እግዚአብሔር ፍቅሩን የገለጠው በስጦታ ነው። ለሥጋና ለነፍስ ፍላጎታችን ሁሉን አድርጎልን ሳለ በመጨረሻ አንድ ልጁን ለቤዛ ለመድኃኒትነት አሳልፎ ሰጠ። ከዚህ በኋላ ሚሊዮን ዓመት ብንኖርና ሚሊዮን ጊዜ ቢደረግልን ከተደረገልን አይበልጥም፣ እርሱም መዳናችን ነው። ራሳችንን አማኝም አገልጋይም ሆነን ያገኘነው በስጦታው ነው። ይህ ስጦታም የማይገባ ደግነት ነው፣ ጸጋ ተብሎም ይጠራል። እግዚአብሔር ብዙ ነገሮችን ሰጥቶናል። ፀሐይን ለመሰማራት ፣ ለማየት፣ ለኃይል ማመንጫ ፣ ለጤናችን ሰጥቶናል። ፀሐይ ባትኖር ኖሮ በቀዝቃዛ አየር በረዶ ሆነን እንቀር ነበር። በአንድ ከተማ ላይ በምሸት ከሚሊዮን በላይ መብራቶች ይበራሉ፣ ጨለማውን ማጥቃት አቅቷቸው ከተማይቱ የተቃጠለች ትመስላለች። እግዚአብሔር ግን በአንዲት ፀሐይ ጨለማን ያስወግዳል። ቀን ብለን ለመጥራት፣ የዘመን ስፍርን ለመለካት የፀሐይ መኖር አስፈላጊ ነው::
ሕፃናት ገና በጨቅላነታቸው ፀሐይ ይሞቃሉ፣ ለተስተካከለ የአጥንት ጤንነት የፀሐይ ብርሃን አስፈላጊ ስለሆነ ነው። በዓለም ላይ ኃይል ማመንጨትና ያንን ወደ ብርሃን መለወጥ በባለጠጎች እንኳ የሚደፈር አይደለም፣ የመንግሥታት ዕዳ ነው። እግዚአብሔር ግን ፀሐይን በቃሉ ፈጠረ። ከ400 ፐርሰንት በላይ የመብራት ክፍያዎች ሊጨምሩ ይችላሉ፣ አስከፋዩ አካል ኃይል የሚያመነጭ ፣ ኃይል የሚያቀርብ ሁለት ተቋም መሥርቶ ይፋጠናል። እግዚአብሔር ግን ግድብ ሳይገድብ ፣ ሽቦ ሳይዘረጋ፣ ምሰሶ ሳይተክል ፣ ቆጣሪ ሳያስገባ ብርሃን ሰጥቶናል። ድሆች ወይም ቸልተኞች ባለመክፈል ኃይል ይቋረጥባቸዋል ፣ እግዚአብሔር ግን ፀሐይን ያቋረጠበት ድሃና ጠላት የለም። አንዳንድ ሰፈሮች መብራት ካልጠፋ ባለሥልጣን አለ ተብሎ ይታሰባል፣ እግዚአብሔር ግን በቤተ መንግሥትም በድሃዋ ቤትም ፀሐይን ያወጣል። በየወሩ ቆጣሪ አንባቢ አለ፣ ብዙ ሒሳብ እንዳያመጡ ልባችን ይደነግጣል። እግዚአብሔር ግን ለፀሐይ ያስከፍላል ተብሎ አይሰጋም። ለመላው ዓለም አንዲት ፀሐይ ሰጠ ፣ ከጥንተ ፍጥረት ጀምሮ እስከ ዛሬ ታበራለች። እግዚአብሔር ይችላል፣ ሲችልም ከፍቅርና ከሰጪነት ጋር ነው። መብራት ኃይል የፈለጋችሁትን ተጠቀመ፣ ብቻ ምስጋና ብቻ አቅርቡ ቢለን በመገረም ፣ በደስታ ፣ ብዙ ምስጋና እናቀርባለን፣ ደሞ ለምስጋና ብለን እናዥጎደጉደዋለን። እግዚአብሔርን ግን ስለ ፀሐይ አመስግነን እናውቅ ይሆን ?
እግዚአብሔር የሰጠን አንዱ ስጦታ ሙሉ ቀን ቢወራ አያልቅም። ፀሐይ የምሥጢረ ሥላሴ ምሳሌ ናት። ተፈጥሮ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ነው። ከአምፖል ምንም አንማርም፣ እግዚአብሔር ግን ይጠቅማል፣ ያስተምራል:: ተፈጥሮን ቤተ ዘመድ አድርጎ ሰጥቶናል። የአንዱ መታጣት ጉዳት ያመጣብናል። ስጦታው ብዙ የሆነ አምላክ ጠባዩን በእኛ ሊያይ ወዶ ስጡ አለ።
የስጦታ ዓይነቶች ብዙ ናቸው፦
አሥራት
ከአሥር አንድ ማለት ነው። አሥራት የልቡና ሕግ ነው። ስለዚህ አብርሃም ለመልከ ጼዴቅ አሥራት አወጣ። ያዕቆብም እንጀራ ብትቆርስልኝ አሥራት አወጣለሁ ብሎ ተሳለ (ዘፍ, 18 : 20 ፤ 28 : 22)። ዛሬ በሌለን ሰዓት በምኞት እንቸራለን፣ ስናገኝ እንሰስታለን። አንዳንዱ በብር አሥራት ያወጣል፣ በዶላር ሲከፈለው በዶላር ለመክፈል ይንቀጠቀጣል። እግዚአብሔር ታዝቦናል !
በኵራት
ከእንስሳት በኵሩ ለእግዚአብሔር ይሰጣል። አባወራ ሳይቀምስ ዶሮ አይበላም ነበር፣ የቤታችን ራስ ጌታ እግዚአብሔር ሳይቀምስ መብላት ነውር ፣ ክብረ ነክ ነው። ከልጅም በኵር የእግዚአብሔር ነው።
ቀዳምያት
የእንስሳ በኵር አርቢዎችን ይመለከታል፣ ቀዳምያት ደግሞ ገበሬዎችን ይመለከታል፣ ይህ አሁንም በገጠሩ አለ ። በእህል አሥራታቸውን ይሰጣሉ። በብሉይ ኪዳን በዓለ ሰዊት ተብሎ የሚጠራው በዓለ ጰንጠቆስጤ የቀዳምያት በዓል ነው ። የፍሬው ባለቤት፣ የዝናቡ ጌታ አንተ ነህ ማለት ነው። ስርቆትን የሚጸየፍ ብዙ ነው፣ እግዚአብሔርን መስረቅ ግን አይጸየፍም።
መባዕ
አሥራት ከደመወዝ ፣ በኵራት ከእንስሳ ፣ ቀዳምያት ከእህል ከፍሬ ሲሆን መባዕ ግን በፈቃድ የሚደረግ ስጦታ ነው፡ ፡ አማራጭ ሳይሆን የፈቃድ ግዴታ ነው:: በእግዚአብሔር ፊት ባዶ እጅ መታየት አይገባም::
ምጽዋት
ለድሆች የሚሰጥ ሲሆን ካለን ላይ በማካፈል ገዳዩን ረሀብ እንበቀለዋለን። ሰው እውቀቱን ፣ ምክሩን ትምህርቱን ማካፈል አለበት።
ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝቶ የሚማረው ሌሎች ስለሰጡ ነው። ግን የሚሰጡትን አያስታውሳቸውም :: ስንሰጥ ወንጌል ይሰበካል፣ ትውልድ ይድናል። አለ መስጠት አልተቀበልኩም ብሎ መካድ ነው!
በመስጠት ይባርከን!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 13 ቀን 2018 ዓ.ም.