የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሰጠንን መስጠት

 

 

“ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን ።” ኤፌ. 4 ፡ 7 ።

 

 

የሰጠንን መስጠት የያዝነው እንዲባረክ ያደርገዋል ። እሳት ራሱን አሙቆ አያውቅም ። ጸጋም ካልሰጠነው ይዳፈናል ፣ የማይጠቅምም ይሆናል ። እግዚአብሔር ያልሰጠን ነገር የለም ። በዓለም ላይ ትልቅ ክህደት ተቀብሎ አልተቀበልኩም ማለት ነው ። ተቀብሎ አልተቀበልኩም ማለት በቃል ብቻ ሳይሆን የሰጠንን ባለመስጠት የምንገልጠው ነው ። ተቀብለው አልተቀበልኩም የሚሉ የመጀመሪያው ባለማወቅ ያሉ ሲሆኑ ሁለተኛዎቹ እግሬ አቀረበልኝ ፣ እጄ ሳበልኝ የሚሉ ናቸው ። በእግዚአብሔር ሰጪነት ሳይሆን በልፋታቸው የሚመኩ ብዙዎች ናቸው ። እግዚአብሔር ሲሰጥ እንቀበለዋለን ፣ የእጃችንን ሥራ ሲባርክም እናከብረዋለን ። እግዚአብሔር አሥራት በኵራትን የሚጠይቀን ስለሰጠን ነው ። ካላስቀመጠበት የሚፈልግ አምላክ የለንም ። አሥራት ማውጣት ተቀብያለሁ ብሎ ማመስገን ነው ። አሥራት አለማውጣትም አልተቀበልኩም ብሎ መካድ ነው ። ትንሽ በነበራቸው ጊዜ አሥራት የሚያወጡ ብዙ ሲያገኙ ይሰስታሉ ። በብር አሥራት ያወጡ የነበሩ በዶላር ሲሆን ልባቸው ፈተና ውስጥ ይገባል ። የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር የቄሣርን ለቄሣር ማለት የእግዚአብሔርን አሥራት ፣ የመንግሥትን ግብር ስጡ ማለት ነው ። አሥራትና ግብር ትይዩ ሁነው ቆመዋል ። አሥራትም ግብርም ካለን ላይ የምንጠየቀው ነው ። አሥራትም ግብርም ብዙውን ለእኛ ይዘን ትንሹን የምንሰጥበት ነው ። አሥራት ለሰማይ መንግሥት ፣ ግብር ለምድር መንግሥት የምንሰጠው ነው ። ግብር አለማውጣት መንግሥትን አለመቀበል ነው ። አሥራት አለማውጣትም የእግዚአብሔርን መንግሥትነት መካድ ነው ። መንግሥት በግብር እንደሚተዳደር የእግዚአብሔር መንግሥትም በአሥራት ይተዳደራል ። ግብር አለማውጣት በአንዳንድ አገሮች አገርን ለማፍረስ የሚደረግ ወንጀል ተደርጎ በሞት ያስቀጣ ነበር ። አሥራት አለማውጣትም ቅጣት አለው ። የምንበላው ጣዕም ፣ የምንለብሰው ሙቀት ፣ የምንኖርበት ቤት መረጋጋት የሌለው ይሆናል ። አሥራትን የምንሰርቀው የምንኖረው በብዛት ስለሚመስለን ነው ። መኖር ግን በብዛት ሳይሆን በበረከት ነው ። አሥራትን የምናስቀረው አስልተን ለእኛ ሲያንስብን ነው ። ስሌት ሥጋዊነት ፣ አሥራት እምነት ነው ። ለእግዚአብሔር ያልሰጠነውን በእጥፍ ሌባ ይወስደዋል ፣ ላንድንበት በየሐኪም ቤቱ እንጨርሰዋለን ። ቀዳዳው ይባዛል ። እንዴት እንደመጣ እንጂ ገንዘቡ የት እንደሄደ አናውቅም ።

 

የሚገርመው አሥራት የብሉይ ኪዳን ትእዛዝ ነው ። ምድረ ከነዓንን ተቀብለው አሥራት በኵራት ማውጣት ካለባቸው በሰማያዊና በምድራዊ በረከት ተባርከን ከአሥራት የበለጠ ማውጣት አለብን ። አሥራት ስናወጣ ጥሩ ፈሪሳዊ እንሆናለን ፣ ከዚያ አለፍ ስናደርግ ደግሞ ክርስቲያን እንሆናለን ። በአውሮፓ በቀደሙት ዘመናት አሥራትን የሚሰበስበው መንግሥት ነበር ። ከእያንዳንዱ ሰው ደመወዝ አሥራትን ለቤተ ክርስቲያን ይቆርጥ ነበር ። ያ ልማድ ሆኖ አሥራት ማውጣት እስካሁን ድረስ የሕሊና ጥያቄ አይሆንባቸውም ። የግብጽ ክርስቲያኖችን ደመወዛቸውን ለቤተ ክርስቲያን ያሳውቃሉ ። ቤተ ክርስቲያንም ምን ያህል አሥራት እንደምታገኝ ታውቃለችና ታቅዳለች ። በሚቀጥለው ወር ላይ ተጨማሪ ገንዘብ የሚያገኝ ከሆነ ቤተ ክርስቲያኑ የበለጠ እንድታቅድ ያሳውቃል ። ታዲያ በየትም አገር ያለ የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሠላሳ ፐርሰንት ከቻለ ሰባ ፐርሰንት ቤተ ክርስቲያኒቱ ችላ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይገዛሉ ። ለስደት ዘመን ብለው በአውሮፓና በአሜሪካ በአውስትራሊያ ለምእመናንዋ ብዙ ቤቶችን ትገዛለች ። አሥራት ስናወጣ ቤተ ክርስቲያንን የተከበረች እናደርጋታለን ። አገልግሎትን ከፍ አድርገነው ክርስትና እንዲስፋፋ እናደርጋለን ። ግብር የሚያወጣ የዚያ አገር ዜጋ ነኝ ማለቱ ነው ፣ አሥራት ማውጣትም የአማኝነትና የሰማይ ዜጋ ነኝ ማለት ነው ። የዲያብሎስን ያህል የእግዚአብሔር ሥራ እንዳይሠራ እንቅፋት የሚሆነው አሥራት የማያወጣ ምእመን ነው ። እንዴት ከዲያብሎስ ጋር ማመሳሰል ይቻላል ከተባለ ሁለቱም የእግዚአብሔርን ሥራ አስታጉለዋል ።

እግዚአብሔር የዘላለም ሕይወትን ብቻ ሳይሆን የዕለት ፍላጎታችንንም አሟልቶልናል ። መንግሥት ግብር ተቀብሎ አገርን ከወራሪና ከዘራፊ ይጠብቃል ፣ አሥራት በማውጣታችንም አገርንና ሕዝብን በጸሎት የሚጠብቁ አገልጋዮችን እንመግባለን ። ግብር ቅድመ ሁኔታ የሌለው ግዴታ ነው ። አሥራትም ቅድመ ሁኔታ የሌለው ግዴታ ነው ። የወር ወጪ የምናወጣው ለምንበላበት ቤት ነው ። እንዲሁም ቃሉን ለምንመገብበት አገልግሎት አሥራት ማውጣት ይገባል ። አሥራት ማውጣትን ለልጆቻችን ማስተማር አስፈላጊ ነው ። የነገው አገልግሎት በልጆቻችን የሚቀጥል ነው ። ልጆች ገና በጠዋቱ እግዚአብሔርንና አገልግሎትን ማፍቀር ይገባቸዋል ።

 

እግዚአብሔር ከድቃቂ ሣንቲም ጀምሮ ብዙ በረከትን ሰጥቶናልና በሰጠን ልክ መታመን ይገባል ። አሥራት በሕግ የተወሰነ ከአሥር አንድ ማለት ነው ። ከምናገኘው ሁሉ ከአሥር አንድ የእግዚአብሔር ነው ። በኵራት መጀመሪያ ላይ የምናገኘውን ልጅ ፣ ደመወዝና ከብት ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር መስጠት ነው ። መባ እንደ ፍላጎታችን ከአሥራታችን ውጭ የምንሰጠው ነው ። መባም ሦስት ክፍል አለው ። የመጀመሪያው ለእግዚአብሔር ሥራ ፣ ሁለተኛ ለአገልጋይ ፣ ሦስተኛ ለድሆች የሚሰጥ ነው ።

 

በሰጠን መጠን መታመን ይሁንልን !

 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 21 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ