የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የበዛ ጥበብ

“ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን ።” ኤፌ. 1 ፡ 8 ።

ጸጋው ካስገኘልን ነገሮች ጥበብና እውቀት ተጠቃሽ ናቸው ። የመጀመሪያው ጥበብ ሲሆን ሁለተኛው አእምሮ ነው ። ጸጋው ድኅነት ሲሆን ድኅነትም ጥበብና እውቀትን አብዝቶልናል ። ጥበብ ምንድነው ብለን መጠየቃችን አይቀርም ። ጥበበኞች የሚባሉም ያለባበስ ቄንጥ ያላቸው ፣ በየመድረኩ ሰውን የማሳቅ አቅም ያዳበሩ አይደሉም ። ጥበበኞች ስንል ብልጦች ማለታችን አይደለም ። የአበላል መንገዱ የገባቸው እነርሱ ጥበበኛ አይባሉም ፣ የሚባሉት ቀማኞች ወይም ሕጋዊ ሌቦች ነው ። ጥበበኛ ዘመን የገባው ሳይሆን ዘመኑን ለእግዚአብሔር የሚያስገዛ ነው ። ጥበብ ከበላይ ያለውን እግዚአብሔር እንድንፈራ ፣ የበላዮችን እንድናከብር ታስተምራለች ። ፈሪሀ እግዚአብሔር በነፍስ በሥጋ ትፈውሳለች ። የበላዮችን ማክበርም ከውርደት ያድናል ። ጥበብ በአሁኑ ሁኔታ አትታጠሩ ፣ በአሁኑ ማግኘት ትዕቢት ፣ በማጣትም ድንጋጤ አይግባችሁ ትላለች ። ጥበብ የማትናገርበት ቀን የለም ፣ ሰዎች ግን የማይሰሙበት ዘመን ብዙ ነው ። ጥበብ ያጣ በአፉ እየደለለ ፣ በልቡ እየገደለ ይኖራል ። ጥበብ ያጣ ሁሉንም በብልጠት እይዛለሁ ብሎ በመጨረሻ እንደ ሞኝ ሁሉም ያውቀዋል ። ጥበብ በሚያልፈው ቀን የማያልፈውን ፣ በምድር ላይ ሰማይን ታስተምራለች ። በዓለም ላይ ድንቁርና የተስፋፋው ትምህርት ጠፍቶ ሳይሆን የሚማር ጠፍቶ ነው ።

ጥበብ አእምሮ ላይ የሚሰማን ደስ የሚል ጨዋታ ፣ ሰውን አታሎ መግባት ፣ ሁሉንም ላለማስቀየም እሺ ፣ እሺ ማለት አይደለም ። ጥበብ ፍትሕን መፈለግና ለእውነት ዋጋ መክፈል ነው ። ጥበብ እውነትን ያከበረ እንጂ የሠዋ ፍቅርን አትሻም ። ጥበብ ሞትን እያሰቡ ቅንነትን በየዕለቱ መጨመር ነው ። የትም ከፍታ ላይ ቢወጡ መውረድ ፣ ከመሬት በታች መሆን አይቀርም ። ያ ሁሉ ክብርና ዝና በሁለት ፊደል ይከተታል ። “ሞተ” በሚለው ይዘጋል ። ጥበብ ፈራሽነትን እያሰቡ ገዳይነትን መጠየፍ ነው ። እርሱ ሞቶ እኔ አልቀርምና ። ጥበብ ጥበበኞች ነን ከሚሉት እጅግ የራቀች ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔር ባለበት ያደረች ናት ። ጥበብ በማስታወቂያ ኃይል የቆመች ሳትሆን የምትፈለግ ስውር እጅ ናት ። በዓለም ላይ ትልቁ ድንቁርና አዋቂ ነኝ ብሎ ማሰብ ነው ። ጥበበኛ ነን ሲሉ እጅግ መደንቆር ይከሰታል ። ዓለም ተጠበብሁ ብላ በመጨረሻ የሠራችው እንኳን ሰውን ቅጠል የማያስቀረውን የኒውክለር አረር ነው ። ጥበብ አውቆ ትሑት በሚሆን ሰው ልብ ውስጥ አለች ። የጥበብ መቀመጫው ነፍስ እንጂ ግድግዳ አይደለም ። በግድግዳቸው ላይ ሥዕል ስለሰቀሉ ጥበበኛ ናቸው ማለት አይደለም ። ጥበብ ግን ለጥበብ ዋጋ አላት ። ጥበብ በአገራችን እንደ ራቀን መጽሐፍ በቅናሽ ዋጋ ፣ ሥጋ በጭማሪ ሲሸጥ ማየት በቂ ነው ። ጥበብ የከዳው ትላንትን ፣ ዛሬንና ነገን ያበላሻል ። ትላንት የሌላትን ዛሬ የሚፈጥሩ የጥበብ ጠላቶች ናቸው ። ዛሬ ትላንት ከሌላት ነገም የላትም ።

ጥበበኞች የዛሬን ትውልድ ሳይዘነጉ ለነገው ትውልድ ያቅዳሉ ። ጥበበኛ የጥበብ ቃላት የሚናገር አይደለም ። እርሱንማ የመቅረጫ መሣሪያውም የቀረጸውን ይናገረዋል ። በቀቀንም የሰማችውን ስትደግም ትውላለች ። የገደል ማሚቱም ያስተጋባዋል ። ጥበብ ኑሮ ነው ። ጥበብ የሚሞቱለት ምክንያት ነው ። ምን ቢሞላ ነገ መጉደሉ ፣ ምን ቢጎድል ነገ መሙላቱ አይቀርም ። ጥበብ የሚያጸጽት ነገር ላለማድረግ ፣ ከመግደል መሞት እንደሚሻል ታስተምራለች ። ያዳነን የገደለው ጲላጦስ ሳይሆን የሞተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ጥበብ ለጆሮ በጣዕም ፣ ለዓይን በውበት ፣ ለልብ በዕረፍት መገለጥ ነው ። ጥበብ ክፉ ልማድን በበጎ ልማድ ትለውጣለች ። ጥበበኞች በማውገዝ ሳይሆን መልካሙን ነገር በማሳየት ሥነ ምግባርን ገናና ያደርጉታል ። ጥበበኛ ሳይታገል ሰዎቹ የያዙትን የተነቀለ ቦምብ መቀበል ይችላል ። ጥበብ ከሁሉም ፍጥረት ትምህርት እንዳለ አምኖ ማስተዋል ነው ። ጥበብ ቅድስናን በልብስ ፣ ቅንነትን በሽቱ የሚለውጥ አይደለም ። ጥበብ ሰውን በላይ ቁመናው አይለካውም ። ያማ ቢሆን ረጃጅሞች ለሰማይ ስለቀረቡ ሀገረ ሕይወትን በወረሱ ነበር ። ጥበብ ለጥበብ ክብር አለው ። ጥበብ ጠቢብን ያውቃል ፣ ያከብራል ። እውነተኛው ጥበብ ክርስቶስ ነው ።

ጥበብ መላውን ሕይወት የሚገዛ ፣ በትጋት ላይ ጥንቃቄን ፣ በትዕግሥት ላይ ደስታን የሚጨምር ነው ። እየተጉ የሚያፈርሱ ፣ እየታገሡ የሚከስሉ አሉና ። ጥበብ ሰዋዊ ፣ አጋንንታዊ ፣ ሰማያዊ ተብሎ ሊከፈል ይችላል ። ሰዋዊ ጥበብ ሕይወትን የቁስ ጥገኛ ሲያደርግ ፣ አጋንንታዊ ጥበብ ፌዝን ያነግሣል ። ሰማያዊ ጥበብ ጊዜን በትክክል ይጠቀማል ። ጠቢብ ከበደልሁ በዚያው ልጥፋ አይልም ። በደልን መቀነስ ቅድስና ፣ ለዓለምም መፍትሔ እንደሆነ ያውቃል ። በነቃ ቀን ቶሎ ይመለሳል እንጂ ሞት ላይ አይተኛም ። ጥበብ ከእግዚአብሔር ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት መፍጠር ነው ። ሳይበላ ራበኝ የሚል ሞኝ ነው ። ቃለ እግዚአብሔር ሳያገኝም ሰላም አጣሁ ብሎ የሚደነቅ ጥበብ ያጣ ነው ። ጥበብ የሌላው ሁከት የእኔ ሰላም ነው አትልም ፣ የሌላው ሰላም የእኔ ሰላም ነው ብላ ታምናለች ፣ ለዚያም ትሠራለች ። ቸር ክርስቶስ ሆይ ጥበብ አብዛልን ፣ በአንተ ድነናልና !

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /16

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 29 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ