የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቀኑ ወለላ

 

ወዳጄ ሆይ !

አንተ ላጣኸው የሚሸሽህ ሲበዛ አትገረም ፤ ፀሐይ ስትጠልቅ እንኳን ሰው የገዛ ጥላህም ይሰወራልና ። እግዚአብሔር የዘገየ የመሰለህ አንተ ስለቸኮልህ ነው ። የእግዚአብሔር ቀን በድንገት ትመጣለችና ተዘጋጅተህ ኑር ። ትልቅ ጅማሬ ከፈለግህ ፍጻሜህ ትንሽ ነው ፤ ትንሽ ጅማሬም ፍጻሜው ትልቅ ነው ። ጥርስና ምላስ ቢነካከሱም ፣ ጥርስና ምላስ ባይመሳሰሉም አብረው ይኖራሉ ። ብንጣላም ሳንጠላላ መኖር ግድ ነው ። አንድን ነገር ስታገኝ ሌላውን እንዳጣህ እወቅ ። በጅምርህ ሰዎች ሲንቁህ በአቅምህ ሳይሆን በራሳቸው አቅም ለክተውህ ነው ። ራስህን ካላበረታኸው የሚያዳክምህ ብዙ ነው ። ያለ አስታዋሽ ቁርስ እየበላህ ለጸሎትና ለቃለ እግዚአብሔር አስታዋሽ አትሻ ። 

ወዳጄ ሆይ !

በክፉ ሥራህ የሰው ዓይን ባያይህ ሕሊና አይቶሃልና መሰደድን አታቆምም ። ድንጋይ በውኃ ውስጥ ቢኖርም አይርስም ፣ እንዲሁም ቃሉን እየተማሩ የሚደነድኑ አሉ ። ድንጋይ መኖሪያው ውኃ ውስጥ ቢሆንም ዋና አይችልም ይባላል ፣ ሰዎችም እረኛ ተብለው ስለተሾሙና በቤተ ክርስቲያን ስላሉ ብቻ መምራት ይችላሉ ማለት አይደለም ። የሰማኸውን ስብከት እየረሳህ የሰማኸውን ስድብ ማስታወስ ተገቢ አይደለም ። አንተ እንድትፋፋ የከሱልህን አትርሳ ። አገርህን ቀብረህ ቀና ብትልም የሚያይህ የለም ። አገርህን አፍርሰህ ሰው አገር ብትቀመጥም አንድ ቀን መግቢያ ታጣለህ ። ብዙ ወዳጅ እንዳለህ ብታስብ እውነቱን የሚነግርህ የመከራ ቀን ነው ። 

ወዳጄ ሆይ !

ሰውን በልብሱና በቤቱ ትልቅ ነው ብለህ አትለካው ። የሰዎችን ምሥጢር ለማወቅ አትጓጓ ። የተሸከመህን መሸከም ክብር ነው ። ሰውን በደንብ እስክታየው የእንስሳት ፍቅር አይገባህም ። ና ብሎ ዕዳ እንዲሉ መለወጡን ሳታይ የቀድሞ ባለጌን አትጥራ ። ወደ ኋላ ለምስጋና ፣ ወደፊት ለግብ ተመልከት ። በዓለም ላይ ሦስት ርካሽ ሰዎች አሉ ። አራተኛውን ግን መሬት አይችለውም ። ተሰጥቶአቸው የማያውቁበት ፣ የነበሩበትን የረሱ ፣ በሰው ውድቀት የሚስቁ ርካሾች ሲሆኑ አራተኛው ግን አምላኩን የካደ ነው ። ሰዓቱ አለፈ ብለህ ከንስሐ አትዘግይ ፤ በሕይወት እስካለህ የንስሐ ዕድል መሆኑን ተረዳ ። እግዚአብሔር ሲደርስ የባከኑ ዘመኖችን ይክሳል ። ሰይጣን የሚፈትንህ ትዕግሥት እንድታጣ ነው ፤ ከዚያ በኋላ የምትወድቀው አንተ ነህ ። አዳም አንድ ጊዜ በሰይጣን ተፈተነ ፣ ውድቀቱ ግን ውድቀት እየወለደ ሲንከባለል ኖረ ። እንደ ጠበቅከው አለመሆኑ ሰው የመሆንህ መገለጫ ነው ። 

ወዳጄ ሆይ !

በሞላ ውኃ አለመታጠብ ፣ በበዛ ቃለ እግዚአብሔር አለመማር ትልቅ ክስረት ነው ። እንደ ማግኔት ተቃራኒህን ካልሳብህ የክርስቶስ ፍቅር ባንተ ላይ የለም ። በየቀኑ እንዳታዝን ስሜትህን ሳይሆን እውነትን ተከተል ። ሌሎችን ማክበር ያለብህ አንተ የሌለህን ስለያዙ ነው ። እያንዳንዱ ትምህርት ሕመም አለው ፤ እያንዳንዱ ሕመምም ትምህርት አለው ። ሕይወትን ዘወትር አዲስ የሚያደርጋት ክፉዎች ቆመው ደጎች ሲወድቁባት ነው ። እንደ ጤና ጣፋጭ ፣ እንደ ፍቅር ማዕረግ ፣ እንደ ይቅርታ ድል ፣ እሰው ፊት እንደ መቆም መራራ የለም ። የገዛኸው እህል አንዱ ፍሬም ሲንጠባጠብ ይቆጭሃል ፣ እግዚአብሔርም በአምሳሉ የፈጠረው ፣ በደሙ የገዛው አንድ ሰው ሲሞት ያዝናል ። ለመፍረድ አቅም ያገኘኸው ለማፍቀር ጉልበት ስላጣህ ነው ። ሌሎችን መጥቀም ትልቅነት ነው ፣ ካልሆነልህ ግን አለመጉዳትም ጨዋነት ነው ። እውነተኛ አስታራቂ ቢኖር ብዙ እሳቶች በበረዱ ነበር ። 

ዲያቆን አሸናፊ መኮንን

ኅዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ