ረቡዕ፣ ጥቅምት 8 2004
ጥሪ አልባ ጉዞ ምሪት አልባ ሩጫ
ራዕይ አልባ እቅድ ግብ አልባ ፍጥጫ
ሠላም አልባ ህይወት ጎብጦ መንከራተት
ክብር ያጣ ማንነት ንቀት የበዛበት
ቃሉ አይነበብ ድምጹ አይሰማኝ
ዕውቀቴ ብዙ ነው ምንስ አዲስ ላገኝ?
ባለኝ እውቀት መጠን መንፈሣዊ ሰው ነኝ፤
ክፉ በሚመስል ቦታ በመዋሌ
አትበሉኝ ጠፍተሀል ሆነሀል አለሌ፤
በማለት ራሴን እንዲሁ ሸንግዬ
በክፉ ሀሳቤ ውስጤን አታልዬ
ክፉ ሆኖ ሳለ መልካሜ ነው ባልኩት
ከንቱ ወዳጅነት የነገሰበት
ቃሉ ቦታ አጥቶ የከረምኩበት
ዝማሬ ተገፍቶ ዘፈን ከፍ ያለበት
እልልታ ተውጦ ጩኸት የበዛበት
ያ የያኔው ጉዞ ያ የያኔው መንገድ
አሁን ጌታን ይዤ ቀጥ ብዬ ስሄድ
የሰጠኝን ሰላም ፍቅሩን ስመለከት
ያደረገልኝን መልካም ነገር ብዛት
የሰጠኝን ሞገስ በብዙ በረከት
የፍቅር እጁ ዳሶኝ ጥቅሜን ስመዝናት
በዘፈን በስካር እንዲሁም በዝሙት
አሁን ይቆጨኛል የባከነው ሰዓት