ ማመን ውስጡ መካድ አለው ፡፡ እግዚአብሔርን ስታምን ዓለምን ክደሃል ማለት ነው ፡፡ ማግኘትም ማጣት አለው ፡፡ ለማግኘት ማጣት ፣ ለመደሰት ማዘን ግድ ነው፡፡ የሮብዓም ጉባዔ ግን ሳቅ እንጂ ደስታን አያውቅም ፡፡ እንደ ነደደህ ተነሥተህ ልቅሶህን አታበላሸው ፡፡ ያ ጊዜና ያ ትዝታ ተመልሶ አይመጣምና እርሳው፡፡ ሕይወትህን ፣ ቤተሰብህን በተንጠፈጠፈው ስሜት ምራው ፡፡ ጠገግ ያላለ ስሜት አፍራሽ ነው ፡፡
የደስታ ቋጠሮ/13
ተጻፈ አዲስ አበባ
ሐምሌ 10/2010 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ