የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሰርጉ እድምተኞች

“ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ” ዮሐ. 2፥2 ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰርጉ ሲታደም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ነው ። በዚያ አነስተኛ ድግስ ላይ ብዙ ሰዎችን ይዞ መገኘት ለሰርገኞቹ ጭንቅ ነው ። ጌታችን ግን የሰውን የሚነካ ሳይሆን የራሱን የሚሰጠን ነው ። በኋላ የለወጠው ወይን ጠጅ ከዘጠኝ መቶ በላይ ሰዎችን የሚሸኝ ነው ። ስለዚህ በአንዱ ደቀ መዝሙር ስም ቢያንስ ሰማንያ ሰው ያህል ጋብዟል ማለት ነው ። ለእግዚአብሔር መስጠት ፥ ለእግዚአብሔር አገልጋዮችም በጎ ማድረግ ማብዛት እንጂ ማሳነስ አይደለም /ማቴ. 10፥42/ ። ምክንያቱም በእኛ ትንሽ እጅ ሰፍረን በመለኮት እጅ ይሰፈርልናል ። እግዚአብሔር የማንም ውለታ ባለ ዕዳ አይደለም ። የሰራፕታዋ መበለት ባለቀ በረከቷ የረሀቡን ዘመን ያለፈችው የእግዚአብሔርን ሰው በመቀበሏ ነው /1ነገሥ. 17፥8-16/ ።
በዚያ ሰርግ ላይ ጌታችን እውነተኛውን ሙሽርነት ያስብ ነበረ ። ደቀ መዛሙርቱም ሚዜዎች ናቸው ። አንድ ሰውን ወደ ክርስቶስ ሲያመጡ ከሙሽራው ማለትም ከደስታው ጋር ያገናኛሉ ። ሙሽራውና ሙሽሪት ከተገናኙ በኋላ የሚዜው ደስታ እንደሚፈጸም አገልጋይም ምእመንና ክርስቶስን በማገናኘት የሚደሰት ነው /ማቴ . 9፥15፤ ዮሐ. 3፥29/ ። ሙሽራ ባይኖር ሚዜ እንደማይኖር ያለ ክርስቶስም አገልጋይነት የለም ። ሙሽራውን አባርሮ ሚዜን ማቀፍ እንደማይሆን ክርስቶስንም ጠልቶ አገልጋዮቹን እወዳለሁ ማለት ሐሰት ነው ። ጌታችን ባለበት ሠራዊቱ አሉ ። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ሰርጉ ታደሙ ።
ይህ ቀን ሠላሳ ዓመት ያለ ደቀ መዛሙርት ብቻውን የታየውና እናቱን ሲያገለግል የኖረው ጌታ ከደቀ መዛሙርት ጋር የታየበት ቀን ነው ። ሠላሳ ዓመት የታላቅ ውሳኔና የአስተርእዮ ዘመን ነው ። ይህ ዘመን የመርጋትና ኃይል ሳይደክም ለታየው ራእይ የሚሮጥበት ነው ። ሠላሳ ዓመት የዕድሜ ሚዛን ነው ። ሠላሳ ዓመት ሰው ራሱን ለታላቅ ራእይ የሚወልድበት ዘመን ነው ። ጌታችን በዚህ ዕድሜው ተልእኮውን ለመፈጸም ወጣ ። በደቀ መዛሙርት ተከብቦ ሲያዩት ከእናቱ በቀር ላያውቁትና ላይገነዘቡት ይችላሉ። ከሰርጉ ሲወጣ ግን አምላክነቱን አወቁ ።
“የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት ፡- የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው” ዮሐ. 2፥3 ።
በዚያ ዘመን ሰርግ ከሦስት ቀን እስከ ሰባት ቀን የሚቆይ ነው ። የአይሁዳውያን ሰርግ ደማቅና ለቀናት የሚዘልቅ ነው ። ወይን ጠጅም የአንድ ሰርግ የማይቀር ግብዣ ነው ። በቃና ዘገሊላ ግን የሆነው በመጀመሪያው ቀን እድምተኛው ገብቶ ሳያልቅ ወይን ጠጅ አለቀ ። እንኳን አልቆ ሞልቶ እንኳ በሰርግ ላይ ትችት አለ ። እንኳን አልቆ ቀጥኖ እንኳ ብዙ ሐሜት አለ ። እመቤታችን ድንግል ማርያም ዘመድ ናትና ደግሞም ቀድማ ጓዳውን አይታለችና የልጇን መምጣት ትጠብቃለች ። ከተለያትና ወደ ምድረ በዳ ከሄደ አርባ ቀን ሆኖታል እንዴት ትጠብቀዋለች ? ብንል የምትወደው ልጇ ብቻ ሳይሆን የምታምነው ጌታዋም ነውና እየጠበቀችው ነው ። የቃና ዘገሊላው ሰርግ በጅምር ሠርክ የሆነ ነው ። ሳይጀመር ያለቀ ነበር ። ይህ ሙሽሮቹን ብቻ ሳይሆን የተዛመዳቸውን የሚያሳፍር ነው ።
ይህ ዓለም ለዓመት ያሉት ለዕለት የሚያልቅበት ዓለም ነው ። ይህ ዓለም ማለዳ ሲሉት ምሽት የሚሆንበት ዓለም ነው ። ከጉዳቱ ይልቅ ሐፍረቱ አንገት የሚያስደፋበት ዓለም ነው ። ባለቤቱ ከተሸከመው በላይ የሰዎች አስተያየት የሚያሳቅቅበት ዓለም ነው ። ገና በሰርጋቸው ላይ ፍቅራቸው ያለቀ ፥ የዘመናትን ቂም የያዙ ብዙዎች ናቸው ። “የእኔ ቅሬታ የጀመረው ገና በሰርጌ ቀን እንዲህ አድርጋኝ ፥ እንዲህ አድርጎኝ ነው” የሚል ድምፅ ሲሰማ የቃናው ሰርግ ትዝ ይላል ። የዓለም ደስታ አጠገቡ ኀዘን አለ ። ነጩ ነጠላ ጥለቱ ጥቁር ነው ። ግን ነጭ ሳይሆን ጥቁር ጥለት ነጠላ ይባላል ። የሚበዛው ነጩ ክፍል ነው ፥ የሚጠራው ግን ጥቁር ነጠላ ተብሎ ነው ። በኑሮ ውስጥም የሚበዛው መልካም ሳለ የሚወራው ግን ጥቂቱ ክፉ ነው ።
ጌታ በተገኘበት ሰርግ ጉድለት ተገኝቷል ግን በተአምር ተለውጧል ። ዛሬም በእግዚአብሔር ቤት ተጋብተው ጉድለት ሊገጥማቸው ይችላል ። ግን በጌታ ይለወጣል ። ሠርክ በጅምር የሚሆኑ ብዙ ነገሮች ያለቀውን የሚቀጥለው ጌታ ያልተጋበዘባቸው ነገሮች ናቸው ። ብዙ ትዳሮች ውስጥ ዋናው ክርስቶስ ነው አልተባለም ፥ ዋናው ቪዲዮ ነው ። ቀሪው ፎቶ ነው ይባላል ። የምንኖረው ያመነውን ለመቀበል ነው ። ስለዚህ የሚቀረው ቪዲዮና ፎቶ ነው ። እርሱም የሚያምረው በኅብረት ሲኖሩ ብቻ ነው ። አሊያ ለማየትም ያስጠላል ። የልቅሶ ርእስ ይሆናል ። ብዙ ሰው ለሰርጉ እንጂ ለትዳሩ አያስብም ። ጥሩ ሰርጎች አሉ ፥ ጥሩ ትዳሮች ግን እየጠፉ ነው ። ለሰርግ ገንዘብ ያስፈልግ ይሆናል፥ ለፍቅር ግን መለኮት ያስፈልጋል ። ዛሬ ግን የሚጋባው ደመወዝ ነው ። ብሩና ብሪቱ ይጋባሉ ሰላም ይጠፋል ። ቤት የሠራ ፥ መኪና የገዛ ሰው የቀረህ ሚስት ነው ይሉታል ። ሚስትን እንደ አንድ ዕቃ ይዞ ለመግባት ያስባል ። ስለዚህ መንፈሳዊና አእምሮአዊ ክብሯን ሊጠብቅ ይሳነዋል ። የትዳር ትልቁ ስኬት የዓላማ አንድነት ነው ። ትዳር ሥጋዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ አንድነትም ነው ። ትዳር የሥጋ የነፍስ የመንፈስ ኅብረት ነው ። የሚቀድመው መንፈሳዊ አንድነቱ ነው ። ቀጥሎ የነፍስ ወይም የአሳብ አንድነት ከዚያም የሥጋ አንድነት ነው ። አሊያ እግዚአብሔር የወጣበት ኑሮ ሲታወክ ይኖራል ። ሁለት ነፍሶች በአንድ ኪዳን መታሰራቸው እርሱ ትዳር ይባላል ። የትዳር አስኳሉ የአሳብ አንድነት ፥ በረከቱ የሥጋ አንድነት ሲሆን መሠረቱ ግን የመንፈስ አንድነት ነው ወይም የአምልኮ አንድነት ነው ። ስለዚህ ለትዳር እግዚአብሔር አለው ወይ ? እግዚአብሔር አላት ወይ ?  ማለት ትልቅ መስፈርት ነው ። እግዚአብሔር ያለው ምን ይጎድልበታል ?
ሰርጉ ሳይጀመር ትዳሩን የሚፈጽሙ ብዙ ናቸው ። ሰርጉ ላይ ስለሚዘፈነው የዘፈን ዓይነት ብዙዎች ተጣልተዋል ። እየዘፈኑ የሚኖሩ ይመስል ትልቅ ደረጃ የደረሰ ጠብ ፥ የእኔ ቋንቋ ተናቀ የሚል ድምፅ ይሰማል ። አዎ ጅምሮች እንኳን ፍጻሜ ለመድረስ አይደለም፥ መልካም ጅምር ለመሆንም እግዚአብሔርን መጋበዝ ያስፈልጋል ። ለእነዚህ ጠዋቱ ለመሸባቸው ወገኖች የሚረዳው ሐሜት ሳይሆን እንደ እመቤታችን ጸሎት ነው።
ቃና የወይን ከተማ ነው ። ዛሬም ቃናን የሚጎበኝ የምትታወቀው በወይኗ ነው ። በቃናው ሰርግ ግን ወይን ጠጅ አለቀ ። እነዚህ ደጋሾች ምን ያህል አነስተኛ ኑሮ እንደሚኖሩ እንረዳለን ። ጌታ ግን እድምተኛ መሆኑ ቀረና እናቱ ስትለምነው ጋባዥ ሆነ ። የተጋበዘውም በጸሎት ነው ። ጸሎት የእግዚአብሔርን ክንድ በተጎዱ ስፍራዎች ላይ ማንቀሳቀስ ነው ። እመቤታችን ሁለት ነገሮችን አይታለች ኃይሉንና ደግነቱን ። ለጸሎት የሚረዳን ኃይሉንና ደግነቱን ማሰብ ነው ። እኛም በተጋበዝንበት ጋባዥ መሆን የምንችለው በጸሎት ነው ። የሌሎች አላለፈብኝም ለማለት ልንጸልይላቸው ይገባል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ