መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የባለጠግነት ፈተና » የባለጠግነት ፈተና -2

የትምህርቱ ርዕስ | የባለጠግነት ፈተና -2

ባለጠጋ መሆን ኃጢአት አይደለም ። አብርሃም ፣ ይስሐቅ ፣ ያዕቆብ ፣ ዳዊት ፣ ሰሎሞን ፣ ኒቆዲሞስ ፣ ዮሴፍ ዘአርማትያስ ባለጠጎች ነበሩ ። እግዚአብሔር የሀብታት ባለቤት ነውና ሀብትን ለሰዎች ይሰጣል ። በምድር ላይ ያለውን መሬት ፣ ወርቅና ብር ስለ ያዙ ሰዎች ባለጠጋ ይባላሉ ። ምድርና ሞላው የእግዚአብሔር ነውና የባለጠግነታቸው ምሥጢር እርሱ ነው ። ባለጸጋ ማለትም ባለ ስጦታ ፣ ተቀባይ ፣ ባለ አደራ ፣ ተጠያቂነት ያለው ማለት ነው ። ሀብት ተጨማሪ ኃላፊነት መሆኑን ብዙ ሰዎች አያውቁም ። አብርሃም በሀብቱ እንግዶችን ይቀበልና ያስተናግድ ነበረ ፣ ዳዊት ለእግዚአብሔር ቤት መሥሪያ ያስቀምጥ ነበር ፣ ሰሎሞን መቅደሱን ሠራ ። የእስራኤል ልጆች ከግብጻውያን በበዘበዙት ብርና ወርቅ የማደሪያውን ድንኳን ተከሉ ። ብዙ ሴቶችም ጌታችንን በገንዘባቸው ያገለግሉት እንደ ነበር ተጽፎአል (ሉቃ. 8 ፡ 3) ። ቆሞ የሚሰብከውን ሰባኪ ያህል በገንዘብም ማገልገል ይቻላል ። ሰው የሚያገለግለው በተሰጠው ነገር ነው ። የተሰጠን ነገር ማገልገያችን እንጂ ራሳችንን እንደ ጌቶች የምናይበት አይደለም ። ገንዘብ አገልጋይ ባሪያ ፣ መገልገያ ቁስ ሲሆን የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ይችላል ።

ባለጠግነት ኃጢአት ባይሆንም ለመንፈሳዊነት ፣ ለሥነ ምግባር ተጨማሪ ፈተና ሲሆን ይታያል ። ገንዘብ አመሉን የማይወስድበት ሰው የጸና አቋም ያለው ሰው ነው ። ገንዘብ መልካሙን ጠባይ ወስዶ የራሱን ክፉ ጠባይ ይሰጣል ። በማቴዎስ 19 ላይ የምናገኘው ወጣት ባለጠጋ የነበረው ፣ ሀብት ጌታን እንዳይከተል እንቅፋት ሆኖበት ነበር ። ይህን ሰው አላውቀውም ብንል ለእርሱ የተነገረውን ቃል ግን እናውቀዋለን ። “ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል” የሚለውን ሁላችንም እናውቀዋለን ። ባለጠጎች ሲያናድዱን የምንጠቅሰው ስለሆነ ነው ። በኢየሩሳሌም ትንሽ በር ነበረ ። ይህ በር የመርፌ ቀዳዳ የሚል ስያሜ ነበረው ። ግመል በዚህ በር ለማለፍ ከነጭነቱ አይችልም ፣ ራሱም ቆሞ ማለፍ አይችልም ። ስለዚህ ተንበርክኮ ማለፍ ነበረበት ፣ እየታከከ ሲያልፍም ቆሻሻውን ያራግፍ ነበር ። ግመል ወርቅ ፣ ዕጣን ፣ ሽቱ ጭኖ የሚጓዝ ነው ። እነዚህ ነገሮች ውድ ቢሆኑ እንኳ እነርሱን ተሸክሞ በዚያ በር ማለፍ አይችልም ነበር ። ራሱም መንበርከክ ነበረበት ። ሰው በሀብቱ አሊያም በትምክሕቱ ሁኖ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይችልም ። የሰጠውን ለሰጠው ጌታ መልሶ መስጠት አለበት ። የባለጠግነት ፈተና፡-

የዝና ጥማት

ሰዎች ባለጠጋ ከሆኑ በኋላ ዝናን ይፈልጋሉ ። ዝናን በሥራ ካጡት ዝነኞችን በመጠጋት ለማግኘት ይመኛሉ ። ብዙ ባለጠጎች ከድሀ ጋር ሳይሆን ከዝነኛ ጋር የሚውሉት ለዚህ ነው ። ዝነኛው ብር የለውም ፣ ባለጠጋው ዝና የለውም ። ይልቁንም ወጣት ባለጠጎች እውቀትን ይሰበስባሉ ፣ እውቀታቸው በራሱ ሀብት መሆኑን ስለማያምኑ ለገንዘብ ማግኛ ብቻ ይጠቀሙበታል ። ገንዘብ የኪስ ሀብት ፣ እውቀት የነፍስ ሀብት ቢሆንም እነርሱ ግን የነፍስ ሀብትን ለኪስ ሀብት ያስገዛሉ ። ወጣት ባለጠጎች መሽቀርቀር የሚወዱ ግን ስስታሞች ናቸው ። ወጣት ባለጠጎች ንግግር አሳማሪ ፣ የተጠና ውሸት ባለቤትና እጅግ ብልጥ ናቸው ። ማንን ቢጠጉ ምን ማግኘት እንዳለባቸው የሚያሰሉ ፣ ምን አገኛለሁ  እንጂ ምን እሰጣለሁ  ለማለት ያልታደሉ ናቸው ። የሚቆጠበውም ሲኖር ነው ፣ ቢሆንም የሚሰጡትም ሲኖር ነውና ባለጠጎች ቸር መሆን አለባቸው ። ያልራበውን ይሉኝታ ለማስያዝ ፣ የሀብትን መጠን ለማሳየት በየቀኑ በሚሊየን ሲጋብዙ ይውላሉ ፣ ለድሀ ድቃቂ ሣንቲም ለመስጠት ግን ይታመማሉ ። ቤተ ክርስቲያንንም የዝናቸው አደባባይ ለማድረግ የሚሹ አሉ ። ወንጌልን የሚገፉ ፣ ገንዘባቸውን ሊቃውንት ለማሳደድ የሚበጅቱ ያልታደሉ አሉ ። በዚያው መጠን የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩ ጥቶች ይኖራሉ ። ዓለሙ ግን አንድ ማኅበረተኛ ስለሆነ ሐሰተኛው ባለጠጋ ሐሰተኛ አገልጋይን ይደግፋል ።

ዝና ታዋቂነት ነው ፣ ከበሬታ በአደባባይ እጅ የመነሣት ጥማት ነው ። የብዙዎች የዕለት ርእስ መሆንን ብዙ ባለጠጎች ይመኛሉ ። ከባለጠግነት ቀጥሎ ያለው ዝና ሳይሆን የድሀ ልጆች ማሳደጊያ ፣ የአረጋውያን መጦሪያን መገንባት ነው ። ማግኘት እንዳለ ማጣት አለ ፣ በሚጠፋ ገንዘብ የማይጠፋ ሥራ መሥራት ዕድለኝነት ነው ። ገንዘብ ብንጨብጠውም ልናየው ግን ላንበላው እንችላለን ። የበዪ ተመልካች ለመሆን ፣ ለነጻ ዘበኝነት ገንዘብን መያዝ ጥቅም የለውም ። ወጣቱ ባለጠጋ ጌታ ዝነኛ ነውና በአደባባይ መምህር ሆይ ብዬ ባመሰግነው እርሱም የክብር ቃል ይሰጠኛል ብሎ የመጣ ነው ። የእገሌ ሰርግ ጳጳሳት የተገኙበት ነው ይባላል ። ሰርግን ክቡር የሚያደርገው ዓላማውና በአንዲት ክህነት መከናወኑ ነው ። ቡራኬው አንድ ነው ። የእገሌ ልቅሶ ጳጳሳት የታደሙበት ነው ይባላል ፣ ተገኙ እንጂ ሬሳውን አያሥነሡትም ። የባለጠጋ ጸሎተ ፍትሐቱ ረጅም ነው ፣ ድሀውን “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” ብለን አቻኩለን ስንሸኝ አምላካችን ይታዘበናል ። ዓለም የጥቂቶች ናት ፣ እግዚአብሔር ግን የሁሉ አምላክ ነው ! የዓለም ታሪክ የምንለው የጥቂት ግለሰቦች ታሪክ ነው ፣ የዓለም ታሪክ የማያውቃቸው በልበ ሥላሴ የተጻፉ ግን አያሌ ናቸው ።

ይቀጥላል

ሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ