መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የሰጪዎች አነሣሽ ምክንያት

የትምህርቱ ርዕስ | የሰጪዎች አነሣሽ ምክንያት

የማይሰጡ ሰዎች ያልታደሉ ናቸው:: ዘር ይዞ የማይዘራ ገበሬ፣ መሳሪያ ይዞ የማይዘምት ወታደር፣ ልጅ ወልዶ የማያሳድግ ወላጅ፣ ተማሪዎች ይዞ የማያስተምር መምህር የራሱን ዘመን፣ የሌሎችን ዕድል ያባክናል። የማይሰጥ ሰው ደስተኛ አይደለም። ጡትዋ የወጠራት እናት ካላጠባች ትጨነቃለች፣ በግድ ቸር ትሆናለች። የሚጠባ ሕፃን ብታጣ መሬት ላይ ታፈሰዋለች። ካልሰጠችው ለራስዋም  አይጠቅማትም :: ተፈጥሮ በግድ ቸርነትን ያስተምራል፤ ከሰጪው እግዚአብሔር ተገኝቷልና። ውሻ ፍቅርን፣ ላም ወተትን ሳይቆጥሩ ይሰጣሉ። መስጠት በሰው፣ በእንስሳና በአትክልት ይታያል። እግዚአብሔር በፍጥረት ሁሉ ላይ ያስቀመጠው መልኩ ሰጪነት ነው::

የማይሰጥ ሰው ዘሩን የሚበላ ገበሬ ነው። ገበሬ ለዘር ሳያስቀምጥ ቢበላ ዘንድሮ ይጠግባል፣ ለቀጣይ ግን  ረሀብተኛ ይሆናል። ስጦታ ዘር ነው። የማይሰጥ ሰው ረሀብን፣ ችግርን ከወገኖቹ ላይ መትቶ እንዲጥል እግዚአብሔር ያዘመተው ወታደር ሳለ ወገኖቹን የጭንቅ ምርኮኛ ያደረገ፣ የስቃይን ዕድሜ ያራዘመ ነው። የማይሰጥ ሰው ተቀብሎ የማያስተላልፍ ነው:: ሁሉን ነገር ያቁራል ፣  ስለዚህ መንፈሳዊና ሥጋዊ ጤንነቱ ይታጎላል። ደም መቆም የለበትም። ከቆመ መርጋት ፣ መበስበስ ፣ መሞት ይመጣል። የማይሰጥ ሰው በቁሙ የሞተ ነው፡ ፡ የተገነዙ እጆች መስጠት አይችሉም። የሚሰጥ ያልታሰረ ወይም ያልሞተ እጅ ነው:: ሁሉም ያለውን መስጠት አለበት። ስጦታ ገንዘብ ብቻ አይደለም። ፍቅር፣ ወንጌል፣ ምክር፣ ገንዘብ እነዚህ ሁሉ መሰጠት አለባቸው። የማይሰጡ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ በማይገባ መንፈስ የሚሰጡም አሉ። እነዚህ ሰዎች ከማይሰጡ ሰዎች እኩል ናቸው::  ስጦታ የራሱ የሆነ ጤናማ መንፈስ ይፈልጋል። ስጦታና ልብ የሚለያዩ አይደሉም።

ውለታ ለማስቆጠር የሚሰጡ

ድቃቂ ሣንቲም ጥለው ወዲያው ወደ ሰማይ ቀና ብለው የሚያዩ ሰዎች አሉ። ለቀኑ ፣ ለሣምንቱ የኑሮ ኪራይ እየከፈሉ መስሎ ይሰማቸዋል። እግዚአብሔርን ብቻ ሳይሆን ሰዎችንም ባለዕዳ ለማድረግ የሚሰጡ አሉ። ጌታ ሆይ እኔ ያንተ ዕዳህ ነኝ በሚል ስሜት እንደ ቀራጩ መጸለይ ሲገባቸው፣ ጌታ ሆይ የእኔ ዕዳ አለብህ በሚል ስሜት እንደሚያነበንቡ ፈሪሳዊ ሰዎች አሉ:: ስጦታ ሰው ለእግዚአብሔር የሚገዛበት ትልቁ የአምልኮ መግለጫ ነው። ሰዎች ከተመኩበት አምልኮ መሆኑ ይቀራል። በእውነት የፈሪሳውያንን ያህል አሥራት የሚያወጣ፣ የሙስሊሞችን ያህል ለድሀ የሚሰጥ ክርስቲያን በዚህ ዘመን ማግኘት ከባድ ነው። በስጦታው ፣ በትንሿ መባው ግን የሚመካ ብዙ ክርስቲያን አለ። እንኳን ሊሰጡ ጠግበዋልና ለአገልጋዮችም ለአገልግሎትም አትስጡ ብለው የሚናገሩ አሉ። ከአባ ቁፋሮ ላይ እሸት ተበልቶለት እንዲሉ ከዚያችው ስጦታ ላይ አትስጡ ተብሎበት ከባድ ነው። እግዚአብሔር ሲሰጠን ነጥብ ለማስቆጠር፣ ይመልሱልኛል ብሎ በማስላት አይደለም። ስጦታ የእግዚአብሔርን ጠባይ ለዓለም የምናሳይበት ነው። ስለዚህ ፍጹም በጸጋ መሆን ይገባዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ